“ያየው ሁሉ የሚያምረው መለወጥ አይችልም” – ወይዘሮ ፀሐይ አምባቸው

“ያየው ሁሉ የሚያምረው መለወጥ አይችልም” – ወይዘሮ ፀሐይ አምባቸው

በአለምሸት ግርማ

ከጥቂት የንግድ ስራ ተነስተው ትልቅ ሀብት በማፍራት ተምሳሌትነት ደረጃ የደረሱ ሰዎች ብዙ ናቸው። እንዲሁም ለሌሎች የስራ እድል ከመፍጠር አልፈው በትጋታቸው ለሌሎች አርዓያ የሆኑ፤ ባገኙት አጋጣሚ ለሌሎች በቀናነት የስራ አቅጣጫ የሚያሳዩ ሰዎችም በርካቶች ናቸው። የዛሬዋ እቱ መለኛችን ወደ ስራ ለመሰማራት ባቀደችበት ወቅት አቅጣጫ የጠቆሟት፤ እና አሁን ላይ የምትወደው ሙያ ባለቤት ያደረጓት እንደነዚህ ያሉ መልካም ሰዎች ናቸው።

በንግድ ስራ ውስጥም ይሁን በሌላ ሙያ የተሰማሩ ሰዎች የራሳቸው ጥንካሬ እና ድክመቶች ሊኖራቸው ይችላል። ውጤታማ ለመሆን የራስን ጥንካሬ መለየት እና በእሱ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል:: የተሰማሩበትን ሙያ በመውደድ፤ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በፅናትና በትዕግስት ለማለፍ አስቀድሞ መዘጋጀት እና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው። ጥንካሬያቸውን ለማስቀጠል የተሰማሩበትን ሙያ አክብረውና ከሰዎች ጋር ተግባብተው የሚሰሩ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህም መካከል የዛሬዋ እቱ መለኛችን ትጠቀሳለች፡-

የወንዶችን ፀጉር ማስተካከል ሙያ ሴቶች በብዛት ከማይሳተፉባቸው ሙያዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። ይሁን እንጂ የስራውን አዋጭነት የተረዱት እነዚያ ሰዎች ግን ወደዚህ ሙያ እንድትገባ ምክራቸውን ሰጥተዋታል። ቀድሞም ለሙያው ፍላጎት ስለነበራት የወዳጆቿን ምክር በመቀበል በጀመረችው ስራ እስከአሁን ዘልቃለች።

ወ/ሮ ፀሐይ አምባው ትባላለች። ሙያዋ የወንዶች ፀጉር ማስተካከል ነው። የተወለደችውና ያደገችው ሻሸመኔ ከተማ ነው። ትምህርቷንም እዚያው ሻሸመኔ የአብዮት ፍሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና ሻሸመኔ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተከታትላለች። ከልጅነቷ ጀምሮ የግል ስራ የመስራት ፍላጎት ነበራት። በዚህም መሰረት የራሷን ስራ ለመስራት ይረዱኛል ያለቻቸውን የተለያዩ ሰዎችን ማማከር ጀመረች።

ባገኘችው ሃሳብ መሰረት በ2001 ዓ.ም ሃዋሳ ከተማ በመምጣት በቤተሰብ ድጋፍ አነስተኛ የወንዶች ፀጉር ቤት ከፈተች።

በወቅቱ ፍላጎቱ እንጂ ሙያው እንዳልነበራት አጫውታናለች። የሙያው ክፍተት ለስራዋ መሰናክል እንዳይሆንባት በማሰብ ስልጠና የወሰደ ባለሙያ ቀጠረች። ይህን ያደረገችው አንድም ስራውን እንዲሰራላት፤ ሌላው ደግሞ ሙያውን ለመቅሰም እንዲረዳት በማሰብ ነበር። በሃሳቧ መሰረት የቀጠረችው ባለሙያ ስራውን ሲሰራ እሷ ደግሞ ሙያውን ትቀስም ነበር። በልምድ የቀሰመችው ስራ አድጎ ቀስ በቀስ ጎበዝ አስተካካይ ለመሆን በቃች፡-

“የፀጉር ስራ ሙያ ከሰው የሚያግባባ ስለሆነ በስራዬ ደስተኛ ነኝ። ደግሞም ስራውን ፈልጌውና ወድጄው ነው የምሰራው። በፍላጎት የተሰማሩበት ሙያ ውጤታማ ያደርጋል። የሰው ልጅ ወደ ስራ ሲሰማራ የሚያስፈልገው ነገር ፍላጎት ነው”

በ2011 ዓ.ም ትዳር የመሠረተች ሲሆን የአንድ ልጅ እናትም ሆናለች። ከምትሰራው ስራ በምታገኘው ገቢ ቤቷን እያስተዳደረች ሲሆን፤ ለልጇም አስፈላጊውን እንክብካቤ እያደረገች በማሳደግ ላይ ትገኛለች። ይህን ማድረግ በመቻሏ ደስተኛ ናት።

አንዲት ሴት የራሷ ገቢ ከሌላት ለሁሉም ነገር የትዳር አጋሯን እጅ ለመጠበቅ ትገደዳለች። የራሷን የገቢ ምንጭ የፈጠረች ሴት ግን በመስራቷ ከተለያዩ ጫናዎች ራሷን ትጠብቃለች። ይህን የተረዳችው ወይዘሮ ፀሐይ “በመስራቴ የራሴንም፣ የቤተሰቤንም ፍላጎት እያሟላሁ ነው። ይህም ትልቁ ትርፌ ነው” ትላለች።

በስራ ህይወት ውስጥ ለሰው ልጅ ጥረት አስፈላጊ ነገር ነው። ስራ የራስ ጥረት ካልታከለበት ውጤታማ መሆን አይቻልም። ሁሉም ስራ በአንድ ጊዜ ስኬታማ ላያደርግ የሚችልበት አጋጣሚ አለ። ስለዚህ ስራን በትዕግስትና በጥረት መስራት ያስፈልጋል ስትልም ትናገራለች።

በቀጣይ ያላትን እቅድ ስትናገር፦

“ስራዬን ስለምወደው ሙያዬን መቀየር አልፈልግም። እግዚአብሔር ቢረዳኝ አሁን የምሰራውን ስራዬን የማስፋፋት ዕቅድ አለኝ። የተሻለ እና የተደራጀ አድርጌ ለማስቀጠል አቅጃለሁ። የተለያዩ ግብዓቶችን በማሟላት ለሌሎች ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠርም የዕቅዴ አካል ነው” ትላለች፡፡

“በሙያ ውስጥ ደንበኞችን ለመያዝ ትእግስት ያስፈልጋል። በንበኞቻችንን በፀባይ ከተያዙ ደንበኝነታቸውን ያጠናክራሉ። በተለይም በዚህ ሙያ ውስጥ የሰውን ፍላጎት ማወቅ፣ ጥሩ ተግባቦትና አክብሮት አስፈላጊ ነው። እና ከቆይታ የተነሳ የስራውን ባህሪ አውቄዋለሁ። ደንበኞቼንም ሆነ አዳዲስ ተገልጋዮች ሲመጡ እንዴት ማስተናገድ እንዳለብኝ አውቃለሁ። ለዚያም ብዙ ደንበኞች አሉኝ” ስትል ነበር ስለሙያዋ ያጫወተችን።

ስለገንዘብ አጠቃቀም ስትናገር፦ “በተለይም በንግድ ስራ ውስጥ ያሉ ሰዎች ገንዘባቸውን በአግባቡ ካልያዙ መሻሻል አይችሉም። ዕድገትን የሚፈልግ ሰው ገንዘቡን በአግባቡ መያዝና በዕቅድ መመራት አለበት። ገንዘቡን በአግባቡ መያዝ የማይችልና ያየው ሁሉ የሚያምረው ሰው መለወጥ አይችልም። ከምንም በላይ ደግሞ ጊዜ ሀብት ነውና በአግባቡ ልንጠቀመው ይገባልም” ትላለች።

