“የሰላም ዋጋ ብዙ ነው” – የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ

“የሰላም ዋጋ ብዙ ነው” – የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ

በመለሰች ዘለቀ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን የአለም የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ ይባላሉ፡፡ ሰላምን በመስበክ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ዞረዋል፡፡ በአካል ጉዳተኞችና በሰብአዊ መብት እንዲሁም በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ በመሳተፍ ይታወቃሉ፡፡ በቆይታችንም የህይወት ተሞክሯቸውን እንዲያስቃኙን እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ንጋት፡እራስዎን በማስተዋወቅ እንጀምር?

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፡ ትውልዴና እድገቴ በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን ነው፡፡ ከ30 አመታት ወዲህ ግን ነዋሪነቴ አዲስ አበባ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የአካል ጉዳተኞች ማህበር መስራች፣ ስራሮ የሚባል በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰራ ድርጅት የቦርድ አባል፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል የሰብአዊ መብት ማዕከል አማካሪና የሰብአዊ መብት አንቂ እንዲሁም የሰላም አምባሳደር ነኝ፡፡ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ነኝ፡፡

ንጋት፡የሰላም አምባሳደር የሆኑበትን ሁኔታ ቢያብራሩ?

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፦ በ1980ዎቹ አካባቢ በደርግ ዘመን በነበረው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት በአንድ እግሬ ላይ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ ከጉዳቴ ካገገምኩ በኋላ በእኔ ላይ የደረሰው በሌሎች ላይ እንዳይደርስ በማሰብ የጦርነትን አስከፊነትና የሠላምን አስፈላጊነት ለመስበክ ወሰንኩ፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ትንኮሳና ጥላቻ በማየቴ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1990 ድረስ በአንድ እግሬ የሰላም ተጓዥ ሆኜ በመዞር ስለ ሰላም ጠቀሜታ እና ስለ ጦርነት አስከፊነት ገለጻ አድርጌያለሁ። የጉዞዬ ዋንኛው አላማ እኛ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ቋንቋ፣  መልክ እና ሀይማኖት ቢኖረንም አንድ ህዝቦች ስለሆንን በሰላምና በአንድነት እንድንኖር በማሰብ ነው፡፡

የእርስ በርስ ግጭቶች ሲኖሩ ንጹሀን ዜጎች፣ ህጻናት፣ ሴቶች፣ አረጋዊያን እና ወጣቶች የጉዳቱ ሰለባ ይሆናሉ።  በአጋጣሚ በእኔ ላይም ጉዳት የደረሰብኝ በጦርነት ምክንያት ነው። ኢትዮጵያ የሰላም አየር የሰፈነባት፣ ፍቅር የሚፈስባት፣ ስራ የምንወድባት ሀገር እንድትሆን የበኩሌን አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ።

በዜጎቻችን ላይ የአካል ጉዳት፣ የኢኮኖሚ ውድመት እና ቀውስ ተመልሶ እንዳይመጣ ከ7 አመታት በላይ መላው ኢትዮጵያንና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን ዞሬያለሁ፡፡ ከአራትና ከሶስት አመታት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያና በአንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ ጦርነቶች በሰላም እንዲፈቱ የድርሻዬን ተወጥቻለሁ፡፡

ንጋት፡የሰላም አምባሳደርነት ማዕረግ እንዴት ሊያገኙ ቻሉ?

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፦ የሰላም አምባሳደርነት ማዕረግ የተሰጠኝ እንግዲህ በአንድ እግሬ በክራንች በመዞር ስለ ሰላም ለከፈልኩት መስዋዕትነት ነው። እኔ በጥላቻና በመጥፎ ዘመን አካል ጉዳት የደረሰብኝ ሲሆን ከ1983 ዓ.ም ጀምሬ ልምምድ በማድረግ ከሸግግር መንግስት ፈቃድ አግኝቼ በሀይማኖት ተቋማትና ከተለያዩ ድርጅቶች የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ሰላም ይሁኑ በማለት የሰላም ተጓዥ ሆኛለሁ።

ከዚህም የተነሳ የሰላም አምባሳደር ማዕረግ ከተለያዩ ተቋማት አግኝቻለሁ። የሰላም ሚንስቴር፣ የአዲስ አበባ የባህል መድሃኒትና ህክምና አዋቂዎች ማህበር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአምባሳደርነት ማዕረግ ሰጥተውኛል፡፡

ንጋት፡የሰላም አምባሳደር ሆነው ሲጓዙ ገጠመኞች ካልዎት?

