ዓላማን ያስቀደመች

ዓላማን ያስቀደመች

በአለምሸት ግርማ

ሰዎች በተለያየ መንገድ የሙያ ባለቤት ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚያም አለፍ ሲል ደግሞ በሙያቸው የሀብት ባለቤት ይሆናሉ። ከብዙዎች የህይወት ተሞክሮ እንደምናየው መድረስ ለሚፈልጉበት ደረጃ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጁና ዓላማቸውን ያስቀደሙ ሰዎች ከስኬታቸው እንደሚደርሱ ነው።

በአንፃሩ ራሳቸውን ለማሳደግም ሆነ ለመለወጥ ችላ የሚሉ እንዲሁም ከሚያገኙት ገቢ ከመቆጠብ ይልቅ ዛሬውኑ መደሰትን የሚፈልጉ ሰዎች በህይወታቸው ላይ ለውጥ ማምጣት አይችሉም። ኑሯቸውም አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደኋላ እንደሚባለው ይሆናል። የዛሬዋ የእቱ መለኛ አምድ ባለታሪካችን ወጣት ናት። ነገር ግን ገና ነኝ ቀስ ብዬ እደርሳለሁ ሳትል የህይወትን ውጣ ውረድ ለመጋፈጥ እራሷን በማዘጋጀት ጐዳናውን ጀምራዋለች፡፡ ስራዋን ከጀመረች አጭር ጊዜ ቢሆንም ከጅምሩ ያላት ተሞክሮ ብዙ ወጣቶችን ሊያስምር ይችላል ብለን ስላሰብን ታሪኳን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል፦ 

ትዕግስት ታንቱ በሃዋሳ በጥልፍ ስራ ሙያ የተሰማራች ወጣት ነች። ወደ ሙያው ከመግባቷ በፊት የነበራትን የህይወት ተሞክሮ እንደሚከተለው አጋርታናለች፦

ተወልዳ ያደገችው ወላይታ ሶዶ ከተማ ነው። ቤተሰቦቿ አሁንም ድረስ እዚያው ናቸው። በወቅቱ ሃዋሳ የነበሩ ዘመዶቿ ጋር ለመማር ነው የመጣችው። ዘመዶቿ ጋር በቤተሰብነት ተቀላቅላ መኖር ስትጀምር ዕድሜዋ ገና ለጋ እንደነበር ታስታውሳለች።

ዕድሜዋ ለትምህርት ሲደርስ ሃዋሳ ሀይቅ ትምህርት ቤት ገብታ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች። በመቀጠልም “አላሙራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምራለች።

በዚህ መሃል ግን ወደ አንድ ሙያ በመሰማራት የገቢ ምንጭ ማግኘት እንዳለባት አሰበች። ለዚህም መነሻ ይሆናት ዘንድ በአንድ የሀበሻ ልብስ ቤት ተቀጥራ መስራት ጀመረች። ስራዋ ቤቱን መጠበቅ፤ ደንበኛ ሲመጣ አሳምኖ ትዕዛዝ መቀበልና መሰል ተግባራት ናቸው። በምትሰራው ስራ በወር የሚከፈላት 1ሺ አምስት መቶ ብር ነበር።

ወጣት ትዕግስት ግን በዚህ ስራ ብቻ ተወስና አልተቀመጠችም። በልጅነቷም የራሷ የሆነ ስራ ለመስራት ጉጉት ስለነበራት “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንደሚባለው ሱቁን እየጠበቀች ሙያውን መቅሰም ጀመረች።

በዚህም ከቀን ወደ ቀን ራሷን እያሻሻለች፤ በመቀጠልም አሰሪዎቿን በማስፈቀድ በማሽን መስራት እየተለማመደች እነሱ እንደሚሰሩት መስራት ጀመረች። የሰው ልጅ የሙያ ባለቤት የሚሆንበት መንገድ የተለያየ ነውና ወጣት ትዕግስትም በዚያው አጋጣሚ የጥልፍ ስራ ሙያ ባለቤት መሆን ቻለች።

“ሙያውን እወደው ስለነበር ለመልመድ ብዙም ጊዜ አልፈጀብኝም” የምትለው ወጣት ትዕግስት፥ ከስራው ጋር በቀላሉ መላመድ መቻሏንም ትናገራለች። በእርግጥ ሙያ በፍቅር ከተሰራ ውጤታማ ለመሆን ጊዜ እንደማይፈጅም ተሞክሮዋ ያሳየናል።

በአሁኑ ወቅት በቀሰመችው የጥልፍ ሙያ በሌላ የሀበሻ ልብስ ቤት በተሻለ ደሞዝ ተቀጥራ እየሰራች ትገኛለች። ቃለ-መጠይቃችንንም ስናደርግ ስራዋን በትጋት እያከናወነች ነበር። በስራ ቦታዋ ተጠናቀው የተሰቀሉ ልዩ ልዩ የባህል አልባሳትም ዓይንን የሚማርኩ ናቸው።

የባህል አልባሳት በበዓላት፣ በሰርግ አልያም በምርቃት ወቅት ፈላጊያቸው ቢበዛም በአሁኑ ወቅት የሀበሻ ልብስ ፈላጊዎች ቁጥር ጨምሯል። ይህም አልባሳቱ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በአዳዲስ ዲዛይኖች መሰራታቸው የለባሾች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ። እንደትዕግስት ያሉ የባለሙያዎች እጅ የሀገር ባህል ልብስ እንዲለበስ ምክንያት ሆነዋል ማለት ነው። አሁን በምትሰራበት ቦታ ከ3ሺ አምስት መቶ ብር ጀምሮ እስከ 20ሺ ብር ድረስ የሚያወጡ ልብሶች ይገኛሉ። ሰዎች አቅማቸው በፈቀደው ልክ እና በወደዱት ዲዛይን የሚያዙትን ልብስ አስውባ ትሰራለች።

ከስራዋ በተጓዳኝ የ11ኛ ክፍል ትምህርቷን በርቀት መርሃ-ግብር በመከታተል ላይ እንደሆነችም አጫውታናለች።

ትምህርቷን በርቀት የምትከታተልበት ምክንያት ቀን ቀን በስራ ስለምታሳልፍ ነው። ስራዋን በትኩረትና በፍቅር እንደምታከናውን ያጫወተችን ወጣት ትዕግስት ይህም ነገ መድረስ ለምትፈልግበት ደረጃ ምክንያቷ መሆኑን ትናገራለች።

ቀጣይ እቅድሽ ምንድነው? ብለን ላነሳንላት ጥያቄም እንዲህ በማለት መልሳለች፦

“በትምህርቴ ውጤታማ መሆን እፈልጋለሁ። በተለይም ደግሞ በጀመርኩት ሙያ የራሴን ድርጅት የመክፈት ዓላማ አለኝ። እዚያ ለመድረስ ደግሞ ስራዬን በአግባቡ እየሰራሁ ነው። ከማገኘው ገቢም እቆጥባለሁ።”

አሁን በምትሰራበት ቦታ ከቀድሞ የተሻለ ክፍያ እያገኘች ነው። ከዋና ስራዋ በተጨማሪ ደንበኞች ሲመጡ የማሳመንና ትዕዛዝ የመቀበል ስራ ስትሰራ ተጨማሪ ክፍያንም ታገኛለች። ጥረት፣ ቁጠባ፣ የግል ዕቅድና ዓላማ ካለ ሴቶች ያሰቡበት መድረስ ይችላሉ ስትልም ትናገራለች።

ሴቶች በማንም ላይ ጥገኛ መሆን የለባቸውም። ባገኙት ዕድል በመጠቀም ራሳቸውን መለወጥ መቻል አለባቸው። እኔ የወደ ፊት ዕቅዴ ተሟልቶልኝ ራሴን ሳልችል ስለትዳር አላስብም። ምክንያቱም አንደኛ የተሻለ ኑሮ መኖር ስለምፈልግ ሲሆን ሌላው በማንም ላይ ጥገኛ መሆን ስለማልፈልግ ነው በማለት ስለህይወት ያላትን አቋም ትናገራለች።

በስራ ህይወት ያሰቡበት ለመድረስ ብዙ ውጣ ውረዶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታወቃል።  በየትኛውም የስራ መስክ ቢሆን ነገሮች አልጋ በአልጋ እንዲሆኑ መጠበቅ፤ ለውጥ ለማምጣት አያስችልም። የተሻለ ህይወት ለመኖር ስራን ሳይመርጡ መስራትና የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጥበብ ማለፍ ይጠይቃል።

እንዲሁም ስራን ከትንሹ በመጀመር እና ሙያን ከሌሎች በመቅሰም ስኬታማ መሆን እንደሚቻልም የወጣት ትዕግስት ተሞክሮ ያሳየናል። ምናልባትም ኮሌጅ ገብታ መሰልጠን እንዳለባት በማሰብ፤ አሊያም ከሌሎች ለመልመድ ሰዎች ምን ይሉኛል የሚል ፍርሃት ቢኖርባት ኖሮ ዛሬ የደረሰችበት ቦታ ለመድረስ አትችልም ነበር።

እሷም ከተሞክሮዋ በመነሳት ለሴቶች እንዲህ ስትል ትመክራለች፦

ሙያ በተለያየ መንገድ ይገኛል። ነገር ግን እንደ እኔ ያሉ ወጣት ሴቶች በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ሙያን ቢማሩ ጥሩ ነው። እኔ በልምድ የሙያ ባለቤት ሆኛለሁ። በዚያም ቀድሞ ከማገኘው የተሻለ ገቢ ማግኘት ችያለሁ። ለቀጣይ ህይወቴም ትልቅ ነገር ማቀድ ጀምሬያለሁ። ይሔ ሁሉ መሆን የቻለው ከሰዎች ተጠግቼ ሙያ በመቅሰሜ ነው። ስለዚህ ሴቶች ራሳቸውን ለመቻል፤ የተሻለ ህይወትን ለመምራት እና የማንም ጥገኛ ላለመሆን በቅድሚያ ባገኙት አጋጣሚ ተጠቅመው ራሳቸውን መቻል አለባቸው። ለዚህ ደግሞ አንዱ መንገድ ስራን ሳይንቁ መስራት እንዲሁም ከእኛ ከሚሻሉ ሰዎች ሙያ በመቅሰም ነው።

ስኬታማ ባለሙያ ለመሆን በርካታ ፈተናዎችን ማለፍ፤ መውደቅ እና መነሳት እንዲሁም የማይቋረጥ ትጋት ይጠይቃል። የራስን የተለየ ፍላጎት፣ ልዩ ችሎታ እና ልምድ ለይቶ ማወቅ ለስኬት ከሚያደርሱ መንገዶች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው።

በራስ ጥረት የተገኘ ውጤት ለሌላ አዲስ ስኬት ያነሳሳል። በእያንዳንዱ የስኬት ምዕራፍ ውስጥ ውጤታማ ስራዎችን ለማስቀጠል ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል። 

ስራ ህይወትን ይለውጣል። ለውጥ ደግሞ የሚጀምረው ከውስጥ ነው። ሰዎች ለመለወጥ መስራት እንዳለባቸው ሊያምኑ ይገባል። ከትንሽ ነገር ተነስቶ ትልቅ ነገርን ማሰብ እንደሚቻል እንደትዕግስት ካሉ ወጣቶች ሊማሩ ይገባል።