ከአመት በዓል ዜማዎች

ከአመት በዓል ዜማዎች

በአንዱዓለም ሰለሞን

አመት በዓል የደስታ ጊዜን የምናሳልፍበት ነው፡፡ ሁሉም እንደ አቅሙ ሽር ጉድ ብሎ ቤቱን የሚያደምቅበት፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ተጠራርቶ፣ በጋራ ማዕድ የሚቋደስበት፣ መልካም ምኞት የሚመኝበት፣ የተራራቀ የሚገናኝበት፣ የተጣላ ካለም የሚታረቅበት ነው – አውደ ዓመት፡፡ የእዚያ ዕለት ታዲያ የቤቱ ሁኔታም ይቀየራል፡፡ የምግቡ መዓዛ፣ የመጠጡ፣ የቡናው፣ የእጣኑና የቄጤማው ነገር ለቤቱ የተለየ ድምቀት፣ ለውስጥ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው፡፡ የአመት በዓል ዜማዎች ደግሞ የዚህ ደስታ ማድመቂያ ይሆናሉ፡፡ የአመት በዓል ዘፈኖችን ስናነሳ፣ ቀድመው ወደ አእምሯችን የሚመጡ ሙዚቃዎች ስለመኖራቸው እሙን ነው፤ በዓሉን ከወዳጅ ዘመድ ጋር በመሆን በደስታ እያሳለፍን የሰማናቸው በመሆኑ ትዝታቸው ውስጣችን የመቅረቱ እድል ከፍ ያለ ነውና፡፡ እኔም ታዲያ፣ መጪው አውደ ዓመት እንደ መሆኑ፣ የድምጻዊ አብዱ ኪያርን አንድ የአመት በዓል ሙዚቃ በማስታወስ ጥቂት ማለት ወደድኩ፡፡ “ጥቁር አንበሳ” በሚለው አልበሙ፥ “መልካም አመት በዓል” የሚል ርዕስ የተሰጠው ይህ ሙዚቃ፣ አዝማቹ በምርቃት ይጀምራል፡፡ እንዲህ በማለት፡ “ተሰብስበን እንዳማረብን በአውድ ዓመቱ ፍቅር ያዝንብብን ቤት ለሌሉት ለራቁት በአካል በያሉበት መልካም አመት በዓል” አውደዓመት ተሰብስበው ማእድ የሚቋደሱበት እንደ መሆኑ፣ እንደ ባህሉና ወግ ስርዓቱ መመራረቅም ይኖራል፡፡

በአብዱ ኪያር ሙዚቃ ላይ የምናየውም ታዲያ ይህንኑ ነው፡፡ ምርቃቱ ደግሞ “ቤት ለሌሉት..” በማለት እንጀራ ፍለጋ ብለው ከሀገራቸው የራቁና በተለያዩ አካባቢዎች በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን ጭምር ያካትታል፡፡ እዚህ ላይ፣ በተለይም በአልን ከቤተሰብ ርቆ ማሳለፍ የሚፈጥረውን ስሜት ለሚያውቅ ሰው፣ ስሜቱ የበለጠ ይገባዋል፡፡

ዩትዩብ ላይ በተለቀቀው በዚህ ሙዚቃ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ ሰዎች መካከል ይህን ስሜት ያንጸባረቁቱ ጥቂት የሚሰኙ አይደሉም፡ “ውዴ ኢትዮጵያ ለመግባት 9 ቀን ብቻ ቀረኝ፡፡ በሰላም ግቢ በሉኝ፡፡ የስደት ጓደኞቼ፣ እናንተንም በሰላም ወደ ሀገራችሁ ይመልሳችሁ፡፡” “ይህን ዘፈን ስሰማ ሀገሬ፣ የእናቴ ቤት ይናፍቀኛል፤ ስደት ዐይኑ ይጥፋ!” ምርቃቱ ሲቀጥል ለእናትና አባት ብሎም ለወንድምና እህት መልካም ምኞት የሚገለጽበት ሆኖ እናገኘዋለን፡ “አንቺ የኢትዮጵያ እናት ይለፍልሽ፣ ከአመት እስከ አመት ይሙላ ጓዳሽ፡፡ አንተ የኢትዮጵያ አባት እሺ ይበልህ፣ ከሰው እንዳታይ እንዳይጎልህ፡፡” ማጀት ከጎደለ እና አጥቶ ነጥቶ የሰው እጅ እያዩ በዓል አይደምቅም፡፡ በከፋ እጦት ውስጥ በዓልን ይቅርና፣ ኑሮን ማሰብም ያደክማል፡፡