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፦  በጉዞዬ ብዙ ጥሩም መጥፎም ገጠመኞች ነበሩ፡፡ አካል ጉዳተኛ ሆኜ  በአንድ እግር በክራንች ስጓዝ እጄ የመድማት ሁኔታም ገጥሞኝ ነበር፡፡ መንግስትንና የሐይማኖት ተቋማትን አስፈቅጄ ወደ የመን ተጉዤ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ጫካ ውስጥ የነበሩ ሽፍታዎች አስረውኝ ያለኝን ዘርፈውኛል። በአንድ እግሬ ስጓዝ በበረሃ ላይ የተቀበሩ ፈንጆች ፈንድቶብኝም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥም የሆነ ፓርቲ አባል ነህ ተብዬ ታስሬም ተቀጥቼም አውቃለሁ፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ስጓዝ ሰዎች አዝነውልኝ በትራንስፖርት ሂድ ብለውኝ ገንዘብ አዋጥተው ሰጥተውኛል፡፡ በተለይ በደቡብ አካባቢ ምግብና ወተት እየሰጡኝ አበረታተውኛል። በጉዞዬ ብዙ ፈተናዎች ቢፈራረቁብኝም ከአላማዬ ፈቀቅ አላደረገኝም፡፡

ንጋት፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በህግ ትምህርት ክፍል ስለሚያደርጉት ተግባራት ቢያጫውቱን?

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፦ በዩኒቨርሲቲው በህግ ትምህርት ክፍል ከሚሰጡ አገልግሎቶች አንዱ ነጻ የህግ አገልግሎት ነው፡፡ ይህም ህጻናትን፣ የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸውን ሴቶች፣ አረጋዊያንና አካል ጉዳተኞችን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ነው የምሰራው። ግለሰቦችና ተቋማት የዜጎችን መብት እንዲጠብቁ የማንቃት ስራ እሰራለሁ። የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም በሰብአዊ መብት ዙሪያ ትምህርት እሰጣለሁ፡፡

ንጋት፡የተለያዩ በጎ አድራጎት ተግባራት ላይም እንደሚሳተፉ ገልጸውልኝ ነበር፤ ተግባራቶቹ ምን፣ ምን ናቸው?

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፦  አዎ፤ የሰላም አምባሳደርነት ማዕረግ ካገኘሁ በኋላ ያንን ስም በመጠቀም በሀገሬ ላይ የልማትና የበጎ አድራጎት ስራዎችን እያስተባበርኩ ቆይቻለሁ፡፡ ለአብነትም የሰቆጣ ቃል ኪዳን ስምምነት እንዲጀመር አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ በአማራ ክልል በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም እንዲጀመር ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ከባለሀብቶች፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከሴቶችና ወጣት አደራጃጀቶች ጋር በቅንጅት  በርካታ ስራዎች ሰርቻለሁ፡፡

በመንግስት ትምህርት ቤቶች የቅድመ መደበኛ ትምህርት ባልነበረበት ወቅት ህጻናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲያገኙ በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ብሩህ ተስፋ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲጀመር አስተዋጽኦ አድርጌያሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ   በሁሉም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ቅድመ መደበኛ ትምህርት እንዲጀመር አሻራዬን አሳርፌያለሁ፡፡

ንጋት፡– “ስራሮየተሰኘው ድርጅት ምንድነው ዋና ሥራው?

የሰላም አብባሳደር መዝገቡ አብዩ፦ ጦርነት ሲኖር ከአካል ጉዳት፣ ሞት ወይም ከመፈናቀል አንዱ ይገጥማል። “ስራሮ” የሚባል ድርጅት በተለያዩ ከባድ የጦር መሳሪያ ለተጎዱ ወገኖች የተለያዩ ድጋፎችን የሚያደርግ ሲሆን እኔም ከሌሎች የጦር ጄነራሎች ጋር በመሆን ችግር የደረሰባቸውን ወገኖች እስከ ሆስፒታል ድረስ በመሄድ የሕይወት ክህሎት ስልጠና እሰጣለሁ፡፡ በጦርነቱ ምክንያት እጁ ላይ ወይም እግሩ ላይ ጉዳት ደርሶበት አልቆረጥም ብሎ እንዳይሞት ተቆርጠህ እንደ እኔ መኖር ትችላለህ በማለት አስተምራለሁ፡፡ በጦርነት ብቻ ሳይሆን  በካንሰር፣ በጋንግሪን እና በሌሎች በሽታዎች ምክንያት አልቆረጥም ብለው የሚሞቱ አሉ፡፡

እኔም ለእነዚህ ወገኖች በህክምና ተቆርጦ መዳን እንደሚቻል ተሞክሮዬን አካፍላለሁ፡፡ እኔም አካል ጉዳተኛ ሆኜ ውጤታማ ህይወት እየኖርኩ፣ ቤተሰብ እየመራሁ ሀገሬን እያገለገልኩ እገኛለሁ እያልኩ አስተምራለሁ፡፡ በዚህም የስነ ልቦና ግንባታ ሥራ ብቻ ሳይሆን በህክምና እርዳታ ከሞትም ሲድኑ አይቻለሁ።  ተጎጂዎችም ጤነኞች ከሚያስተምሩ ይልቅ እኛ አካል ጉዳተኞች ስናስተምር በቀላሉ ስነ ልቦናቸው ሊጠገን ይችላል፡፡

ንጋት፡ስለ ትምህርት ሁኔታዎ ማንሳት ብንችል?

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፦ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ፡፡ በትምህርት ላይ ብዙም አልገፋሁበትም፡፡ በወቅቱ አባቴ ሠፊ የእርሻ መሬትና ሀብት ሰለነበርው እንድማር ፈቃደኛ አልበረም፡፡ በራሴ ጥረት እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ተምሬያለሁ፡፡ ሆኖም ግን ከተማሩ ሰዎች ያልተናነሰ ስራዎችን እሰራለሁ፡፡

መደበኛ ትምህርት ውጤታማ የሚሆነው የተወሰኑ ሰዎች ላይ ብቻ ነው፡፡ አብዛኛው ወረቀት ላይ ብቻ ነው የሚቀረው፡፡ መማር አይጠቅምም ማለቴ ግን አይደለም ፍላጎት ካለ ማንኛውንም ስራ ለመስራት ትምህርት አይገድብም። በራሴ ላይ ያየሁትም ይህንን ነው። ከአንድም ሁለት ቦታ  ቢሮዎች አሉኝ። በሁለቱም ቢሮዎች ጻሀፊ የለኝም፤ እራሴ ነኝ በኮምፒዩተር የምጽፈው፡፡ ገንዘብ ከፍዬ ፕሮጀክቶችን የማጸፋቸው ሰዎች እያየሁ ነበር የኮምፒዩተር ጽሁፍ የለመድኩት። ፕሮጅክቶችን በአማርኛ ከቀረጽኩ በኋላ ከፍዬ ወደ እንግሊዝኛ አስቀይራለሁ፡፡   

ንጋት፡ስለ ሰላም አስፈላጊነት ምን አይነት መልዕክት ያስተላልፋሉ?          

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፦  በኢትዮጵያ ላይ መኖር ያለብን በጋራ ነው፡፡ መሬቱ አልጠበበንም፡፡ ሁላችንም የአንድ አዳም ልጆች ነን፡፡ የሰላም ዋጋ ብዙ ነው። ከዛሬ 25 አመታት በፊት የመን ሄጄ ነበር። ያኔ ሰላማዊ ሀገር ነበረች። የእኛ ሀገር ዜጎችም እዛ ሄደው ይሰሩ ነበር። ወደ ሳውዲ አረቢያ መሸጋገሪያ ሆናም ታገለግላለች። በአሁኑ ጊዜ የመን በጦርነት ምክንያት ወድማለች፡፡ እኛም ሀገር ይህ እንዳይመጣ ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ መሰጠት አለበት፡፡

ዛሬ እኔ አካል ጉዳተኛ ሆኜ ብዙ ሮጬ ባልሰራም አቅሜ በፈቀደው መጠን ስለ ሰላም ሰርቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር እና አብሮ ስለመኖር እስቲ እንወያይ እላለሁ፡፡

ለሺህ ዓመታት የኢትዮጵያ ጠላቶች ሌሎች ሀገራት ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን እኛ እራሳችን  የሀገራችን ጠላት ሆነናል፡፡

ታሪክ እንደሚያስረዳው  ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ናት፡፡ ውድ ኢትዮጵያን  በቋንቋ፣ በሀይማኖት፣  በጎጥ እየተከፋፈልን አንጣላ፡፡ አንዳችን የሌላውን ቋንቋውን አክብሩ፣ ባህሉን ጎጂ ካልሆነ ውደዱለት ሀገራችን መሬቷ በጋራ ልንኖርባት ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ህዝብ ማስተማሪያ ሆና የተፈጠረች መሆኗን እንወቅ እንዋደድ የመጣብንን  ጠላት  በጽናት፣ በቅንነትና በመግባባት በሠላም እንፍታ፡፡ ከምንም በላይ እራስ ወዳድነትንና ጎጠኝነትን ከእያንዳንዳችን ሀሳብ ላይ እናስወግድ ማለት እፈልጋለሁ፡፡

ኢትዮጵያዊያን ዥንጉርጉር ቢሆኑም አንድ የሚያደርጋቸው በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን አይቻለሁ፡፡ በዞርኩባቸው የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ጅቡቲ፣ ሱማሊያና ኤርትራ አንድ አይነት ሐበሾች አይቻለሁ፡፡ መልካቸው ቀይ፣ ጸይም፣ ጥቁር፣ ነጭም ሐበሾች አሉ አንድ የሚያደርጋቸው በአብዛኛው ፀጉራቸው ነው።  የሐበሾች ዘር በብዙ ሀገሮች ይኖራሉ፡፡

እኔ ስለ ሰላም በአንድ እግሬ ዞሬ ብዙ ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡ አሁን መጓዝ ባልችልም በሚዲያና በተለያዩ ጉባኤዎች ተገኝቼ የተጓዝኩበትን የሰላም ጉዞ ዓላማ እና የገጠመኝን እንዲሁም የወቅቱ ፈተናን እያነሳሁ ተሞክሮዬን እያካፈልኩ እገኛለሁ። ምቀኝነት ጥላቻ ይጥፋ ሰላም፣ ፍቅርና ልማት ይስፋፋ ማለት እፈልጋለሁ።

ንጋት፡ስለሰጡኝ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናሉ?

የሰላም አምባሳደር መዝገቡ አብዩ፡ እኔም ተሞክሮዬን እንዳካፍል ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