የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መንግስት በከተማና በገጠር ለጀመራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ሞተሮች ናቸው – አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)

የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መንግስት በከተማና በገጠር ለጀመራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ሞተሮች ናቸው – አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)

‎ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መንግስት በከተማና በገጠር ለጀመራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ሞተሮች ናቸው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

‎በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ(ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በአርባምንጭ ፖሊ ቴክኒክ ሳታላይት እንስቲትዩት የሚከናወኑ ተግባራትን ጎብኝቷል፡፡

‎የአርባ ምንጭ ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲን አቶ በዛብህ ባርዛ እንዳሉት፤ ኮሌጁ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በገጠርና በከተማ ለሚከናወኑት የልማት ፕሮጀክቶች በማቅረብ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማስመዝገብ እየሰራ ይገኛል።

‎መንግስት ለኮሌጁ እያደረገ ያለው ድጋፍ ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸው፤ ኮሌጁ በመፍጠርና በመቅዳት ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

‎የጋሞ ዞን ሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሐኪሜ አየለ፤ በኮሌጁ እየተከናወኑ ያሉ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ለወጣቱ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ግብዓቶችን ለማሟላት ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

‎ለማህበረሰቡ የሚጠቅሙ አዳዲስ ማሽነሪዎችን በማምረት ረገድም ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አብራርተዋል።

‎የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ኃላፊ አቶ በዛብህ ገበየሁ፤ ኮሌጆች ቴክኖሎጂን በመፍጠርና በመቅዳት ሀገሪቱ በገጠርና በከተማ ለጀመረችው የለውጥ ጉዞ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል።

‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)፤ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች ለሀገር ዕድገት የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዶክተር አበባየሁ ታደሰ፤ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሀገሪቱን ብሎም የክልሉን ብልፅግና የሚያሳልጡ የሰው ሃይል የሚፈሩባቸው ተቋማት ከመሆናቸውም ባሻገር መንግስት በከተማና በገጠር ለጀመራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች በጥራት ግብዓት እያቀረቡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

‎ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን