ልደት እና ባለ ልደት
በይበልጣል ጫኔ
እነሆ ገና። እኛም ላቱ የሚወዛወዝ በግ በገዛንበት ዘመን ፈንታ÷ ላታችንን እያወዛወዝን በትዝታ ቆዘምን። ለጨዋታው ድምቀት እንጂ “ላታችንን” ያልኩት÷ ላቱ እንኳን የኛ ሳይሆን የትዝታችን ነው። “ትዝታ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ላት አበቀለ?” የሚል አንባቢ ቢኖር÷ ትዝታ እና ጅራት አበቃቀላቸው ከኋሊት÷ ብዬ እመልሳለሁ። የሆነው ሆነና÷ ላቱን የሚያወዛውዝ ትዝታዬን የቀሰቀሰብኝ ቴሌቪዥኔ ነው።
የገና በዓል መድረሱን ምክንያት በማድረግ ቴሌቪዥኔ በበግ እና በዶሮ ተጥለቅልቋል። አንድ ማስታወቂያ ላይ ወፍራም በግ በገመድ የሚጎትት ወፍራም ልጅ ይታያል።
ከሀገር ውጪ የሚኖር አጎቱ በላከው ብር የተገዛ ነው በጉ። እኔ በግ የሚጎትተውን ልጅ እያየሁ ወደ ልጅነቴ ኮበለልኩ። ልጅ ሆኜ እንዲህ በዓል ሲደርስ አባቴ በግ ይገዛል። የኔ ብቻ ሳይሆን የጓደኞቼ አባቶችም በግ ይገዛሉ። የዚያኔ እንደዛሬው በግ መግዛት የሀብት መለኪያ አልነበረም።
እኛ ልጆችም በጎቹን እየጎተትን ወደ ሜዳ እንወጣለን። ሳር እናብላቸው ብለን ነው ከቤት የምንወጣው። ኋላ ላይ ሳር ማብላቱ ይቀርና÷ በጎቹን መጋለብ እንጀምራለን። መጋለብን ለፈረስ እና ለበቅሎ ብቻ ያደረገው ማነው?÷ እናላችሁ በግ እየጋለብን ስንዝናና÷ አንድ ቀን እንዲህ ሆነ። ግልቢያው በየተራ ነበርና÷ አንድ የዕድሜ ተጋሪያችን በተራው በጉን ይዞ ቀረበ።
ከአህያ ጥቂት መለስ ያለ ነበር በጉ። ወጥቶ ጀርባው ላይ እንደተፈናጠጠ÷ በጉ ፈረጠጠ። ማናችንም እንዲህ ይሆናል ብለን አልገመትንም። የበጉን ሁኔታ ላስተዋለ÷ ቅንጣት ነገር ጀርባው ላይ የተሸከመ አይመስልም። ጓደኛችን በጉ ጀርባ ላይ ያለው ፀጉር እስኪነቃቀል ድረስ በእጆቹ ጨምድዶ ይዞ፦ “አድኑኝ፣ አድኑኝ፣ ድረሱልኝ …” እያለ÷ ከዓይናችን ራቀ። እኛ “አድኑኝ” እያለ በበግ ጀርባ ላይ ተሳፍሮ ከዓይናችን የራቀው ልጅ ጓደኞች÷ ልናድነው አልቻልንም። ድረሱልኝ እያለ ቢማፀንም አልደረስንለትም። ልንከተለው÷ ባንደርስበትም አብረነው ልንሮጥ ብንፈልግም አልቻልንም። በጎቻችን ቢጠፉብንስ ብለን ሰጋን። ጥቂት ዘግይተን በጎቻችንን እየጎተትን በሄደበት መንገድ ስንሄድ÷ መሬት ላይ ተኝቶ አገኘነው። ስንጠራው አይሰማም። ዞር ዞር ስንል በጉ በአካባቢው የለም። ደነገጥን። ያስደነገጠን የጓደኛችን ስንጠራው አለመስማት ይሁን÷ የበጉ አለመኖር ትዝ አይለኝም። ጓደኛችንን በተኛበት ትተን÷ በጎቻችንን እየጎተትን ወደ ቤታችን ተመለስን። የሆነውን ነገር ለአባቱ ስንነግራቸው÷ ቀነኒሳ በቀለን በሚያስንቅ ፍጥነት ሮጠው ልጃቸው ጋ ደረሱ። እሳቸውም ሲጠሩት አልሰማ አላቸው። ከጎረቤት ግቢ አምጥተው አንድ ባልዲ ውኃ ሲከለብሱበት÷ ከእንቅልፉ እንደሚነቃ ሰው አይኖቹን ገለጠ።
እኛ ጓደኛችን የተኛበትን ቦታ ከበብን የቆምን ውሪዎች÷ ዓይኖቹን ሲገልጥ ሪጎሬ ያገባ ያህል አጨበጨብንለት። ግን ምን ዋጋ አለው?÷ ከተጋደመበት መሬት ሳይነሳ አባትየው “በጉስ?” ሲሉት መልሶ አይኖቹን ጨፈነ። እሱን እንደምንም ቀስቅሰው ወደ ቤት አስገቡት። በጉ የተገኘው ግን የገና በዓል ካለፈ በኋላ ነበር። ወደ ልጅነቴ ካሰጠመኝ የትዝታ ባህር ያወጣኝ የልጄ ጥያቄ ነበር። ወፍራም በግ የሚጎትተውን ወፍራም ልጅ እያየ፦ “አባዬ አንተስ በግ አትገዛም እንዴ?” ሲለኝ÷ በተቀመጥኩበት ቦታ ድርቅ ብዬ ቀረሁ።
ጥቂት አሰብ አድርጌ ወደ ልጄ ዞር ስል÷ መልሴን እየተጠባበቀ ነበር። ኮስተር ብዬ “በግ የዱር እንስሳ ነው። የዱር እንስሳ ደግሞ አይበላም” ልለው አስቤ ነበር። የዘንድሮ ልጅ ግን እንዲህ በዋዛ የሚሸውዱት ዓይነት አይደለም። ካ’ፍታ ቆይታ በኋላ አሪፍ ሃሳብ መጣልኝ፦ “እኔም እኮ በግ የመግዛት ሃሳብ ነበረኝ። ነገር ግን በጉ የሚያድርበት ቦታ የለንም። …” ብዬ ንግግሬን ልቀጥል ስል÷ አቋረጠኝና፦ “ችግር የለም እነ ቡቡ ጋ እናሳድራለን። ከነሱ በግ ጋር ያድራል” አለኝ በጉጉት። እኔም ኮስተር ብዬ፦ “እዚህ ለማሳደርም ለማረድም አይመቸንም።
ስለዚህ የበዓሉ ቀን እዚያው ገዝቼ አሳርጄ አመጣለሁ” አልኩት። ባይዋጥለትም ተስማማ። እኔም እፎይ አልኩ። የበዓሉ ዕለት የበሬ ስጋ በኪሎ መግዛቴ ስለማይቀር÷ በጉ ነው እለዋለሁ ብዬ። ጥቂት እንደቆየን ቴሌቪዥኔ “ለ2017 ዓ.ም የገና በዓል እንኳን አደረሳችሁ …” እያለ ማስታወቂያውን ማዥጎድጎድ ቀጠለ። በገዛ ቴሌቪዥኔ 15 ደቂቃ የማይሞላ ፕሮግራም ላይ 15 ማስታወቂያ መልቀቃቸው አናዶኝ÷ ወዲህም አንዱን ሸቀጥ እንኳን መሸመት ላልችል፣ ከነልጄ በጉምዥት ካራ ከምተፈተፍ÷ ሪሞቴን አንስቼ ወደ ሌላ ጣቢያ ቀየርኩ። እዚህም ሌላ ማስታወቂያ። በመሃል ልጄ ሌላ ጥያቄ አነሳ፦ “አባዬ የገና በዓል ግን ለምን ይከበራል?” “የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ስለሆነ” መለስኩለት።
አንዳንድ ጊዜ ጥያቄው ምንም እንኳን ቀላል ቢመስል÷ ባልመልስለት እመርጣለሁ። ከመልሶቼ ጥያቄ እየመዘዘ ማረፊያ ያሳጣኛል። ወይም ደግሞ አስቤው ከማላውቀው ጉዳይ ጋር ወስዶ ያላትመኛል። ከአንዳንድ ጥያቄዎቹማ ቀንዱ የተጠማዘዘ፣ ላቱ የሚገላበጥ በግ መግዛት ይቀላል።
ቀጠለ፦ “ኢየሱስ ግን የት ነው ያለው?” “እላይ በሰማይ” “እሱ ሰማይ ላይ ከሆነ÷ እኛ ለምንድነው እዚህ ልደቱን የምናከብረው?÷ ባለ ልደቱ በሌለበት ቦታ ልደት ይከበራል እንዴ?” ይኼኛው ጥያቄው አስገርሞኛል። ማስገረም ብቻ ሳይሆን ሌላ ቁምነገር ማሰብ እንድችል አድርጎኛል። በእርግጥ ልደት ሲባል እሱ የሚያውቀው÷ ባለ ልደቱን ከብበው “ልደትህ ዛሬ ነው÷ ወፏ ነግራኛለች” እያሉ÷ ኬክ እና ቸኮሌት የሚበሉበትን በዓል ነው። እዚህ በዓል ላይ አጃቢዎቹ የሚታደሙት ባለልደቱ ያለበት ቤት ነው። ለኢየሱስ የልደት በዓልም ቢሆን ትክክለኛው አካሄድ ይኼ ነው።
አንዳንድ ጊዜ ኃይማኖታዊ እውነቶቻችን በልማድ ሲዋጡ አያለሁ። ልማዶቻችን ሲደጋገሙ ደግሞ ትክክለኛ አካሄድ መምሰላቸው አይቀሬ ነው።
“ነገር በምሳሌ …” እንዲሉ የገና በዓል ሲደርስ÷ ሰዉ ከዶሮ እስከ በሬ አቅሙ የፈቀደውን ያዘጋጃል። የሚጠጣውንም እንዲሁ÷ በዓይነት በዓይነቱ ይደረድራል። የበዓሉ ዕለትም እየተጠራሩ መብላት መጠጣት ነው። “እየተጠራሩ” ሲባልም ብድር መመለስ የማይችሉትን አያካትትም።
በአጭሩ ምሳ የሚጋበዙት እራት መጋበዝ የሚችሉት ናቸው። በዚህ ሁኔታ ከጠዋት አንስቶ እስከማታ ድረስ የሆድ ተዝካር ሲደገስ÷ ባለ ልደቱ የተባለው ኢየሱስ ክርስቶስ ስፍራው የት እንደሆነ ማንም አያውቅም። ማንም አይጠይቅም። ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ስጋ ለብሶ እንዲገለጥ ያስፈለገበት ምክንያት ለአብዛኛው ሰው ምኑም አይደለም። ደግሞ ከዚህ የሚብስ አለ። ገናን ጨምሮ ሌሎች መንፈሳዊ እና ኃይማኖታዊ በዓላት በሚከበሩበት ዋዜማ ላይ፦ “ታላቅ የሙዚቃ ኮንሰርት ምናምን …” እያሉ ነጋሪት የሚጎስሙ ይበዛሉ። የቻሉ እና የተሳካላቸው ዘፋኞቹ እና አስጨፋሪዎቹ ያሉበት ቦታ ሄደው ሰውነታቸው እስኪላቀቅ ሲጨፍሩ ያድራሉ። ያልቻሉም ደግሞ በቅርባቸው ካለ የምሽት መዝናኛ ክበብ የሚያስቀራቸው ኃይል የለም።
ሰበብ የሚያደርጉት ደግሞ የበዓል ዋዜማ መሆኑን ነው። ይኼኔ ይኼንን ሁሉ እንድል መነሻ የሆነኝን የልጄን ጥያቄ መጠየቅ ያምረኛል፦ “ባለ ልደቱ የሌለበት ቦታ÷ ልደት ይከበራል ወይ?” መቼም እንደ ልጄ÷ ባለ ልደቱ ያለው በሰማይ ስለሆነ የት እናገኘዋለን እንደማትሉ ተስፋ አለኝ። ካላችሁም ደግሞ÷ በዋዜማው በአቅራቢያችሁ ወዳሉ አብያተ ክርስቲያናት ሂዱና “ቅዱስ ቅዱስ …” ስትሉት እደሩ። ባለ ልደቱን እዚያ ታገኙታላችሁ። ከዚያ ውጪ ያለው ግን ከንቱ ድካም ነው።
More Stories
የልጅነት ገናን በትዝታ፣ የአሁኑን በትዝብት
በኢትዮጵያ ገና ለምን ታህሳስ 29 ይከበራል?
ከአመት በዓል ዜማዎች