“በዓመት 3ሺ 20 ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ ነው”
በአለምሸት ግርማ
ሀገራችን በእንስሳት ሀብት የበለፀገች እንደሆነች የዘርፉ ባለሙዎች ይናገራሉ። ምቹና ተስማሚ የአየር ጠባይ ያላት፥ እንዲሁም በእንስሳት ሀብት ባለፀጋ ብትሆንም ከተለያዩ ማነቆዎች የተነሳ ከዘርፉ በቂ የሆነ ጥቅም ሳታገኝበት ዘመናት ተቆጥረዋል። የእንስሳት ሀብት ለወጪ ንግድ ገቢም ምንጭ ከሆኑት የሚመደብ ቢሆንም፣ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም እንዳልተገኘበት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ጥራት ያለው ምርት በማምረት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የራሱ መስፈርት ያለው ሲሆን እነዚህን መስፈርቶች ለማሟላት እንደ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችንም ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከነዚህም መካከል ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን በሚያሟላ መልኩ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦን ሳያቋርጡ በጥራትና በብዛት ማምረት አለመቻል፤ የቴክኖሎጂ ውስንነት፣ ድርቅና የእንስሳት በሽታ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። ድርቅ በመጣ ጊዜ የመጀመሪያ ተጠቂዎች እንስሳት ሲሆኑ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመኖ ዋጋ በየጊዜው መናር፣ በአገሪቱ ያሉት የመድኃኒት ፋብሪካዎች ውስን በመሆናቸው ምክንያት አብዛኛው መድኃኒት ከውጭ መምጣቱና በዋጋ መወደዱ ሌላው የዘርፉ ችግር እንደሆነም ይጠቀሳል፡፡ የቁም እንስሳት የኮንትሮባንድ ንግድ መጧጧፍም አገሪቱን የውጭ ገቢ በማሳጣት ዘወትር የሚጠቀስ ነው፡፡
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የመስኩ ባለሙያዎች በየዘመናቱ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በእንስሳት አመጋገብና የጤና አጠባበቅ፣ በአርብቶ አደሩ አኗኗር፣ እሴት ሰንሰለት፣በመሬት አጠቃቀምና ሌሎች ተግባራት ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ለእዚህ ተጠቃሽ ነው። በተጨማሪም የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው። የእንስሳት ሀብት ልማትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አከናውነው ውጤታማ ከሆኑ ክልሎች መካከል አንዱ ሲዳማ ክልል ነው።
የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ዳይሬክቶሬት ክፍል የንብና ሀር ልማት ባለሙያና የዳይሬክተሩ ተወካይ አቶ ታደሰ ሌዳሞ በሰጡን መረጃ፥ በክልሉ የእንስሳት ሀብትን ለማልማት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። በተለይም የእንስሳት ዝርያዎችን በማሻሻል፤ በንብ ማነብ ስራ፣ በዓሳ ግብርና ልማት፣ በዶሮ እርባታ እና በመሳሰሉት በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ተገኝቶባቸዋል። በዋናነትም የእንስሳት መኖ ማምረትና ማከፋፈል፣ የእንስሳት ጤና አጠባበቅና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ላይ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል።
በተለይም በአነስተኛ ወጪና በጠባብ መሬት ላይ ብዙ ምርት ከመሰብሰብ ጋር ተያይዞ በተሰራው ስራ ውጤታማ መሆን ተችሏል። በሌማት ትሩፋት ስራም እንዲሁ ስኬታማ መሆን ተችሏል። የ’ሌማት ትሩፋት’ መርሐ-ግብር ዋና ዓላማ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተለይም በስጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት በበቂ መጠን ማምረት እንዲቻል ማድረግ ነው። በዚህም የስጋ፣ የወተትና የእንቁላል አቅርቦት የተሻሻለ ሲሆን አርሶ አደሩም የተሻለ ገቢ የሚያገኝበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ሀዋሳን ጨምሮ በክልሉ ባሉ ሰባት ከተማ አስተዳደሮች እና አራት ዞኖች የእንስሳት ሀብት ልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ ሲሆን የተሰሩ ስራዎችም እንዲሁ የተሻለ ውጤት የታየባቸው ናቸው።
