በጎፋ ዞን በያዝነው በጀት ዓመት ከ117 ሺህ በላይ አባወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ
መምሪያው የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2017 በጀት ዓመት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የንቅናቄ መድረክ አካሄዷል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የንቅናቄ መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በተመጣጣኝ ክፍያ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።
በህክምና ተቋማት የሚስተዋለው የመድኃኒት አቅርቦትና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች በፕሮግራሙ ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑን አንስተው፣ችግሩን ለመቅረፍ በየደረጃው ያለው አመራር ለጤና መድህን ፕሮግራም ውጤታማነት መረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሊቃውንት አዛዜ በበኩላቸው በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት 117ሺህ 146 አባወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ96 ሺ በላይ ነዋሪዎችን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ የዕቅዱ 86 በመቶ መከናወኑን አቶ ሊቃውንት ገልጸዋል።
በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ጉድለቶችን ፈጥኖ በማረም ዜጎችን በተሟላ መልኩ የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ አዲስ አባል ማፍራትና ነባር አባላት እድሳት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባም ነው አቶ ሊቃውንት የጠቆሙት።
በኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አርባምንጭ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ጨንቻ መላው የጤና መድህን ፕሮግራም ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠ መሠረታዊ የጤና አግልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጎላ አስተዋጽኦ ስላለው ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በቂ ሀብት ማፍራት አስፈላጊ በመሆኑ ገቢን መሠረት ያደረገና ከገበያ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ የክፍያ ስርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ማአጤመ አስተባባሪ አቶ ታዲዮስ ጣሊያን የአፈፃፀም ጉድለት የሚታይባቸው መዋቅሮች አሰራርና ስርዓቱን ተከትለው የነባር አባላት እድሳት እና አዳዲስ አባላትን በማፍራት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል
የጤና መድህን መርሀግብር የጤና አግልግሎት ፍትሀዊነትና ተደራሽነት ያረጋገጠ ሰው ተኮር ፕሮግራም በመሆኑ ለውጤታማነቱ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ያነጋገርናቸው አስተያዬት ሰጭዎች ገልጸዋል።
ዘጋቢ ፡ አይናለም ሰለሞን ከሳውላ ጣቢያችን
More Stories
ከመማር ማስተማር ተግባሩ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ጥረት ቢደረግም በተፈለገው ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን የቱም ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ መምህራን ተናገሩ
ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በጋራ በመከላከል የሸማቹን ህብረተሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ
ጳጉሜ 2 የሪፎርም ቀን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ የዞንና የክልል አመራሮች በተገኙበት ወይይት ተካሂዷል።