“ማንበብና መፃፍ ልዩ ባህሪዬ ነው” – ነጋሽ ወልደኪዳን /ገጣሚ፣ ጋዜጠኛና ሐያሲ/

“ማንበብና መፃፍ ልዩ ባህሪዬ ነው” – ነጋሽ ወልደኪዳን /ገጣሚ፣ ጋዜጠኛና ሐያሲ/

በአብርሃም ማጋ

አቶ ነጋሽ ወልደኪዳን የዛሬው ባለታሪካችን ናቸው፡፡ ከላይ በርዕሱ የተጠቀምነውን ሃሳብ ያነሱት የተለያዩ ሙያዎች ባለቤት በመሆናቸው ካካበቱት ልምድ በመነሳት ነው፡፡

ይህንኑ ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩም ከአንድ ሺህ የሚበልጡ መፅሃፍትን ማንበባቸውን ይገልጻሉ፡፡ በርካታ ግጥሞችን መግጠማቸውንም በማከል፡፡ የተለያዩ አስቂኝና አስደሳች የሆኑ ማህበራዊ ህይወት የሚዳስሱ ጽሑፎችን አዘጋጅተውና ጽፈው ከትምህርት ቤት ሚኒ ሚዲያ ጀምሮ የተለያዩ የሚዲያ አማራጮችን በመጠቀም ማሰራጨታቸውን በመጥቀስ ያብራራሉ፡፡

አክለውም ከ5ኛ ክፍል ጀምረው እስከ አሁን ድረስ መጽሐፍ ማንበብና መጻፍ የዘወትር ሥራቸው መሆኑን የተናገሩት ለልዩ ባህሪያቸው ያላቸውን ፍቅር ለመግለፅ ነው፡፡

ለመግቢያነት ይህንን ካልን ስለሙያቸው እና አጠቃላይ የሕይወት ታሪካቸው ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ መልካም ንባብ፡፡

ገጣሚ፣ ጋዜጠኛና ሐያሲ ነጋሽ ወልደኪዳን በቀድሞው አጠራር በሲዳሞ ክፍለ ሃገር፣ በወላይታ ሶዶ አውራጃ ሶዳ ከተማ በ1948 ዓ.ም ነው የተወለዱት፡፡ አሁን 69ኛ እድሜያቸው ላይ ይገኛሉ፡፡

ትምህርት ቤት በልጅነታቸው ነበር የገቡት፡፡ ገና የ5 ዓመት ልጅ እያሉ አባታቸው ቤት ውስጥ ፊደል እንዳስቆጠሯቸው ያስታውሱታል፡፡ በዚህ መነሻ በ6 ዓመታቸው ሊጋባ በየነ አባኮስትር ት/ቤት ገብተው ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡

በትምህርታቸው ጐበዝ ተማሪ ስለነበሩ የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 96 ነጥብ 4 በማምጣት ወደ 9ኛ ክፍል ተዛወሩ፡፡ በወቅቱ በት/ቤቱ የበቁ፣ ጥሩ ደረጃ ላይ የነበሩ፣ እንዲሁም በቂ እውቀት የሚያስጨብጡ መምህራን ስለነበሩ እሳቸውንም ጥሩ ውጤት እንዲያመጡ ማገዛቸውን ከምስጋና ጋር አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ውጭም በት/ቤቱ ከውጭ ሃገር የመጡና ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ መምህራን /ፒስኩሮች/ ነበሩ፡፡ ከ4ኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርቱ የሚሰጠው በእግሊዝኛ ስለነበርም ገና በጅምሩ በእነዚሁ መምህራን እገዛ ቋንቋውን አቀላጥፎ ለመናገር በቅተዋል፡፡

5ኛ ክፍል እያሉ ከመደበኛ ትምህርት ጐን ለጐን ሰዎችን የማሳቅ ፕሮግራም ስለተጀመረ ከነበሩት ተማሪዎች ጋር ተወዳድረው በማሸነፍ የት/ቤቱን ማህበረሰብ በማሳቅና በማስደሰት በቀዳሚነት ይጠቀሱ ጀመር፡፡

