በወራቤ ዩኒቨርስቲ ሴቶችን ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት ባለፉት አመታት በተከናወኑ ስራዎች ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸው ተመላከተ

በወራቤ ዩኒቨርስቲ ሴቶችን ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት ባለፉት አመታት በተከናወኑ ስራዎች ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸው ተመላከተ

“50 አመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በወራቤ ዩኒቨርስቲ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ እየተከበረ ባለው በዚህ በአል የኢፌዴሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፎዚያ አሚንን (ዶ/ር) ጨምሮ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ቀመሪያ ረሻድ ፣ የወራቤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ቶፊክ ጀማል(ዶ/ር) ፣ በየደረጃው ያሉ ሴት የአመራር አካላትና ሴት ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።


በበአሉ መክፈቻ ላይ የወራቤ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ኢንጂነር ቶፊክ ጀማል(ዶ/ር) ባስተላለፉት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በዩኒቨርስቲው ሴቶችን ወደ አመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት ባለፉት አመታት በተከናወኑ ስራዎች ለውጦች እየተመዘገቡ መምጣታቸውን ተናግረዋል።


በበአሉ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፍዚያ አሚን (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልእክት አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 ሲከበር ቀኑን አስቦ ለመዋል ብቻ ሳይሆን ባለፉት ሃምሳ አመታት ሴቶች ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና ለመስጠት መሆኑን ተናግረዋል።
የቀኑ መከበር ለሴቶች ትርጉሙ ጥልቅ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ ካለፈው ተምረን ለወደፊት የምንዘጋጅበት ነው ብለዋል።


በእለቱ ሲሆን ሴቶች የትግል ሂደት ያለፉት ሃምሳ አመታት ጉዞን በሚመለከት ለውይይት መነሻ የሚሆን ጽሁፍ የቀረበ ሲሆን ሰፊ ውይይት ይካሄድበታል ተብሎ ይጠበቃል። በዝግጅቱ የሴቶችን ሚና የሚያሳዩ የተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎችም ቀርበዋል፡፡

ዘጋቢ : ወንድወሰን ሽመልስ