ከወልቂጤ – ጉብሬ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ህጉን ተከትለው የሚሰሩና የህብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ መሆናቸው ተጠቆመ

ከወልቂጤ – ጉብሬ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ህጉን ተከትለው የሚሰሩና የህብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ ለመሆናቸው ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ከወልቂጤ-ጉብሬ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ህጉን ተከትለው የሚሰሩና የህብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ መሆናቸውን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ከዚህ ቀደም የትራንስፖርት አገልግሎት በሚገለገሉበት ወቅት ያለ ልክ መጫንና ለተለያዩ እንግልት ይዳረጉ እንደነበር ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተናግረዋል።

የታክሲ አገልግሎት ሲጠቀሙ አግኝተን ካነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል መምህር ኬልቂያስ አለሙና አቶ ጀማል ሲገኙበት፥ ከዚህ ቀደም ያለ ልክ መጫንና ለተለያዩ እንግልት ይዳረጉ እንደነበር ተናግረዋል።

መንግስት ያወጣውን የታክሲ ታሪፍ እየከፈሉ አገልግሎት እየተጠቀሙ መሆኑን ያነሱት ተገልጋዮች ታክሲዎቹ በወልቂጤም በጉብሬም የመጫኛና የማውረጃ ቦታዎች ያሏቸው መሆኑ ለመገልገል ቀላል አድርጎታል ብለዋል።

ያነጋገርናቸው አሽከርካሪዎች እንደገለጹት ቀድሞ በረጅም ርቀቶች ህብረተሰቡን ያገለግሉ እንደነበር ሲያነሱ አሁን ላይ የታክሲ አገልግሎት በመጀመሩ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን በማሟላት የመኪና ቀለም ቅያሪ በማድረግ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘው ሞነቤ የወጣቶች ማህበር የታክሲ መኪኖች በተራቸው እንዲጭኑ ተራ ከማስያዝ ባለፈ ተሽከርካሪዎቹ ከተፈቀደላቸው የሰው ቁጥር በላይ እንዳይጭኑ እንደሚቆጣጠሩ የማህበሩ አስተባባሪዎች ተናገረዋል።

ከቁጥጥርና ተራ ከማስከበር ውጪ የተሳፋሪዎች እቃ ተሸክሞ መጫን፣ የሰው መጨናነቅ በሚኖርበት ጊዜ ላይ ተሳፋሪዎችን ከሌባ የመጠበቅ፣ አዛውንቶችና እርጉዝ እናቶች ቅድሚያ እንዲያገኙ ማድረግና ህብረተሰቡ በዜብራ እንዲሻገር የግንዛቤ ስራዎችን እንደሚሰሩ የማህበሩ አስተባባሪዎች አስረድተዋል።

ረዳት ኢንስፔክተር አማረ ተስፋዬ በወልቂጤ ከተማ አስተዳደር የትራፊክ ፓሊስ ሲሆኑ ከወልቂጤ ጉብሬ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ የሚመላለስበት መስመር ሲሆን ነገርግን ከዚህ ቀደም ህብረተሰቡን የሚያመላልሱ የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ከሚፈቅድላቸው የሰው መጠን በላይ በመጫን ተሳፋሪን ለአላስፈላጊ ወጪና ለተለያዩ አደጋዎች ይዳረጉ እንደነበር ሲያነሱ የታክሲ አገልግሎት ከጀመረ ወዲህ ይህ ችግር መቀረፉን ገልጸዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ሶስት ክፍለ ከተማ ያላት ሲሆን የጉብሬ ክፍለ ከተማ ከወልቂጤ በዘጠኝ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን የከተማው ነዋሪ ባስፈለገው ሰአት ለመንቀሳቀስ የታክሲ አገልግሎት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ወጣቶች በማህበር እንዲደራጁ በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር መንገድ ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ትግስቱ ፉጄ ገልጸዋል።

መስፈርቱን በማሟላት 28 ተሽከርካሪዎች የታክሲ አገልግሎትን እየሰጡ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ ትግስቱ ቀድሞ የነበረው ታሪፍ ካለው የናፍጣ መጨመርና የመኪና የመለዋወጫ እቃዎች ጋር የሚሄድ ባለመሆኑ ከማህበሩና ከህብረተሰብ ጋር በመነጋገር የታሪፍ ማሻሻያ መደረጉን አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ ዳዊት ዳበራ – ከወልቂጤ ጣቢያችን