በዘመናዊ መንገድ ንብ የማነብ ስራ በመጀመር ውጤታማ መሆናቸውን በወላይታ ዞን የዳሞት ወይዴ ወረዳ ወጣቶች ተናገሩ
በወረዳው የማር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት አስታውቋል።
በወረዳው በደጋጋለንዳ ቀበሌ ዶሪ መንደር የንብ እርባታ ማህበር በዘርፉ ከተሠማሩ ወጣቶች መካካል የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ተክለ ጋትሶና አባሎቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ሥራ አጥ መሆናቸውን በማንሳት፤ አሁን ተደራጅተው ወደ ሥራ ገብተው ወጤታማ መሆናቸውን ገልጿል።
በማህበር ሲደራጁ የወረዳው አስተዳደር እና የሚመለከታቸው አካላት ባደረጉት ድጋፍ ከሥራ አጥንት ወጥተው ሌሎችን ለመርዳት ሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆናችውን ተናግረዋል።
የማህበሩ አባላት ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ባህላዊውን የንብ ማነብ ስራ ወደ ዘመናዊ ቀይሮ በመስራታቸው የምርት መጠን እየጨመረ መምጣቱን በመጠቆም፤ የማር ፍላጎት እንደ ሀገርም እያደገ መምጣቱ በትኩረት እንዲሠሩ ማገዛቸውን ጠቁሟል።
የንብ ማነብ ስራን የበለጠ በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ዘመናዊ ቀፎ መጠቀም ለምርት የተሻለ ጥቅም እንዳለው ያነሱት የማህበሩ አባላት፤ አሁን ለማህበሩ ከ90 በላይ ቀፎ መኖራቸውን ጠቁመው ከሚመለከታቸው አካላት የሚደረግ ድጋፍ ጥሩ ቢሆንም ለቀጣይ የተሻለ ስልጠና እንደሚፈልጉ ጠቁሟል።
በወረዳው የዳጋጋለንዳ ቀበሌ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድማሱ ወጋሶ፤ በቀበሌው በሁለት ማህበር ከ24 አባላት በላይ ወጣቶች በማር ምርት መደራጀታቸውን በመጠቆም ሥራውን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲተገበሩ ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የዳሞት ወይዴ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ማርቆስ ኡሹላ በበኩላቸው፤ መንግሥት ባስቀመጠዉ አቅጣጫ መሠረት የማር ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በወረዳ ደረጃ በ13 ቀበሌዎች ከ300 በላይ ወጣቶችን ከመንግሥት እና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ድጋፍ ወደ ሥራ ማስገባታቸውን ተናግረዋል።
ለቀጣይ በወረዳ ደረጃ የንብ ማነብ ሥራን አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ ያነሱት ኃላፈው፤ ዘርፉ ዘመናዊ እና አዋጪ መሆኑን በመረዳት ሥራ አጥ ወጣቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሠማሩ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ ይትባረክ ጎአ – ከዋካ ጣቢያችን

More Stories
አሽራፍ ሀኪሚ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ ተመረጠ
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ሕዳር 08/2018 ዓ.ም
የማታ 1፡00 ዜና 24፤ ሀዋሳ፡ ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም