በቴክኖሎጂ የተካኑ ዜጎችን ለማፍራት በትኩረት በመሥራት ሀገሪቱን ማበልጸግ እንደሚገባ ተገለጸ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ “ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እንተጋለን” በሚል መሪ ቃል “የነገው ቀን” በውይይት መድረክ ተከብሯል።
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የዲላ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ መንግሥቱ ተክሌ፤ ዓለማችን በቴክኖሎጂ ምጥቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሚጠበቀው በላይ እየፈጠነ እንደሚገኝ ገልፀው ከቴክኖሎጂው ዕድገት እኩል በመራመድ ከዓለምአቀፉ ማሕበረሰብ ጋር ተመሳሳይ መስተጋብር መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል።
በተለይ በኢትዮ-ኮደርስ፣ በዲጂታል መታወቂያ፣ በዕለተ ተዕለት የኮምፒውተር አጠቃቀም ዙሪያ ሁሉም የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው መንግስት የተቻለውን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በመጠቀም የነገውን ትውልድ በቴክኖሎጂ ለመቅረጽ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።
መረጃ ሀብት በሆነበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያም የመረጃ ሀብቷን ከማከማቸት እስከ መጠበቅ የዘለቀ ስኬታማ ለውጥን በማምጣት በቴክኖሎጂው ዘርፍ የነገ መሰረቷን እያደላደለች ትገኛለች ሲሉም ኃላፊው አክለዋል።
የዲላ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታሪኩ በየነ፤ ዓለም የ5ጂ ቴክኖሎጂ ባለቤት ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ቀድማ እየሠራችበት እንደሆነ በመጠቆም በቴሌ ኮሙኒኬሽን፣ በዲጂታል ፋይናንሲንግ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አተገባበር ረገድ አበረታች ለውጦች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
የተለያዩ የግብር ክፍያዎችን ለመክፈል፣ የተለያዩ ምርቶችን ለማስተዋወቅም ሆነ በገበያ ማዕከላት ለመሸጥ፣ የባንክ ቤት ሂሳቦችን ለማንቀሳቀስና ለማዘዋወር በአሁኑ ሰዓት ያለ ቴክኖሎጂ እገዛ የማይታሰብ ነው ያሉት አቶ ታሪኩ፤ በተለይ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን በዘርፉ ማበረታታትና መደገፍ ይገባቸዋል በማለት በአጽንኦት ተናግረዋል።
አክለውም ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕድገት ሥራ ጎን ለጎን በአሁኑ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የሳይበር ደኅንነት ጥቃቱን ለመከላከል ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የሚቃጡባትን ጥቃቶች በውጤታማነት እየተከላከለች እንደምትገኝ በመግለፅ ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመጠቀም የመረጃ ሀብትን ከመጠበቅ ጎን ለጎንም የሀገሪቱን ስልጣኔ ለማፋጠንና የመንግሥት አገልግሎትን ለማዘመን በተጀመረው ርብርብ ሁሉም ተቋማት በባለቤትነት ሊሰሩበት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: እስራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
በቴክኖሎጂና ፈጠራ ተወዳዳሪ የሰው ኃይል በማፍራት የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማፋጠን የሃገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ እየሰራ መሆኑን በስልጤ ዞን የቂልጦ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ገለፀ
የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሥራዎችን ለማጠናከርና ዘርፉን በማሳለጥ በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኦሞ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ገለፀ
ለዜጎች በሶላር ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ስልጠና በመስጠት ዘርፉ ላይ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አስታወቀ