በሆሳዕና ከተማ በዋቸሞ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ የሆነው ታዳጊ ብሩክ ግርማ ሮኬት ፣ ደሮኖችን፣ ደማሚት (Dymamet) ከነ መቆጣጣሪያ ስርዓት የፈጠራ ውጤት
ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ለፈጠራ ስራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት የፈጠራ ስራዎች ለታለመው አገልግሎት መዋል እስክችሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትኩረት እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራ የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ጽ/ቤት አስታውቋል።
ታዳጊ ብሩክ ግርማ ይባላል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሀዲያ ዞን በሆሳዕና ከተማ አስተዳደር በዋቸሞ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ11ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነው ::
ተማሪው ከጨቅላነት ዕድሜው አንስቶ ለፈጠራ ስራዎች የነበረው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት በዙሪያው የሚያገኛቸውን የኤሌክትሮኒክስና እና ያገለገሉ ቁሳቁሶችን በመገጣጠም እና በመፍታት አሃዱ ብሎ መሞከር የጀመረው ጥረት አብቦ ዛሬ ላይ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን እንዲያበረክት እንዳስቻለው ይናገራል።
ከዚህ ቀደም በ1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ሳለ ባለሦስት እግር ባጃጅ፣የሌብነት መቆጣጠሪያ መጥሪያ (alarm)፣ እንኩቤተር፣ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽን፣ ያለ ኔትወርክ የሚሰራ አጭር መልዕክት መላላኪያ፣ በኮሮና ወቅት ያለእጅ ንክኪ የሚሰራ እጅ መታጠቢያና ሌሎችንም የፈጠራ ስራዎችን ታዳጊው ሰርቷል።
ተማሪው በአሁኑ ወቅት 6 የፈጠራ ስራዎችን ከ10 ስስተም መቆጣጠሪያ ጋር እስከ 3ኪ/ሜ መወንጨፍ የሚችሉ ሮኬቶችን፣ SAR BOMB የተሰኙ ፍንዳታዎችን ሊያስከትል የሚችል ደማሚቶችን (Dymamet)፣ የሚሊታሪ እና የካሜራ ድሮኖችን ከነ መቆጣጠሪያ ስርዓት ይፋ አድርጓል።
ትምህርት ቤቱ እና መምህራኖቹ ቁሳቁሶችን በማቅረብ እና በምክር እገዛ ሲያደርጉለት እንደነበር የሚናገረው ተማሪው ሌሎች ያቀዳቸውን ጨምሮ የተጀመሩ የፈጠራ ስራዎች ከግብ እንዲደርሱ የቁሳቁስና የፋይናንስ ድጋፍ አለመኖር እክል እንደፈጠረበት ገልጿል::
ወደፊት የሀገርን ዳር ድንበር የሚያስጠብቁና ጠላትን ድባቅ መምታት የሚችሉ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እንዲመረቱ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የገለፀዉ ተማሪ ብሩክ ከዚህ ባሻገር የፈጠራ ባለሙያ በመሆን ማሽነሪ ነክ እና ሶፍትዌሪን መሰረት ያደረጉ ፈጠራዎች ላይ በመሳተፍ ከአለም አቀፍ ካምፓኒዎች ጋር ለመስራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል::
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አዳነ ዘመድኩን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ለሆነው ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት ከግለሰቦች ከሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች በተጨማሪ በከተማው በሚገኙ አምስት 2ኛ ደረጃ እና አስራ ሦስት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች የፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት አዉደ-ራዕይና ኤግዚብሽኖችን በማመቻቸት ዕውቅና አንዲያገኙ ጭምር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከወን ላይ ይገኛል ብለዋል።
በዘርፉ የሚያጋጥሙ ቸግሮችን በመቅረፍ ጅምር ላይ ያሉ የፈጠራ ስራዎች ተግባር ላይ ወርደው የተፈለገውን ዓላማ እንዲያሳኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እና ትኩረት እንዲያገኙ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ይህንንም በቀጣይ አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ኃላፊው አቶ አዳነ ገልፀዋል።
ዘጋቢ :ሄኖስ ካሳ-ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የእርሻ መሳሪያዎችን የማምረት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ
በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ ልማቶችን በጥናትና ምርምር አስደግፎ በመሥራት ረገድ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ
የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማስፋፋት የእርባታ ስራውን ምርታማነት የማሳደግና የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