ከተጫዋችነት ተተኪ ወደ ማፍራት

በአስፋው አማረ

የዛሬው አሰልጣኝ እግር ኳስን የጀመረው ገና በለጋነት እድሜው ነበር። በዚሁ በታዳጊነት ዕድሜው በእግር ኳስ ፍቅር ተለከፈ፡፡ ይኸው ፍቅር አድጎ ተጫዋች የመሆን ሕልሙ ተሳክቶ ያ ጊዜ ሲያበቃ ደግሞ አሰልጣኝ ለመሆን በቅቷል።

ሙሉ ስሙ አሰልጣኝ ሚካኤል ወልደሩፋኤል ይባላል፡፡ የተወለደው አዲስ አበባ ኮተቤ በሚባለው ሰፈር ነው። በሰፈርና በትምህርት ቤት ሜዳዎች ላይ በመጫወት ነበር የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው፡፡

ታዳጊው እግር ኳሱ ላይ የነበረው የተለየ ትኩረት ለትምህርቱ ጥሩ እንዳልሆነ በማሰብ በቤተሰቡ ውሳኔ ገና የ4ኛ ክፍል ተማሪ እያለ በሀዋሳ ከተማ ወደ ሚኖረው አጎቱ ይላካል።

እንደ ድንገት ሆነና በአጎቱ መኖሪያ አቅራቢያ ስቴዲየም ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ለአሰልጣኝ ሚካኤል እግር ኳስን በልጅነቱ ለመጫወትና በቀላሉ በፕሮጀክት ለመታቀፍ እድሎች ፈጠሩለት፡፡

ለስፖርቱ ትልቅ ፍቅር ስለነበረውም ስቴዲየም ጨዋታ በሚኖርበት ወቅት መመልክት ያዘወትር ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገርም እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ታዳጊ፣ እግር ኳስን በጨርቅ ኳስ ሰፈር ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር በመጫወት ክህሎቱን ያሳድግ ነበር፡፡

ከዚያም በፕሮጀክት በመታቀፍ እግር ኳስ መሰልጠን ጀመረ፡፡ ከስልጠናው ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የሰፈር ቡድኖች ጋር ግጥሚያ/ ውድድር ያከናውን ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ በበርካቶች ዘንድ አድናቆት ይቸረው ነበር፡፡

በዚህም ከሀዋሳ ተመርጦ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች በመሄድ የመጫወት እድሎችም ተፈጠሩለት፡፡ ይሄ አጋጣሚ ደግሞ እሱ እና ጓደኞቹ በልጅነታቸው ለሐዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ለመጫወት ወደ ነበራቸው ህልም የሚመራ ነበር፡፡

በትምህርት ቤት ጨዋታ ክልሉን በመወከል ድሬዳዋ ከተማ ላይ በተካሄደው የኢትዮጵያ የትምህርት ቤቶች ውድድር ላይ ተሳትፎ ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ በማሳየት ከውድድሩ በሚመለስበት ወቅት ነበር በወቅቱ አሰልጣኝ ታመነ ይርዳው አማካኝነት ለ3 ታዳጊዎች የሙከራ እድል ሲሰጥ ነው ሚካኤል አንዱ መሆን የቻለው።

በዚህም ወደ ሐዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ የመግባት እድሉን ማግኘቱን ይናገራል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ሜዳ ላይ በሚያሳየው ድንቅ ብቃት ከተጠባባቂነት ወደ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ መግባት ቻለ፡፡

በእግር ኳስ ህይወትህ ለአንተ የመጀመሪያው ትልቅ ስኬት ምን ነበር? ብለን ላነሳንለት ጥያቄ ሲመልስ፦

“ሐዋሳ ከነማ እግር ኳስ ቡድንን ከተቀላቀልኩ በኋላ የመጀመሪያውና ሁልጊዜ የማልዘነጋው ቢኖር አንድ ክስተት ነው፡፡ እሱም በ1996 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፕዮን ስንሆን የነበረው ደስታ እጅግ በጣም ከልክ ያለፈ ነበር፡፡

“ይህ ጊዜ ለእኔና የቡድን አጋሮቼ ቀላል አልነበረም፡፡ በወቅቱ የተሰማን ደስታ እስካሁን ድረስ በህሊናዬ ተስሏል። የነበረው የመጨረሻ ጨዋታ በእኔም በክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ሁሌም አብሮ የሚኖር ነው፡፡ በተለይም ደግሞ የማሸነፊያውን ጎል በማስቆጠሬ ደስታዬን ልዩ ያደርገዋል።

“ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ ክልሎች የመጣ ዋንጫ ነበር። ትልቅ አክብሮትና አድናቆት ተችሮናል። እንደዚሁም የተለያዩ ሽልማቶች ተበርክቶልናል፡፡ ይህ ስኬት ለእኔ የመጀመሪያው ነበር ማለት እችላለሁ፡፡

“ከዚህ በኋላ ነበር ሌሎች የተለያዩ ትላልቅ ስኬቶችን እውን ማድረግ የቻልኩት፡፡ በ1997 ዓ.ም ደግሞ የኢትዮጵያ የክለቦች ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮን ዋንጫን ማሳካት ችያለሁ፡፡ ይህ ደግሞ ይበልጥ ከእግር ኳስ ማህበረሰቡ ጋር በስፋት የተዋወኩበት አጋጣሚን ፈጥሮልኛል” ሲል አሰልጣኝ ሚካኤል ይናገራል፡፡

በተለይም ሜዳ ላይ በሚያሳየው ድንቅ ብቃት ቋሚ ተሰላፊ የነበረው ሚካኤል÷ በ1997 ዓ.ም ደግሞ የአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ እና በኢስት አፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ላይ ተጫውቶ ማሳለፉን በቆይታችን ወቅት ለማወቅ ችለናል፡፡

በአፍሪካ የተካሄዱ የተለያዩ ውድድሮች ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ በ1998 ዓ.ም በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ በመሳተፍ በግል ብቻ ሳይሆን እንደ ቡድን ጥሩ የሚባል ውጤትና ልምድ ማካበት መቻላቸውን ይናገራል፡፡

ከምንም በላይ በሐዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ውስጥ መጫወቱ እና ያሳለፋቸው በጣም ጥሩ የሚባሉ ጊዜያቶች ዛሬ አሰልጣኝ እንዲሆን መሰረት እንደሆኑትም ይገልጻል፤ በክለቡ ውስጥ ብዙ ዓመታትን መጫወቱን በማስታወስ፡፡

ሐዋሳ ከነማ እግር ኳስ ክለብን ከለቀክ በኋላ ቀጣይ ያረፍክበት ክለብ የትኛው ነው? ብለን ያነሳንለትን ጥያቄ ሲመልስ ደግሞ፦

“በሐዋሳ ከነማ ለአራት ዓመት ያህል ከተጫወትኩ በኋላ በቀጣይ ያመራሁት ወደ ኒያላ እግር ኳስ ክለብ ነበር፡፡ በዚህ ክለብ ውስጥ ለሁለት ዓመት በቀኝ የአማካይነት ስፍራ ላይ በመጫወት ጥሩ የሚባል ጊዜ ማሳለፍ ችያለሁ፡፡

“ከኒያላ በመቀጠል ለሻሸመኔ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መተሀራ ስኳር፣ ሀረር ቢራ፣ አርሲ ነገሌ፣ ኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች እና አምበርቾ ዱራሜ ክለቦች ለእያንዳንዳቸው ለአንድ ዓመት፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ወልቂጤ ከነማ ክለቦች ለእያንዳንዳቸው ሁለት አመት፣ እንዲሁም ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋሳ ከነማ ሶስት ዓመት ተጫውቻለሁ” በማለት ያሳለፈውን የእግር ኳስ ጉዞውን አጫውቶናል፡፡

አሰልጣኝ ሚካኤል በተጫዋችነት ለመጨረሻ ጊዜ የተጫወተበት ክለብ አርሲ ነገሌ እግር ኳስ ስፖርት ክለብ እንደሆነ አውግቶናል፡፡

እግር ኳስ እየተጫወተ ወደፊት አሰልጣኝ የመሆን ከፍተኛ ዝንባሌ ስለነበረው የተለያዩ የአሰልጣኝነት ስልጠናዎችን እንደወሰደ ይገልጻል፡፡ በዚህም የተጫዋችነት ዘመኑ እንዳበቃ ስልጠናውን በማጠናከር ወደ ማሰልጠን መግባቱን ይናገራል፡፡

ከወሰዳቸውም ስልጠናዎች መካከል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ማህበር እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከብራዚል ፕሮፌሽናል ማህበር (ETHIOPIA-GERMAN Long-term football project፣ EPFA- EFF Brazilian professional)፣ እንደዚሁም ከአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር የ“ዲ” ፈቃድ ማግኘቱን ተናግሯል። በአሁኑ ወቅት የካፍ “ቢ” የአሰልጣኝነት ፈቃድ በመውሰድ ላይ መሆኑን ይናገራል።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ከተማ “አንድነት የታዳጊዎች እግር ኳስ ፕሮጀክት” በሚል መጠሪያ ታዳጊዎች ላይ በመስራት ላይ መሆኑን አውግቶናል። በዚህ ፕሮጀክት እስካሁን ከአንድ መቶ በላይ ታዳጊዎች ሰልጥነው ማለፋቸውና አሁንም በማሰልጠን ላይ ነው፡፡

በፕሮጀክቱ ሰልጥነው ወደ ተለያዩ እግር ኳስ ክለቦች ተመልምለው የተወሰዱ ታዳጊዎች መኖራቸውን ገልጾ÷ በቀጣይም ታዳጊዎች ላይ በሰፊው የመስራት እቅድም እንዳለው አጫውቶናል፡፡