የፍራፍሬ ምድር

በገነት ደጉ

መንግሥት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡  በመላው ኢትዮጵያ የፍራፍሬ ዛፎችን መትከል  እና አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ እንዲያለማ የተሰሩት ስራዎችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በፍራፍሬ ምርቱ ይታወቃል፡፡ በተለይም ክልሉ በሙዝ፣ አቮካዶ፣ ሎሚ፣ ማንጎ፣ ግሽጣ፣ የደጋውን ፍራፍሬ አፕልን ጨምሮ የበርካታ ገፀ- በረከቶች  ምድር ነው፡፡

ይሁን እንጂ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያለውን የፍራፍሬ ሀብት ልማት እምቅ አቅም በተገቢው ተጠቅሟል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለውጪ ገበያ ከማቅረብም ባሻገር የፍራፍሬ አግሮ ፕሮሰስ በማድረግ የተሰራው ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡

የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ግብርና መር ኢንዱስትሪ ለሚከተሉ ታዳጊ ሀገራት ወደሚቀጥለው ደረጃ ለመሸጋገር ለሚያደርጉት ጉዞ አጋዦች ናቸው፡፡

በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የሚሰማሩ ባለሀብቶች የስራ ዕድል ከመፍጠራቸው ባሻገር የውጪ ምንዛሪ ለማሳደግ ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡  የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግም አስተዋጽኦ አላቸው፡፡

አርሶ አደሩ ከፍራፍሬ ምርቱ የተሻለ ገቢ ማግኘት እንዲችል እሴት መጨመር ያስፈልጋል። ለዚህም የአካባቢውን አቅም የሚመጥን አግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ያሻል። በዚህ ረገድ እንደ ሀገር የግብርና ምርቶች ዕሴት በመጨመር የተጀመሩ አበረታች እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው በመቀጠል ወደ ሌሎችም አካባቢዎች  መስፋት  አለባቸው፡፡

በፍራፍሬ ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ መገበያየት አርሶ አደሩ ያወጣውን ጉልበትና ገንዘብ መመለስ እንዲችል ከማድረግ ባሻገር፤ የሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ሚና  ይጫወታል።    

 መንግሥትም ባለሀብቶችን በግብርና ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ለሀገር  ውስጥና ለውጭ ገበያዎች ምርትን የሚያቀርቡበት ዕድል እየፈጠረ ነው፡፡  በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች እየለሙ የሚገኙ ሜካናይዝድ እርሻ ልማቶችም ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ ለዚህም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየለማ የሚገኘው ግዙፉ ዳኜ ሜካናይዝድ እርሻ ተጠቃሽ ነው፡፡

ከሐዋሳ ከተማ በስተደቡብ ምዕራብ 70 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የዳኜ የግብርና ተቋም የግብርና ኢንቨስትመንት ምርጥ ዘር፣ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትና የተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎችን በስፋት ማልማት ጀምረዋል፡፡

በአባያና በብላቴ አካባቢ የተጀመረው ይኼው እርሻ ልማት ከ2 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ይሸፍናል፡፡ መሬቱ በፓፓያ፣ በሙዝና በተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች ተሸፍኗል።

የፍራፍሬ ችግኞች በከፍተኛ ገንዘብ ነው የሚገዙት፡፡ “ግራንድ ናይን” የተባለውን የሙዝ ዘር ከእስራኤል አስመጥቶ በቢሾፍቱ ከተማ እያመረተ ከሚገኝ ኩባንያ ነው የሚገዛው፤ ለአንዱ ችግኝ ብቻ 75 ብር ይከፈላል፡፡

በብላቴ እየለማ የሚገኘው የሙዝ ማሳ አምስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ሲኖረው፣ የ1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡ በሙዝ እርሻው ላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሙዝ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ የሙዝ ችግኞቹ ከዚህ ቀድም በኢትዮጵያ ከተለመዱት የሙዝ ዝርያ ዓይነቶች በምርታማነታቸው የተለዩ ናቸው፡፡

የሙዝ ተክሉ አንድ ዘለላ በጥቅሉ 80 ኪሎ ግራም የሚመዝን ሲሆን፣ የሙዝ ፍሬዎቹ ይዘትም ከተለመደው የሙዝ ዝርያ በመጠንም ተለቅ ያሉ ናቸው።

ሌላው በብላቴ እርሻ እየለማ የሚገኘው የአቮካዶ ምርት ነው፡፡ ይህ እርሻ በአሁኑ ወቅት በአንድ ሚሊዮን የአቮካዶ ዛፎች ተሸፍኖ ይታያል። የአቮካዶ ዛፎቹ ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ከፍተኛ ጥራት ያለው የአቮጋዶ ምርት የማቅረብ እድሎች ይፈጥራሉ፡፡

በብላቴ የሚገኘው የእርሻ ልማት ትኩረት ካደረገባቸው የፍራፍሬ ምርቶች ሌላው የብርቱካን ምርት ሲሆን፥  በአሥር ሺህ የብርቱካን ዛፎች ተሸፍኖ ይታያል።

ከዚህ በተጨማሪም ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ የብርቱካን ግንዶችን ከዑጋንዳ በማምጣት እያለማ ይገኛል፡፡ በላይኛው አዋሽ የግብርና ልማት የሚለማውን “ትንሿ ዛፍ” በሚል ስያሜ የምትታወቀውን ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነች የቫሌንሲያ የብርቱካን ተክል በመግዛት በብላቴ የእርሻ ልማት ከተተከሉት መካከል ተጠቃሿ ናት።

በአጠቃላይ በብላቴ የእርሻ ልማት ውስጥ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ወደ 100,000 የብርቱካን ችግኞች የሚተከሉ ይሆናል፡፡

የለማው የፓፓያ ችግኝም  በመጪዎቹ አራት ዓመታት የሚሰበሰብ ሲሆን፣ ከአንድ ግንድ በዓመት አራት ኩንታል የፓፓያ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ተገምቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፓፓያ ምርቱ ለአገር ውስጥ ገበያ እየቀረበ  ነው፡፡ 

ለእያንዳንዱ የአቮካዶ ዝርያ ችግኝ 200 ብር የወጣበት ሲሆን ለተወሰኑ ምርጥ ዘር ችግኞች ደግሞ እስከ 350 ብር ወጪ ተደርጓል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የ30፣ 40፣ 30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት ጀምሯል፡፡ ይህ ኘሮጀክት በዳሰነች ወረዳ እየተካሄደ ነው፡፡ በዚህ አዲስ ፕሮጀክቱ ሲጀመር በአርብቶ አደሮቹ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ያደከመ ቢሆንም ውጤቱን በማየት አሁን ላይ ግን በብዙ አርብቶ አደሮች ዘንድ ጭምር ከፍተኛ ፍላጎትና መነሳሳት ፈጥሯል። 


የ30፣40፣ 30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት አንድ አርሶ ወይም አርብቶ አደር በመጀመሪያ ዓመት 30፣ በሁለተኛው ዓመት 40 እና በሶስተኛ ዓመት 30 የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል ተጠቃሚ የሚሆንበት መርሃ ግብር ነው። በመጀመሪያው ዓመት በተለይም በቆላማ አካባቢ የሚኖሩ አርሶና አርብቶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው የፍራፍሬ ተክሎችን በመትከል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ 

አርሶ እና አርብቶ አደር አካባቢዎች በ30፥ 40፥ 30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት መንግስት የሙዝ እና ፓፓያ ተክሎችን እንዲሁም የውሃ መሳቢያ ፓምፕ ሰጥቷቸው በማልማት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት መቀየር ችለዋል። ከዚህ ቀደም እንስሳቶቻቸውን ይዘው ለግጦሽ በመንቀሳቀስ የሚኖሩ ሲሆን አሁን ላይ እርሻ በመጀመራቸው ለከብቶቻቸው ጭምር መኖ እያገኙ መሆናቸው ይነገራል፡፡  

በመጀመሪያው ዓመት ትግበራም ከ2 ሺህ 3 መቶ በላይ አባወራዎች የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ሲሆኑ ሁለተኛ ዓመቱን የያዘው የ30፥ 40፥ 30 የፍራፍሬ ልማት ፕሮጀክት ጠቀሜታው በተግባር በመታየቱ በቀሪዎቹ ሁለት ዓመታት ወደ ሌሎቹ አካባቢዎችም የማዳረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በአሁኑ ጊዜ ከ80 በላይ ባለሀብቶች በግብርና በመሠማራት አትክልትና ፍራፍሬዎችን በማምረት ላይ ይገኛሉ። በዞኑ ለግብርና ሥራ የሚሆን ከ438 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሲኖር፤ ከዚህ ውስጥ 134 ሺህ ሄክታር መሬት እየለማ ነው። ቀሪ ሊለማ የሚችል ከ300 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት መኖሩን ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ይህ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ከአካባቢው ማህበረሰብ አልፎ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ለሚመጡ ዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በአሁኑ ጊዜ በዞኑ ከተሠማሩ ከ80 በላይ አልሚዎች መካከል በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ የሚገኘው ፍርኤል ኢትዮጵያ ድርጅት ተጠቃሽ ነው። የፍርኤል ኢትዮጵያ እርሻ ልማት የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል።

ድርጅቱ በዋናነት የሙዝ ምርት የሚያመርት ሲሆን፥ ይህንኑ ምርቱንም ወደ ሶማሊላንድ ይልካል። ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜ ከአራት ሺህ 500 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን ለሀገሪቱም የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው። በቀጣይ የእርሻ ሥራዎችን በማስፋት ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ስለመሆኑ ተግልጿል።

በዞኑ 80 የሚደርሱ አልሚዎች ያሉ ሲሆን፤ ክልሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀ በኋላ በርካታ አልሚዎች ወደ ዞኑ እየመጡ ነው። በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ተጨማሪ 20 አልሚዎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል። ለአካባቢው የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረጉ መሆኑንም ተገልጿል።

በዞኑ ያሉ ባለሀብቶች ወደ 6 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ኢንቨስትመንት ማካሄዳቸውን በመግለጽ፤ ሙዝና ሀባብ ወደ ሶማሊላንድ በቀጥታ እንደሚላክም ተጠቅሷል።

መንግስት ሰፋፊ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ለማካሄድ የጋራ ስምምነቶች ከተለያዩ የውጭ ሀገር ባለሃብቶች ጋር ያደረገ ሲሆን አብዛኛዎቹም የውጪ ገበያን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡

በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ በሚገኙ የችግኝ  ጣቢያዎች አማካይነት የተሻሻሉ ችግኞች ምርት ላይ ወጪ እያደረገ ይገኛል፡፡ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪና የግብርና ምርምር ማዕከላት ለጥረቱ እገዛ ያደርጋሉ፡፡ የመልካሣ የግብርና ምርምር ማዕከል ለቆላ ፍራፍሬ ልማት ብሔራዊ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ምርታማነት ማሻሻያና የገበያ ስኬት ፕሮጀክት  የአነስተኛ አርሶ አደሮችንና ገበያ ተኮር ምርትና ምርታማነት ለማሻሻል አሳታፊ የሆነ ገበያ ተኮር የእሴት ሰንሰለት ማበልፀጊያ ዘዴ አስተዋውቋል፡፡ ዘዴው በራሱ ሁሉን አቀፍ ሲሆን፥ በውስጡ ምርትን፣ ግብዓት አቅርቦትን፣ የግብርና አገልግሎቶችን ግብይትንና የንግድ ሥራ ድጋፍ አሰጣጥ አገልግሎቶችን ያካተተና ውጤት ማስገኘት የሚችል ነው።

የክህሎት ማዳበር በወረዳ ደረጃ ባለው የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት የተነሳ ከወረዳው ውጭ ካሉ አሰልጣኞች ጋር ትስስር እንዲፈጠር ተደርጓል፡፡ ለአብነት መልካሳ፣ አዴት ግብርና ምርምር ጣቢያና የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ከአድአ፣ ጐማ፣ ቡሬ፣ ዳሌና መተማ ለተውጣጡ አርሶ አደሮችና የልማት ሠራተኞች በማንጐና አቮካዶ የማዳቀል ዘዴ ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በጨንቻና በእንጅባራ የሚገኙ የቃለ ህይወት ቤተክርስቲያን ችግኝ ጣቢያዎች ለአርሶ አደሮችና ለልማት ሠራተኞች በአፕል ፍሬ አመራረት ላይ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡

የገበያ ተኮር ችግኝ አዳቃዮች ከምርምር ተቋማትና ትላልቅ ኩባንያዎች ጋር ትስስር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የምርምር ተቋሞች ወይም የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮዎች ከገበያ ተኮር ማዳቀያዎች ለሚገኙ ችግኞች ደንብ በማውጣት ጥራትና እውነተኛነትን የሚያረጋግጥና ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ ማስረጃ ሊሰጥ ይገባል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፍራፍሬ ልማት በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ከሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አንድ ሀሳብ አስፍረው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፥ 34 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ፍራፍሬ እና 7 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል አትክልት ተመርቷል ብለዋል።

ይኽን በደቡብ ክልል የታየ ስኬት በሌሎች ክልሎችም ለማስፋፋት የጋራ እድገት ለማስገኘት እና የምግብ ዋስትና ትልማችንን አሳክቶ ዘላቂ ልማትን በሚያረጋግጥ መልክ ጠንክረን መስራት ይገባል ሲሉም አመልክተዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ክልሉን ሀገራዊ የአትክልትና የፍራፍሬ ልማት ኮሪደር ለማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን እና ከክልሉ ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።