ደጋማ አካባቢዎች ላይ የተሻሻለ ዝርያዎችን ከቦንጋ በማስመጣት የእርባታ ስራዎች እየተከናወነ ይገኛል። ሶስተኛ ዓመት ላይ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት ስራዎች በየዓመቱ መሻሻሎችን ያሳየ ነው። በዚህም 120 አርሶ አደሮችን በወተት መንደር፣ መቶ አርሶ አደሮች በዶሮ፣ 15 አርሶ አደሮችን በዓሳ ልማት እንዲሁም 20 አርሶ አደሮች በንብ ማነብ ምርት ስራ ተደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ። እነዚህ አርሶ አደሮች ከየመንደሩ የተደራጁ ሲሆን ከየአደረጃጀቱ ሶስት ሰብሳቢዎች ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ እነሱም የሰለጠኑትን ለሌሎች እንዲያሰለጥኑ በማድረግ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው አቶ ታደሰ ይናገራሉ።
በዶሮ ዘርፍ ስራ የተሰማሩ ማህበራትን በተመለከተ የዶሮ እርባታ ስራ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦው ላቅ ያለ ነው። በክልሉ ትምህርት ጨርሰው ስራ የሌላቸው ወጣቶች ተደራጅተው የአንድ ቀን ጫጩት ወስደው በማሳደግ ስራ የተሰማሩ ሲሆን ለአርባ አምስት ቀናት አቆይተው ለሌሎቹ ማህበራት እንዲያስረክቡ ይደረጋል። እነዚህ ማህበራትም ጫጩቶቹን ተረክበው በሚፈለገው ደረጃ ካደረሱ በኋላ እንቁላል መጣል ሲጀምሩ በዓመት ቢያንስ ከአንድ ዶሮ በትንሹ እስከ 3መቶ እንቁላል ያገኛሉ። በዚህም መሰረት የራሳቸውንም የምግብ ፍጆታን ከማሟላት ባሻገር የተሻለ ገቢ እንዲያገኙም ዕድል ፈጥሯል።
የኤክስቴንሽን ባለሙያዎችም አርሶ አደሮቹን በቅርበት እየተከታተሉ ድጋፍ ያደርጋሉ። በዚህ ዘርፍ በ2017 ዓ.ም 10 ሚሊዮን የ45 ቀን ጫጩት፤ 8ሚሊየን የ1ቀን ጫጩት ለማምረት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል። እስከአሁን ባለውም የተሻለ አፈፃፀም እየተገኘበት ነው። በዚህም መሰረት አንድ አርሶ አደር እስከ 5ሺ ዶሮ ማርባት የሚችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።
የንብ ማነብ ስራን በተመለከተ በዘርፉ አቅም ባለባቸው አካባቢዎች ላይ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ። የክልሉ መንግስትም በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ብር ግብዓት መግዣ ድጎማ ያደርጋል። በክልሉ በዓመት ከ2-3 ጊዜ ማር የሚቆረጥባቸው አካባቢዎች አሉ። ለዚህም አንድ አርሶ አደር 1የሽግግር፣ ባህላዊና ዘመናዊ ቀፎዎችን እንዲይዝ ይደረጋል። ንቦቹን ከንብ መንጋ ለመጠበቅ ዳስ ያዘጋጃሉ። ዘመናዊ የሚባለው ከጣውላ የሚሰራው ሲሆን ባህላዊው ደግሞ በአካባቢ በሚገኝ ግብዓት የሚዘጋጅ ነው። ከአንድ ቀፎ በአማካኝ እስከ 16 ኪሎ ግራም ማር ይቆረጣል። ለዚህም አስፈላጊው የባለሙያ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን ከዝግጅት እስከ ውጤት ባለው ሂደትም የባለሙያ ድጋፍ ያገኛሉ። በተለይ ተቀሳሚ ተክሎችን በመትከል፣ እንዳይቆረጡ በመንከባከብ፣ በማልማት፣ ንፅህናን በመጠበቅና በባለሙያ የታገዘ የኬሚካል ርጭት በማድረግ አጥጋቢ ምርት እንዲሰበሰብ እየተደረገ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከንብ በሽታ ጋር ጉዳት እንዳይደርስ የባለሙያ ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል። ይህም ጥራት ያለው ማርና ሰም ለገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ገቢ ከማሻሻል አኳያ አበረታች ውጤት ተገኝቶበታል። በክልሉ በዓመት 3ሺ 20 ቶን ማር ለማምረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። አርሶ አደሮቹ ምርታቸውን ለማህበራት የሚያቀርቡበት የገበያ ሰንሰለትም ተዘርግቷል።
የአሳ ምርትን በተመለከተ በክልሉ ሶስት የኣሳ ማባዣ ማዕከላት ይገኛሉ። የተለያዩ ማህበራትና ግለሰቦች ዓሳን ከማምረት ጀምሮ ለገበያ በማቅረብ እንዲሁም ዓሳ ሾርባ በማዘጋጀት ስራ ላይ ተሰማርተዋል። መንግስት በዘርፉ ለተሰማሩ ማህበራት ዓሳ ለማጥመድ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
የስጋ ከብትን በሚመለከት በ3 ወራት ደልበው ለገበያ የሚቀርቡ ከብቶች ላይም እየተሰራ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በማህበራት ደረጃም ብድር የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷል። ከመኖ አቅርቦት ጋርም እንዲሁ አሰራር ተዘርግቶ አርሶ አደሮች እጥረት እንዳያጋጥማቸው ተደርጓል። አርሶ አደሮች መኖ እንዲያመርቱ፤ ሲደርስ ሳሩን ሸጠው ዘሩን እንዲያስቀምጡ የባለሙያ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። በዚህም የተሻሻሉ የእንስሳት መኖ ዓይነቶችን በማልማት ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢም ተፈጥሮላቸዋል።
ዝርያቸው የተሻሻሉ የወተት ላሞች በተመለከተ አርብቶና አርሶ አደሮች ሀዋሳ ከተማ፣ ይርጋለም፣ በዳሌ ውረዳ ፤ ለኩ፤ ዳዬ ከተማ፥ በመንደር ተደራጅችተው በስፋት እየሰሩ ይገኛሉ። ለማህበራቱ የወተት ማለቢያና ማጓጓዣ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል።
እንዲሁም ሴቶች የሀር ትሎችን ከማልማት ጀምሮ ትሎቹ የሚያመርቱትን ጥጥ ፈትሎ ክሩን ለገበያ እስከ ማቅረብ ድረስ ተደራጅተው በመስራት ላይ ናቸው።
በክልሉ እነዚህ ተግባራት ሲከናወኑ ሴቶች ከመቼውም በላይ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊ ዘርፍ ተሳትፎአቸው መጨመሩን አቶ ታደሰ ያስረዳሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው አሰራር የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አጥጋቢ እንዳልነበር አንስተው በተለይም በእንስሳት ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች የሴቶች ተሳትፎም ሆነ ተጠቃሚነት ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
በቀጣይም በክልሉ በእንስሳት ሀብት ልማት ስራዎች የተገኘውን ውጤት አጠናክሮ ለማስቀጠል በጥናት የተደገፈ እና የህብረተሰቡን ዘላቂ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በክልሉ የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በስፋት ማምረት የሚያስችል አቅም አለ። በሌላም በኩል የዘርፉ ስራ ሲስፋፋ ለዜጎች የስራ ዕድልን የሚፈጥር በመሆኑ የሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ትልቅ አዎንታዊ አበርክቶ የሚያመጣ ነው።
ከዚህ ቀደም ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ ምክንያት አመርቂ ውጤት ሳይገኝ መቆየቱ የሚታወስ ቢሆንም፤ ዘርፉ በቅንጅት ከተመራ፣ በቴክኖሎጂ ከታገዘ፥ የምሁራን ድጋፍ ከታከለበት ችግሮቹን መቅረፍ ይቻላል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የሀዋሳ ግብርና ምርምር ማዕከል እና ወንዶ ገነት ምርምር ማዕከል የክልሉን እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ስራዎች በንብ ሀብት ልማት ሥራ ላይ፤ የተሻሻለ የእንስሳት መኖ ዝርያ፤ በሀር ልማት፤ በወተት ከብቶች አያያዝና አጠቃቀም፣ በዓሣ ልማት ላይ ከፍተኛ ድጋፍን እንደሚያደርጉላቸው አቶ ታደሰ ተናግረዋል።
የ”ሌማት ትሩፋት” መርሐ-ግብር የእንስሳት ተዋእፆ ምርት እምርታን ማረጋገጥ እና ከእምርታው ፍሬም የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ዓላማን ያነገበ ነው። ሀገራችን ለእንስሳት የሚስማማ አየር፣ ለንቦች አመቺ የሆነ ስነ-ምህዳር፣ ያላት በመሆኗ ይህንን አቅም ከመጠቀም አንጻር አሁንም ብዙ መስራት ይጠበቃል።
በምግብ ራስን ከመቻል በላይ የኢትዮጵያን የአምራችነት ታሪክ የመቀየር ግብ ለሰነቀው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ስኬታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር መስራት ያስፈልጋል። በተለይም በዘርፉ ያሉ ምሁራን ለለውጡ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ ናቸውና የተጀመረው በጋራ ሀገርን የማልማት ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል!
More Stories
የልጅነት ገናን በትዝታ፣ የአሁኑን በትዝብት
ልደት እና ባለ ልደት
በኢትዮጵያ ገና ለምን ታህሳስ 29 ይከበራል?