የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆናቸው ከድንገተኛ ህክምና ወጪ እንደታደጋቸው የይርጋጨፌ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ
ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆናቸው ከድንገተኛ ህክምና ወጪ እንደታደጋቸው በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።
የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት በበኩሉ የማአጤመ አባላት የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጿል።
አቶ ደሳለኝ ፈይሳ እና ወ/ሮ ደብሪቱ ደምሴ በወረዳው የኦሮበተላ እና የጋርቦታ ቁጥር ሁለት ቀበሌ ነዋሪዎች እና የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላት ሲሆኑ፥ በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆናቸው ከድንገተኛ ህክምና ወጪ እንደታደጋቸው ተናግረዋል።
ሌላኛው በወረዳው የአርቻ ቀበሌ ነዋሪ እና የቀድሞ የሰራዊት አባል አቶ አለሙ ደያሶ እንደተናገሩት የሀገር ህልውና ለማስጠበቅ በዘመቱበት ወቅት የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው በመገንዘብ መንግሥት ያዘጋጀውን ነጻ እድል በመጠቀም የማአጤመ አባል ሆነው እራሳቸውም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው የነጻ ህክምና አገልግሎት እያገኙ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
አሁን ላይ ወደ ጤና ተቋማት ለህክምና በሚሄዱበት ጊዜ የጤና ተቋማት ባለሙያዎች በጥሩ ሁኔታ እያስተናገዱአቸው እንደሆነ ያነሱት ነዋሪዎቹ፥ በጤና ተቋማት አልፎ አልፎ የሚስተዋለው የመድኃኒት እጥረት ችግር እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።
በይርጋጨፌ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ አበራ እንደተናገሩት፥ የወረዳው ነዋሪዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባል መሆን ያለውን ፋይዳ በመረዳት አባል እንