በኢትዮጵያ ገና ለምን ታህሳስ 29 ይከበራል?
በመሐሪ አድነው
የአውሮፓውያንን የጊዜ ቀመር በሚከተሉ ሀገራት የክርስቶስ ልደት /ገና/ ታህሳስ /ዲሴምበር/ 25/ታህሳሳ 16/ ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ1ዐ በላይ ሀገራት በዓሉን ከ12 ቀናት በኋላ ታህሳሳ 29 ያከብሩታል፡፡ “እንዴት ሊሆን ቻለ?” ሲል ቢቢሲ የሃይማኖት ሊቃውንትን ጠይቆ ከአመታት በፊት የሠራውን ዘገባ እንዲህ አዘጋጅተናል፡፡ “የጐርጐሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ያመጣው ፍልሰት” የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የዘመን አቆጣጠር የተለየ ነው፡፡
በሁለቱ የዘመን አቆጣጠሮች መካከል አንደኛ ሠባት አመት ከስምንት ወር ከአሥር ቀን ልዩት አለው፡፡ ሁለተኛ እያንዳንዱ ወራት የሚይዟቸው ቀናት ልዩነት አላቸው፡፡ “በእያንዳንዱ ወር ውስጥ ከስድስት እስከ አሥር ቀናት የሚደርሱ ልዩቶች አሉ፡፡” ይላሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የዘመን ቀመር /ባህረ ሃሳብ/ ዙሪያ መፅሐፍ ያሳተሙት መጋቢ ጥበበ በእምነት ምትኩ፡፡
“የጐርጐርሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር እስከ ጀመረበት ድረስ መላው ዓለም ተመሳሳይ የዘመን አቆጣጠር እንደነበረው ይታመናል” የሚሉት መጋቢ ጥበብ በእምነት “ነገር ግን በ1382 ዓ.ም የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳስ የነበረው ጐርጐሪዮስ የዘመን አቆጣጠሩ ችግር አለበት በሚል እንደገና እንዲሰላ ወሰነ። ከዚያም በአንድ አመት ውስጥ 365 ቀን ከ6 ሠዐት ነው ያለው የሚለውን ሃሳብ በማንሳት በየአመቱ አንድ አንድ ሠዐት ተጨምሯል፡፡” ይላሉ፡፡
ስለዚህ እንደ መጋቢ ጥበብ በእምነት ይህ አንድ ሠዐት ተጠራቅሞ መጨመር አለበት በማለት ከኒቂያ ጉባኤ ጀምሮ ያለውን አስልቶ በማሳሰብ 1ዐ ቀን በመሙላቱ ጥቅምት /ኦክቶበር/ 5 የነበረውን ጥቅምት 15 ነው ሲል አውጇል፡፡ “ስለዚህ በእኛና በእነርሱ መካከል እየቀነሰ የሚሄድ ቢሆንም የ1ዐ ቀናት ያህል ልዩነት አለ።” እንግዲህ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከኖህ ዘመን ጀምሮ የነበራትን የቀን አቆጣጠር ጠብቃ ይዛ የቀጠለችና ምንም ነገር ያላሻሻለች በመሆኗ የነበረው እንዳለ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ በተመሣሣይ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳትሆን የግብፅ ቤተክርስቲያንም ምንም አይነት ማሻሻያ አላደረገችም፡፡ “ዘመንን በአንድ ክብ ላይ አንድ ነጥቡን መነሻ አድርጐ ክቡን የመቁጠር ሂደት ነው” የሚሉት ደግሞ መጋቢ ሰለሞን አበበ ገብረመድህን ናቸው። ዘመን መቁጠር የጀመረው ክርስትናው አይደለም የሚሉት መጋቢ ሠለሞን ክርስትናው ከመጣ በኋላ ግን “ታላቁን ክስተት የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን መወለድ መነሻ አደረጉ” ብለዋል፡፡
“ይህም በአንድ ክብ ላይ የትኛው ነጥብ ላይ ሄጄ ነው መቁጠር የምጀምረው እንደ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ዞረው በሚገጥሙ በማያቋርጡ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች የምድርን ዙረት መሠረት አድርጐ ዘመናችን ስለሚለዋወጥ ነው የምንቆጥረው፡፡” ስለዚህ እንደ መጋቢ ሠለሞን በጁሊያን አቆጣጠር ለቆጠራ እንዲመቸውና እንዲሞላለት በዘፈቀደ ያስገባቸው ወደ 44 ደቂቃ እና 56 ሽርፍራፊ ሠኮንዶች ተጨምረዋል፡፡