በዚሁም በየወቅቱ በሚዘጋጁ አጫጭር አስቂኝ ጽሑፎች 1ኛ በመውጣት ደብተርና ስክሪብቶ መሸለም የተለመደ ተግባራቸው ሆነ። አዲስ አመት ሲገባ ደብተሩም ሆነ እስክሪብቶ ከእሳቸው አልፎ ለታናሽ እህታቸው ይተርፍ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በት/ቤቱ የክርክር /ዲቤት/ እና የቲያትር ቤት ተቋቁሞ ስለነበር በክርክር፣ እንዲሁም በትወና ከፍተኛ ብቃታቸውን ማስመስከርም ችለው ነበር፡፡

በወቅቱ ከሌሎቹ ተማሪዎች ልጅ ስለነበሩ በትልልቆቹ መካከል ገብተው እንደለማኝና እንደአሽከር ሆኖ በመተወን የተመልካቹን ልብ በከፍተኛ ሁኔታ ይስቡ ነበር፡፡

ሁለገቡ ነጋሽ በከፍተኛ ውጤት ወደ 9ኛ ክፍል እንደተዛወሩ በቀጣይነት ያሉ ክፍሎችን የተማሩት በባሌ ክፍለ ሃገር በጐባ ከተማ በአዝማች ደግላሀን ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነበር፡፡

በ1961 ዓ.ም 9ኛ ክፍል በት/ቤቱ ሲማሩ ምርጥ አንባቢያን ተማሪዎች ይሸለሙ ስለነበር እሳቸውም ከቤተመጽሐፍ በሳምንት 3 መጽሐፎችን አውጥተው በማንበብ ፈጣን አንባቢ በመሆን ይሸለሙ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

ከዚህ ውጭም በት/ቤቱ እውቅና ተሰጥቷቸው በከተማዋ የተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮችን በመቃኘት ከሁለት ገጾች ያላነሰ የትዝብት ፅሑፎችን በማዘጋጀት ጠዋት ጠዋት ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል በማንበብ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ያስጨብጡ ነበር፡፡ አስቂኝ ጽሑፎችም በማዘጋጀት ገና በጠዋቱ ያስቁና ያስደስቱም ነበር። በዚህም የትዝብት ጋዜጠኛ ለመሆን በቅተዋል።

በተጨማሪም የ1ዐኛ ክፍል ተማሪ እያሉ በት/ቤቱ መምህራን አጓጊ ርዕስ እየተሰጣቸው በክርክር /ዲቤት/ ላይ ሁሌ እየተሳተፉ በማሸነፍ ታዋቂ (Popular) ተከራካሪ ሆነው ይሸለሙም ነበር። የክርክር ጥበብን ከዚህ ት/ቤት መማራቸውን ሳይገልፁ አላለፉም፡፡

በ1964 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ውጤት ቢያመጡም በግል ውሳኔያቸው ለመማር አልፈለጉም፡፡

በመሆኑም በ1965 ዓ.ም ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ወላይታ ሶዶ ከተማ ተመልሰው በወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበርን /ወወክማ/ ተቀላቅለው ለሁለት ዓመታት ያህል ነፃ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡

በ1967 ዓ.ም ደግሞ ጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው 6 ወር ከተማሩ በኋላ እድገት በህብረት የእውቀትና የሥራ ዘመቻ አዋጅ ሲታወጅ እሳቸውም በካፋ ምድብ ጣቢያ ጅማ ተመደቡ፡፡

በዘመቻው አንድ ዓመት ከ6 ወር ያህል ቆይተው ሲመለሱ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳጋጠማቸው ያነሳሉ፡፡

በ1968 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ወደ ሶዶ ከተማ እንደተመለሱ የወላይታ እርሻ ልማት /ዋዱ/ ድርጅት ሠራተኞችን ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድረው በማለፍ የኤክስቴንሽን መስክ አስተባባሪ ሆነው ተቀጠሩ፡፡

በወቅቱ ከብዙ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ሁለት ሰዎች ብቻ ፈተናውን ሲያልፉ እሳቸው 1ኛ ሆነው ማለፋቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በሥራው ዓመት ሳይሞላቸው የድርጅቱ የፐርሶኔል ሥራ ክፍል ረዳት በመሆን በእድገት ተዛውረው ቀጠሉ፡፡

የዛሬው የሥራ ብስለትና ክህሎት ዩኒቨርሲቲያቸው የነበረው ይህ ድርጅት እንደሆነ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ በድርጅቱ ከ1969 ዓ.ም እስከ 1977 ዓ.ም ድረስ ለ8 ዓመታት ያህል በረዳትነትና በሠራተኞች አስተዳደር ሃላፊነት ሠርተዋል፡፡

የድርጅቱ የሥራ ግንኙነት /ኮሙኒኬሽን/ በእንግሊዝኛ የነበረ ሲሆን የአንድን ሥራ ዘመናዊ የእቅድ አወጣጥና የአፈፃፀም መገምገሚያ ልዩ ልዩ ሞዴሎችንና የአሠራር ዕቅዶችን (ፕሮፖዛሎችን) የማዘጋጀት እውቀትና አሠራር በአግባቡ ያስተማራቸውም ይህ ድርጅት እንደሆነም አልሸሸጉም፡፡

አቶ ነጋሽ በአብዮቱ ጊዜ ከመደበኛ ሥራቸው ጐን ለጐን ፀሐፊና ሊቀመንበር በመሆንም አገልግለዋል፡፡ ነገር ግን ታስረው የተፈቱበት ሁኔታም ተፈጥሮ እንደነበር አንስተዋል፡፡

በ1977 ዓ.ም ከየካቲት ወር ጀምሮ ወደ ደቡብ ቀጠና ግብርና ጽ/ቤት ሐዋሣ ከተማ በዝውውር መጥተው የማሰልጠኛና የህዝብ ግንኙነት ተጠባባቂ ሃላፊ ሆነው ለ4 ዓመታት አገልግለዋል፡፡

በ1981 ዓ.ም የአስተዳደራዊ መዋቅር ማሻሻያ ሲደረግ በዚሁ ሥራ ዘርፍ ወደ ሰሜን ኦሞ አስተዳደር አካባቢ አርባ ምንጭ ከተማ ተዛውረው ለ5 ዓመታት ያህል በሃላፊነት ሠርተዋል፡፡

በአርባ ምንጭ እስከ 1986 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ ቆይተው እንደገና የደቡብ ክልል ግብርና ጽ/ቤት ሲቋቋም የዝውውር እድል አግኝተው ወደ ሐዋሣ ተመልሰው የማሰልጠኛና ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆነው በማገልገል ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ በተጠባባቂ ሃላፊነት ሠርተዋል፡፡

በመቀጠልም ወደ ደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ተመድበው በሠራተኛ አስተዳደር የኤች አይ ቪ /ኤድስ/ ሜኒስትሪሚንግ ቡድን ሃላፊ ሆነው በመምራት እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ ሰፊ አስተዋፅኦ አበርከተዋል፡፡

ጤና ቢሮ እየሠሩ በቆዩበት ጊዜ በሻሸመኔ ፋና ሬዲዮ ጣቢያ “ሊንኪንግ ጃም” የተሰኘ ፕሮግራም ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የአየር ሰዓት ገዝተው ያሰራጩ ነበር፡፡

በተለይም ቅዳሜ ከ10 እስከ 11 ሰዓት ድረስ የዓለም አቀፍ መረጃዎች የትንተና ፕሮግራም ያቀርቡ ነበር፡፡ ፕሮግራማቸው ተወዳጅ፣ በርካታ አድማጮችን የሳበና በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እንዲቸራቸው ያደረገ ነበር፡፡

ይህንን ፕሮግራም በማስፋት ከ2008 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የተለያዩ ፕሮግራሞችን በሙሉ ጊዜ በማዘጋጀት በሳምንት አራት ቀን ከእሮብ እስከ ቅዳሜ ከ7 እስከ 8 ሰዓት ድረስ ከጋዜጠኛ አብይ ይልማ ጋር ያሠራጩም ነበር፡፡

ከሥራው ጋር በተገናኘ የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች በሁለቱም ሚዲያዎች እንግዳ አድርገው በተለያየ ጊዜያት ያቀርቧቸው እንደነበርም አውስተዋል፡፡

አቶ ነጋሽ ወልደኪዳን በሥራ ወቅት የትምህርት ደረጃቸውን ለማሻሻል በቅድሚያ በሐዋሣ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በመቀጠልም በዲላ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ በማስተማር ዘዴ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ማግኘት ችለዋል፡፡

በሥራ ዘመናቸው በበርካታ የሙያ ዘርፎች ብዙ ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ ሁለገብ እውቀት እንዲኖራቸው ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ ስልጠናዎች እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ብዙ ስልጠናዎችን መስጠታቸውንም ያወሳሉ፡፡ የሬዲዮ ፕሮግራም በሚያሠራጩበት ወቅት የእውቅና ሽልማቶችን አግኝተዋል፡፡

ልዩ ባህሪያቸው ምን እንደሆነ ላነሳንላቸው ጥያቄ፡- “ማንበብና መፃፍ ነው” በማለት የተናገሩት ከልጅነታቸው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እየተገበሩት እንደሚገኙ በመግለፅ ነው፡፡

እስከ አሁን ስንት መጽሐፍ አንብበዋል? ተብለውም ተጠይቀው፡- “ከአንድ ሺህ በላይ መጽሐፍት አይበልጡምን?” በማለት ጥያቄያዊ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ምን ያህል መጽሐፍ እንዳላቸው ተጠይቀውም ቁጥሩን እንደማያውቁ ገልፀው የኪራይ ቤት ሲቀይሩ 8 ማዳበሪያ ሙሉ አሽገው መጽሐፍት ብቻ እንደሚጭኑ ተናግረዋል፡፡ ዛሬም እየገዙ ያነባሉ፣ ይፅፋሉ፡፡

ምን አይነት መጽሐፍ ማንበብ እንደሚወዱም ነግረውናል፡፡ የፍልስፍና፣ የታሪክ፣ የልብ ወለድ፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ምርጥ ግጥሞችን ማንበብ ምርጫቸው ነው፡፡

እስከ አሁን ድረስ ካነበቧቸው መጽሐፍቶች ውስጥ በ1960 ዓ.ም በፈረንጆቹ አቆጣጠር የአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ያነቃነቃቸውን ኤያነራንድ መጽሐፍት Atlas Shiragde የተሰኘውንና ሁለተኛ መጽሐፍዋን Founte head የተባሉትን እንደሚያደንቁ ተናግረዋል፡፡

ከልብ ወለዶች፣ ከግጥም፣ ከሥነ ጽሑፍ ሥራዎችም ብዙ የሚያደንቋቸው መጽሐፍት እንዳሉም አብራርተዋል፡፡

ከሃገራችን ድርሰቶች ውስጥ ከታሪክ መጽሐፍት የተክለፃድቅ መኩሪያን፣ ከፍልስፍና መጽሐፍት ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን መጽሐፍን ያደንቃሉ፡፡

በሥራ ላይ ያላቸውን ፍቅር ሲገልፁ፡- “ሥራን በሰዓት ገድቤ አልሠራም” ሲሉ ለሌሎች አርዓያ የሚሆነውን አቋማቸውን ሰንዝረዋል፡፡ ሃሳባቸውን ሲያበራሩት ቢሮም ሆነ ቤት እንደሚሠሩ በመግለፅ ነው፡፡ “አለቃ ምን ይለኛል ብዬ አልሠራም፡፡ ሥራ መሥራት እፎይታና ደስታ ይሰጠኛል፡፡ ደከመኝና ሰለቸኝ የሚሉ ቃላቶችን አላውቅም” ሲሉም አክለዋል፡፡

የወደፊት እቅዳቸውን ሲገልጹ፡- ከ50 ዓመት በላይ የነበራቸውን የህይወት ልምድ ያገናዘቡ የግጥም መድብል መጽሐፍት ማሳተም ቀዳሚው ነው፡፡ በዚህም ከራሳቸው ዘመን ጀምሮ ይህ ትውልድ ትምህርት ያገኝባቸዋል ብለው የሚያስቡትን የግጥም መድብል ለማሳተም በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

ወደ ትዳር ዓለም የገቡት በወጣትነታቸው ሲሆን 4 ወንድና 3 ሴት በድምሩ የ7 ልጆች አባት ናቸው፡፡ ሁሉም ልጆቻቸው ዲፕሎማና ከዚያ በላይ የተማሩ ሲሆን በግልና በመንግስት ሥራ ላይ ተሰማርተው ራሳቸውን የቻሉ ናቸው፡፡

በግል ያላቸውን የህይወትና የንባብ እውቀትን ለማህበረሰቡ የሚያሳውቁበትና የሚያደርሱበት የሬዲዮ ፕሮግራም ካገኙ እውቀቱን የማጋራት ዝግጁነት እንዳላቸው በመግለፅ የሚመለከተው አካል ዕድሉን እንዲያመቻች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