“ሴቶች ስራን ለመጀመር ሲያስቡ የወንድ እና የሴት ስራ ብለው ይመርጣሉ። ይሁን እንጂ ፍላጎቱ ካለ መስራት ይቻላል። በልምድ ያገኘሁት ሙያዬ ዘላቂ መተዳደሪያ ሆኖ ለዚህ አድርሶኛል። የማንንም እርዳታ ሳልጠይቅ ቤተሰቦቼን አስተዳድራለሁ። ስለዚህ ሴቶች ስራ ሳይመርጡ ወደ ስራ ሊገቡ ይገባል። ለዚህ ደግሞ አስፈላጊው ነገር ፍላጎትና እችላለሁ ብሎ ማመን ነው።

“ሴቶች ዓላማቸውን ማሳካት የሚችሉት የራሳቸው ገቢ ሲኖራቸው ነው። ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ፤ ሰውን ለመርዳት እንዲሁም የሚፈልጉትን ለማድረግ የራስ ገቢ ያስፈልጋል። ከትዳር አጋራቸው እየጠበቁ የሚፈልጉትን ሁሉ ማድረግ ወይም ቤተሰቦቻቸውን በፈለጉት መጠን መርዳት አይችሉም። ስለዚህ የወንድ ወይም የሴት ስራ ነው ብለው ስራን ሳይንቁ ሊሰሩ ይገባል። ስራ በራስ መተማመንን ይፈጥራል። በተለይም ለሴት ልጅ ስራ ብዙ ጠቀሜታ አለው።” ትላለቸ፡፡

ከዚህ ቀደም በጎዳና ይኖሩ ለነበሩ ሙያ የሚያገኙበትን ዕድል አመቻችታ ወደ ስራ የገቡ ጥቂት ሴቶች መኖራቸውን አጫውታናለች። ለዚህም ቀበሌዎች ድጋፍ እንዳደረጉላት ተናግራ፤ በቀጣይም ቢሳካላትና ድጋፍ ብታገኝ በጎዳና ያሉ ወጣት ሴቶች ሙያ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ትፈልጋለች።

ከወ/ሮ ፀሐይ ተሞክሮ ጥንካሬን፣ ትዕግስትን፣ ስራ ወዳድነትን መማር የሚቻል ሲሆን በተለይም ወደ ግል ስራ ለሚሰማሩ ሴቶች ብዙ ጊዜ ምክሯን እንደምትለግስ አጫውታናለች። ተግባቢና በስራዋ ታታሪ መሆኗን በቅርበት የሚያውቋት ሰዎች ይናገራሉ። ከራሷ አልፋ ለሌሎች ለመትረፍ የምታደርገው ጥረት ለሌሎች መማሪያ የሚሆን ተግባር ነው።

የግል ስራ በፍላጎት በተለይም በሚወዱት ሙያ ሲሆን ውጤታማነቱ ከፍ ይላል። ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር ምቹ የማይሆንበት አጋጣሚም ሊኖር ይችላል።

በዕረፍት ቀናት፣ በበዓላትና ሁነቶች በሚኖሩበት ጊዜ ስራው ደመቅ የሚል ሲሆን እንደፀሐይ ደንበኞችን የመያዝ አቅም ያላቸው ደግሞ የገበያ ሁኔታ አያሳስባቸውም። ተባብሮ በመስራት የምታምነው እቱ መለኛችን በአሁኑ ወቅት እንደ እሷ ካለች ባለሙያ ጋር አብራ በመስራት ላይ ትገኛለች። ይህም የሚመጡ ደንበኞችን በፍጥነት ለማስተናገድ ከማስቻሉም በላይ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻልም በማመኗ እንደሆነ ትናገራለች።

የራሷ የገቢ ምንጭ ያላት ሴት ኢኮኖሚያዊ ጫና አያርፍባትም። የራሷንና የቤተሰቦቿን ፍላጎት ለማሟላት አትቸገርም። በዚህም ለቤተሰቦቿም ሆነ በቅርበት ለሚመለከቷት ምሳሌ ትሆናለች።