ይህን ስናስብ ነው እንግዲህ የምርቃቱ ክብደት የሚገባን፡፡ … “ጀግናዋ እህቴ የእናቷ ልጅ፣ ከብረሽ ቆይልን ውለጅ ክበጂ፤ ወንድሜ አንበሳው ያባቱ ልጅ፣ ክፉ አያሳይህ ደጋጉን እንጂ፡፡” “ሀገር የሚገነባው ቤተሰብ ውስጥ ነው” እንዲሉ፣ እንግዲህ ምርቃቱ ለሀገር፣ ለወዳጅ ዘመድ፣ ለመላው ኢትዮጵያዊያን ነው ብለን እያሰብን እንቀጥል፡፡

በእርግጥ ቀጣዮቹ የሙዚቃው ስንኞች የሚያስረግጡልንም ይህንኑ እውነታ ነው፡ “ከሀገር ርቀው ለተሰደዱት፣ በህመም በስቃይ ካልጋ ለዋሉት፣ በህግ ተይዘው እስር ቤት ላሉት፣ ያድርግላቸው እንደሚመኙት፡፡” ቀጣዮቹ የሙዚቃው ስንኞች የሚያወሱት ደግሞ የኢትዮጵያዊያንን ሀገር ወዳድነት ነው፡፡

ይህን ከወዳጅ ናፍቆት ጋር ተሳስሮ የሚገለጸውን ጽኑ የሀገር ፍቅር ስሜት የሚገልጡልን ቀጣዮቹ ስንኞች ሀሳብ ጥልቀትም የትየለሌ የሚሰኝ ነው፡ “ካለም ሚለየን ከማንም ዜጋ፣ የሚያሳምመን ልክ እንደ አለንጋ፣ ልብ ውስጥ ታትሞ የማይዘነጋ፣ ያገር ፍቅር ነው የነፍሶች ዋጋ፡፡”

የኢትዮጵያዊያን የሀገር ፍቅር ስሜት ለነጻነት ከተከፈለ ታላቅ መስዋዕትነት የመነጨ መሆኑን ከሚነግሩን ከእነዚህ የስንኝ ቋጠሮዎች መለስ ስንል ደግሞ፣ ቀጣዮቹንና የኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያዊያንን እንግዳ ተቀባይነት የሚያወሱ የግጥም ስንኞችን እናገኛለን፡ “ከእየሩሳሌም ደግሞም ከመካ፣ እኛን አክብሮ ከሩቅ ጃማይካ፣ ኢትዮጵያን ብሎ በእኛ ሲመካ፣ ተቀብለናል ትመስክር አፍሪካ፡፡” ሙዚቃው ሲቀጥል፣ ይህ የእንግዳ ተቀባይነት ባህላችን፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ካለው ጠንካራ መስተጋብር፣ የመተሳሰብና በጋራ የመኖር ጥበብ ውስጥ የሚመነጭ መሆኑን የሚያጠያይቁ ስንኞች ይከተላሉ፡፡ እነዚህ ስንኞችም በልዩነቶቻችን ውስጥ ደምቆ የሚታየው አብሮነታችን መገለጫ ስለመሆናቸው የተነገረባቸው ናቸው፡- “የወንጌሉ ሰው ላገሬ እስላሙ፣ ወገኑ አይደል ወይ ደራሽ ወንድሙ፤ የቁርአኑ ሰው ለክርስቲያኑ፣ ወንድሙ አይደል ወይ ደራሽ ወገኑ፡፡” እዚህ ላይ፣ ዓለም በአድናቆት “አጃኢብ” የሚሰኝበት፣ የኢትዮጵያዊያን በፍቅር ላይ የተመሰረተ አንዱ የሌላኛውን ሀይማኖት የማክበር ነገር በአጽንኦት የተገለጸበት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ቀጣዮቹ የሙዚቃው ስንኞች ደግሞ የዚህን እውነታ ጥግ ያስገነዝቡናል፡ “ረመዳን ስጾም በርታ የሚል ጓዴ፣ አይዞህ የምለው ሲሆን ኩዳዴ፤ የእኔና የእሱን ታላቁን ፍቅር፣ ኢትዮጵያን ያየ መጥቶ ይመስክር፡፡” በመጨረሻም በምርቃት የጀመረው ሙዚቃ፣ በምርቃት ያበቃል፤ ከአንድ ምድር የበቀልን፣ “የአንድ አፈር አፈሮች” እንደመሆናችን፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ተቻችለን እንድንኖር እያሳሰበ፡- “የፍቅር ጊዜ ያድርግልን፣ እያፋቀረ ቸር ያቆየን፣ እያቻቻለ ፍቅር ይስጠን፡፡” እኔም የሳምንት ሰው ይበለን በማለት፣ ስንብቴን በዚሁ ምርቃት ማድረግን ወደድኩ፡፡ ቸር ይግጠመን፤ ሰላም!