“በኋላ ላይ ጐርጐሪዮስ ሲያርመው ከአመታት በኋላ ተጠራቅመው እነዚያ ደቂቃዎች አሥር ተጨማሪ ቀናት ወልደው ተገኙ፡፡ “ጐርጐሪዮስ እነዚህ አሥር ቀናት ከናካቴው ተጐርደው /ተቆርጠው/ ይውጡ የሚል አቋም ወሰደ” ሲሉ ያስረዳሉ መጋቢ ሠለሞን፡፡ እርማቱ ሲካሄድ ለጊዜው በአመት፣ በአሥር አመት የማይታሰቡ ቁርጥራጭ ደቂቃዎች ቀን በመውለዳቸው ልዩነቱ እንደተፈጠረ የሚናገሩት መጋቢ ሠለሞን “እኛ እንግዲህ የጁሊያን ሳይታረም የቀረውን ይዘን በመሄዳችን በወራቱ እና በቀናቱ ላይ አሥርም ስምንትም እንዲሁም በአመታቱ ላይ ልዩነቶችን እየፈጠረ መጣ፡፡
ስለዚህ የመጀመሪያው ልዩነት ሲታረም የታረመውን አለማካተታችን ነው፡፡ የክርስቶስ ልደት መፅሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ መሠረቶች እንደ መጋቢ ጥበብ በእምነት የአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር መሠረት ያደረገው በ735 ዓ.ም የተከሠተውን የሮም መቃጠልን ነው። “ከዚያ ተነስተው ነው የአዲስ ኪዳን ዓመተ ምህረታቸውን የቀመሩት።”
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ግን እንዲህ አይነት ክስተቶችን መሠረት እንዳላደረገች የሚናገሩት መጋቢ ጥበብ በእምነት ምክንያቱ ደግሞ እንዲህ አይነት ክስተቶች የአመት ልዩነት ሊፈጥሩ ስለሚችሉ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ልደተ ክርስቶስ መነሻ የምታደርገው መፅሐፍ ቅዱስን ነው። ይሄውም የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ አንድ ላይ ቅዱስ ገብርኤል በስድስተኛው ወር ወደ ድንግል ማሪያም ተላከ ይላል፡፡
ስድስት ወር ማለት ከዚያ በፊት አንድ ታሪክ አለ ማለት ነው፡፡ “በዚያው ምዕራፍ ላይ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ዘካሪያስ ሄዶ ዮሐንስ እንደሚፀነስ ብስራት ነግሮታል፡፡ የዮሐንስ ፅንሰት ከተከናወነ ከስድስተኛው ወር በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን ሄደ ማለት ነው፡፡ “ስለዚህ የጌታ ልደት መነሻ የሆነው የዮሐንስ ፅንሰት ወይም ልደት ነው፡፡ ዮሐንስ ደግሞ መቼ ነው የተፀነሰው የሚለውን ስናይ ዘካሪያስ በቤተመቅደስ ገብቶ ያጥን ነበር ይላል።
ይህ ሥርዐት ደግሞ በአመት አንዴ የሚፈፀም ነው፡፡” እንደ መጋቢ ጥበብ በእምነት ያንን ጊዜ ለማወቅ ደግሞ ብሉይ ኪዳን ላይ ዘካሪያስ ገብቶ ቤተ መቅደሱን ያጠነበት ቀን በሠባተኛው ወር ከቀኑም በአስረኛው ቀን ነው (ዘሌ 16፡ 29፣ ዘሌ 23፡27) የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም የአይሁዳውያን የዘመን አቆጣጠር የሚጀምረው ደግሞ ከመጋቢት ነው።
ከዚያ ተነስተን መስከረም ስንቆጥር ሠባተኛው ወር ላይ እንደርሳለን፡፡ ስለዚህ ካህኑ ለህዝቡ ስርየተ ሃጢያት የሚለምነው በመስከረም ወር ነው ማለት ነው፡፡ ይላሉ መጋቢ ጥበብ፡፡ “ስለዚህ በቤተክርስቲያናችን የብስራቱ ቀን መስከረም 27 ነው፡፡ ያንን ተከትሎ ደግሞ ከሦስት ቀናት በኋላ ለሚስቱ ሄዶ ነግሯት ዮሐንስ ተፀነሰ፡፡
