የአርብቶ አደሩን አከባቢ ማህበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ተገለጸ

የአርብቶ አደሩን አከባቢ ማህበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 21/2017ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ከተረጅነት ወደ ምርታማነት ለማሸጋገር በተጀመረው ስራ አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑ ተጠቆመ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ስራቸው ተጓትው የነበሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ስራ ገብተዋል።

መንግስት የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል ከሚሰሩ የልማት ሥራዎች አንዱ የመስኖ ልማት ሲሆን በደቡብ ኦሞ ዞን ሐመር ወረዳ ግንባታው በ2004ዓ.ም ተጀምሮ በቀመጠለት ጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ የቆየው የቁማ መስኖ ፕሮጀክት አሁን ላይ ተጠናቆ ወደ ስራ መገባቱ ተመላክቷል።

በወረዳ በዚሁ የመስኖ ፕሮጀክትና በሌሎች አማራጮች የተለያዩ ሰብሎችንና የጓሮ አተክልትን በማልማት ከአርብቶ አደሩ የምግብ ፍጆታነት ባለፈ ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ እንዳለ የሐመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሣሙኤል ጋርሾ ተናግረዋል።

በዞኑ ቀድም ሲል የግንባታ ስራቸው ተጠናቆ ወደ ማልማት በገቡ የኛንጋቶም ናፍቲኮይት እና የዳሰነች ራቴ የመስኖ ፕሮጀክቶች የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አርብቶ አደሮቹ ገልፀዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ቢሮ የቱሪሚ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ያዘው አፈወርቅ ቁማን ጨምሮ በአርብቶ አደሩ አከባቢ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ከነዳጅ ወደ ሶላርና ኤሌክትርክ ኃይል በመቀየር ወጭ ቆጣቢ ለማድረግ እየተሠራ እንዳለ አመላክተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አከባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ በክልሉ የአርብቶ አደር አከባቢ ማህበረሰብን ኑሮ ለማሻሻልና ከተረጅነት ለማላቀቅ ወደ 30 የሚጠጉ የመስኖ ተቋማት ተገንብተው 15ቱ በሙሉ አቅሙ የመልማት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ወደ ስራ የገቡ የመስኖ ተቋማት ከ5 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳላቸውና አሁን ላይ 4ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከ30 ሺህ በላይ አርብቶ አደሮች እያለሙ እንደሚገኙ ያመላከቱት ቢሮ ኃላፊው፥ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና በነዳጅ የሚሰሩ የመስኖ ተቋማቶችን ወደ ሐይድሮ ኤሌክትሪክና ሶላር ኢነርጂ ለመቀየር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን አመላክተዋል።

በቢሮው የአርብቶ አደር አከባቢውን ማህበረሰብ ኑሮ ለማሻሻል ከሚሰራው የግብርና ልማት በተጨማሪ የኑሮ መሠረቱ የሆነውን የእንስሳት ልማት ሥራውን ለማዘመንና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም የሠላም ግንባተታ ላይ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ እንዳሉ አቶ ታረቀኝ አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ መልካሙ ቡርዝዳቦ – ከጂንካ ጣቢያችን