የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የእርሻ መሳሪያዎችን የማምረት ሥራ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ታህሳስ 21/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎችን የማምረት ሥራን አጠናክሮ መቀጠሉን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ የሚዛን የገጠር ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ማዕከል አስታወቀ።
በማዕከሉ የሚመረቱ ቴክኖሎጂዎችና አነስተኛ የእርሻ መሳሪያዎች ጊዜ ጉልበትን የሚቆጥቡ መሆናቸው ተገልጿል።
የሚዛን ገጠር ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ማዕከል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ስር የሚተዳደርና በ1991 ዓ.ም ተመስርቶ 33 የሰው ሀይልን ይዞ ለ6ቱም ዞኖች የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎችን በማምረት በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ የሚገኝ ተቋም ነው።
ማዕከሉ በክልሉ ባሉት 6 ዞኖች ለአርብቶና አርሶ አደሩ የግብርናና የእርሻ መሣሪያዎችን ተደራሽ በማድረግ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝ የሚዛን ገጠር ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ማዕከል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጌታቸው ተናገረዋል።
ማዕከሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማምረትም ባሻገር በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁና ሞዴል ለሆኑት ማህበራት የቴክኖሎጂ ሽግግር በማደረግ አርሶና አርብቶ አደሩ ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ታስቦ እንደሆነ ኃላፊው አብራርተዋል።
ከ30 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የድህረና ቅድመ-ምርት ቴክኖሎጂዎች በማዕከሉ ተመረተው እንደሚሰራጩ የገለፁት አቶ ሰለሞን ከ80 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ስልጠና መሰጠቱንም አስረድተዋል።
የተለያዩ ፕሮጀክቶች ከማዕከሉ ጋር ለመስራት እየተፈራረሙ ከመሆናቸውም ባለፈ ከዞኖች ጋር እየተደረገ ያለው የተጠናከረ ግንኙነት ለተቋሙ የጎላ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ በየዞኖች የሚገኙ የስራ ክህሎት ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ተቋማት ትኩረት ወሳኝ እንደሆነ ኃላፊው ገልፀዋል።
ማዕከሉን ለማጠናከር በባለፉት ጊዜያት ክልሉ የ1 ሚሊዬን ብር ጥሬ ዕቃ ድጋፍ ማደረጉን አቶ ሰለሞን አውስተው የአርሶ አደሩን አቅም ያማከለና የተቋሙን አለማ ያልሳተ ቴክኖሎጂዎችን የማምረቱ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ካነጋገርናቸው የማዕከሉ ባለሙያዎች መካከል የብረታ ብረት ስራ ክፍል አስተባባሪና የማሽን ባለሙያ ህይወት ገዛኸኝ፣ የእንጨት ሥራ ክፍል አስተባባሪ አቶ አንዷለም ባህሩ እና የቴክኖሎጂ አቅርቦትና ስርጭት ባለሙያ አቶ ገበየሁ ምትኩ በሰጡት አስተያየት የተለያዩ ለገጠር እርሻ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እያመረቱ እንደሚገኙም ተናገረዋል።
ከሚመረቱት ቴክኖሎጂዎች መካከል የበቆሎ ማፈልፈያ፣ የስንዴ፣ የገብስ፣ የሩዝና የጤፍ ማበጠሪያዎች፣ የቆጮ ማፋቂያ፣ የወተት መናጫ፣ የጀርመንና የኬንያ ቀፎ ሞዴሎች፣ የዕንቁላል መጣያ ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ የእርሻ መሳሪያዎች የመሳሰሉት እንደሚገኙበት አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል።
በማዕከሉ የሚመረቱ አነስተኛ የእርሻ መሳሪያዎች ለአርብቶ አደሩና ለአርሶ አደሩ ጊዜ፣ ጉልበትና ኢኮኖሚን በመቆጠብ ረገድ ከፍተኛ ሚና ያላቸውና በቀጣይም ተቋሙ አነስተኛ ትራክተሮችን ከመስራትም ባለፈ የትራክተር መለዋወጫዎችን ለመስራት ማቀዱም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡ አብዲሳ ዮናስ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በሆሳዕና ከተማ በዋቸሞ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ የሆነው ታዳጊ ብሩክ ግርማ ሮኬት ፣ ደሮኖችን፣ ደማሚት (Dymamet) ከነ መቆጣጣሪያ ስርዓት የፈጠራ ውጤት
በመንግስት ተደራሽ ያልሆኑ ልማቶችን በጥናትና ምርምር አስደግፎ በመሥራት ረገድ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተገለጸ
የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን በማስፋፋት የእርባታ ስራውን ምርታማነት የማሳደግና የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