ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ጥር 18/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሁሉም የጤና ተቋማት ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ጤና ጽ/ቤት አስታወቀ።

ጽ/ቤቱ “ጥምረት ለጥራት” በሚል መርህ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በተርሆኘ ጤና ጣቢያ አካሄዷል።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ቃሲም ጸጋዬ እንደገለፁት በወረዳው በሁሉም የጤና ተቋማት ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።

በወረዳው በአፈጻጸሙ በቀዳሚነት በሚገኘው ተርሆኘ ጤና ጣበያ “ጥምረት ለጥራት” በሚል መርህ የተከናወነው የጤና ተቋማቱ የመጀመሪያ ግማሽ አመት የተግባር አፈጻጸም ላይ ልምድ በመቅሰምና ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት በቀጣይ በወረዳው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ነው ብለዋል።

ስለሆነም የተርሆኘ ጤና ጣበያ በአገልግሎት አሰጣጥና በተለይ በወሊድ ወቅት የሚከሰተውን የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ ከእናቶች ማረፊያና ሌሎች ተግባራት ጋር ተያይዞ አበረታች ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በመድረኩ ካገኙት ልምድ በመነሳት በየተቋማቸው የተሻለና ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት መስጠት አለባቸው ሲሉ አቶ ቃሲም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የተርሆኘ ጤና ጣበያ ኃላፊ አቶ ተሾመ አለሙ በበጀት አመቱ ለጤና ተቋሙ እየተሰጠ ያለውን የህክምና አገልግሎት ዘመኑን የዋጀ ለማድረግ ባለሙያውና ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ባከናወናቸው ተግባራት ከወረዳው ካሉ የጤና ተቋማት ግንባር ቀደም እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል።

በቀጣይም ከዚህ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አቶ ተሾመ አመላክተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ በሃሩ ደሴ፣ ወ/ሪት ቅድስት አብርድ እና ወ/ሪት ምህረት ሸምሱ በሰጡት አስተያየት ከተርሆኘ ጤና ጣቢያ ባዩት የውስጥ አደረጃጀትና አገልግሎት አሰጣጥ መልካም ልምድ መቅሰማቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ካገኙት ልምድ እና በውይይቱ ከተነሱ ጠንካራና ደካማ ጎኖች መነሻነት በየተቋማቸው የህብረተሰቡ ጤና እንዲጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በተሻለ መልኩ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በመድረኩ ላይ በወረዳው የሚገኙ የጤና ጣቢያ ሀላፊዎችና የትስስር ባለሙያዎች፣ የጽ/ቤቱ የማኔጅመንት አካላትና ባለሙያዎች እንዲሁም የተርሆኘ ጤና ጣበያ አጠቃላይ የጤና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ፉአድ አብደላ – ከወልቂጤ ጣቢያችን