የማህበረሰቡን ቋንቋ፣ ባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ከማልማት እና ከማስተዋወቅ አንጻር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል – ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ

የማህበረሰቡን ቋንቋ፣ ባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ከማልማት እና ከማስተዋወቅ አንጻር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል – ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሱቡን ቋንቋ፣ ባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ከማልማት እና ከማስተዋወቅ አንጻር የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

በዩኒርሲቲው የቋንቋ፣ የባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ማዕከል በአዲስ መልክ መደራጀትን አስመልክቶ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አውደጥናት ተካሄዷል።

በመርሃግብሩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል፥ ሀገሪቱ የበርካታ አኩሪ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃገር በቀል እውቀቶችና መሠል እሴቶች ባለቤት መሆኗን ጠቁመው፥ ነባር ሃገረሰባዊ እሴቶችን ከዘመን ዘመን ማሸጋገር መቻሉን አንስተው፥ እሴቶቹ ከማስተዋወቅ አንፃር የሚጠበቀውን ያህል አለመሰራቱን አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች በቀጣይ እነዚህ የማህበረሰቡ እሴቶችን በማልማትና በማስተዋወቅ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ በስርዓተ ትምህርቶቻችን ማካተት እንዳለባቸው በመጠቆም፥ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲም ለዘርፉ ውጤታማነት በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የቋንቋ፣ የባህልና የሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ማዕከል በአዲስ መልክ መደራጀትን አስመልክቶ የተዘጋጀው አውደ ጥናት ለዘርፉ ውጤታማነት ፋይዳው የጎላ እንደሆነም አመላክተዋል።

በመድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ እንደገለፁት፥ ቢሮው የሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በርካታ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለይም ክልሉ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ የማህበረሰቡን ቋንቋ፣ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ከማልማትና ማስተዋወቅ አንፃር እያከናወነ የሚገኘው ስራ አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልፀዋል።

የአውደ ጥናቱ መካሄድ ደግሞ በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎች በዘላቂነት ውጤታማ እንዲሆኑ ዕድል አንደሚፈጥር ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የቋንቋ፣ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ዳይሬከተር ረዳት ፕሮፌሰር ካሚል ኑረዲን በበኩላቸው በዩኒቨርስቲው የቋንቋ፣ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ማዕከል መቋቋሙን ጠቅሰው በዚህ ዙሪያ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አውደ ጥናት መካሄዱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በቀጣይ የማህበረሰቡ የቋንቋ፣ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ በማመላከት ለዘርፉ ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት አሰፈላጊውን ድጋፍና ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው ገልፀዋል።

በመድረኩ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ጥናት መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር የወንድወሰን አውላቸው እንዳሉት ሀገር በቀል ዕውቀት በምዕራባዊያን እየተበረዘ መምጣቱን ተከትሎ ባግባቡ ስራ ላይ አለመዋሉን ጠቁመው፥ እሴቱ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ከምርምር ጋር በማስተሳሰር የማልማትና ማስተዋወቅ ስራው ለነገ የማይባል ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

በዩኒቨርሲቲው በአዲስ መልክ የተቋቋመው የቋንቋ፣ ባህልና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ልማት ማዕከል ዓይነተኛ ሚና ይጫወታልም ነው ያሉት።

የአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም በየደረጃው የማህበረሰቡን ባህል፣ ቋንቋና ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ የሚደረገውን ጥረት ትልቅ ዕገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው በዘርፉ የተጀመረው ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በመጠቆም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላትም አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ መሐመድ ሽሁር – ከወልቂጤ ጣቢያችን