ስለዚህ ከስድስት ወር በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ወደ እመቤታችን የሄደበትን ቀን ስንቆጥረው ታህሳስ 29 ላይ እንደርሳለን” ይላሉ፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት መቼ ነው በትክክል መከበር ያለበት? የሚለውን ለመመለስ ቤተክርስቲያን በይፋ በሚታወቅ መልኩ ልደቱን ማክበር የጀመረችው መቼ ነው? የሚለውን ማየት አስፈላጊ እንደሆነ ደግሞ መጋቢ ሠለሞን ይናገራሉ፡፡
ቅዱስ መፅሐፍ የጌታን ልደት እንጂ የተወለደበትን ቀን አይነግረንም የሚሉት መጋቢ ሠለሞን፣ በይፋ የተመዘገበ ታሪክ የምናገኘው በ4ኛው ምዕተ አመት ላይ ነው ይላሉ፡፡ አንዳንዶች በሦስተኛው ምዕተ አመትም የመከበሩ ምልክቶች አሉ የሚል ዘገባ ያቀርባሉ ይህ ከሆነ በዚህ የቀን ፍለጋው ውስጥ አሁንም ልዩነቶች ተፈጥረዋል፡፡
የተለያዩ ምሁራን የቀን ቆጠራ ለማካሄድ ባህረ ሃሳብም ሆነ ጐርጐሮሳያውያን ወደ ኋላ ሲሄዱ ስህተት መፈፀማቸውን የሚናገሩት መጋቢ ሠለሞን፤ ከዚያ ይልቅ ከኢየሱስ ልደት ጋር ያለውን ቀን መለየት መፅሐፍ ቅዱስን መመልከት ይሻላል። ይላሉ፡፡ ኢየሱስ በተወለደ ጊዜ የነበሩ ምልክቶች የታላቁ ቄሳር መኖር፣ የህዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ ማዘዙ፣ የኮከብ መታየት (ሥነ ከዋክብት ተመራማሪዎች ወደ ኋላ ሄደው እንዲመረምሩ ስለሚያስችላቸው)፣ በይሁዳ ላይ ሄሮድስ የሚባል ንጉሥ መኖሩ፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስ በሮም ላይ ገዢ ሆኖ መሾሙ፣ እነዚህ ታሪካዊ ክስተቶችን ከመፅሐፍ ቅዱስ ውጭ ካሉ ሠነዶች ጋር አያይዘን ካየን ሁለቱም የዘመን አቆጣጠሮች ወደ ኋላ ተሄዶ ሲመረመሩ ስህተት አለባቸው ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡ “በጐርጐሮሳውያኑ 7 አመት ወደ ኋላ፤ በእኛ ደግሞ 15 ዓመት ወደ ኋላ ተመልሶ ነው የታሪክ ሁነቶች የተከሰቱት የሚሉ ጥናቶች ወጥተዋል” ይላሉ መጋቢ ሠለሞን፡፡
እንደ መጋቢ ሠለሞን ከሆነ በኢትዮጵያ ወንጌላውያን ክርስቲያኖች ልደት፣ ሞትና ትንሣኤን አበይት በዓላት አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ ቀደምት ክርስትና ነበር። ቀዳሚውም ክርስትና ወደ 2ሺህ አመት ኖሯል። ይህ ሀገር የክርስትና ውርስና ቅርስ አለው” ይላሉ።“ ምንም እንኳን ወንጌል አማኞች በአንዳንድ አስተምህሮዎችና ትውፊታቸው ቀዳሚት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቢለዩም ነገር ግን የጌታን ልደት በማክበሩ ላይ ያንኑ የቀዳሚውን ይዞ መሄዱን መርጠዋል፡፡” ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የትኛውንም ለመምረጥ ምንም የተለየ መፅሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለም የሚል ነው፡፡ “ይልቁንም ትውፊትን ነው የመረጥነው ማለት ነው” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በሄደችበት ሀገር ያለውን ባህልና አካሄድ በመከተል የእምነት ስብከቷን እንደምታካሂድ የሚናገሩት መጋቢ ጥበብ በእምነት፣ በዚህ የተነሳም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊ ቤተክርስቲያን የተየለ የቀን አቆጣጠር አትከተልም ብለዋል፡፡ እንኳን ለጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል /ገና/ በሠላም አደረሳችሁ፡፡
More Stories
የልጅነት ገናን በትዝታ፣ የአሁኑን በትዝብት
ልደት እና ባለ ልደት
ከአመት በዓል ዜማዎች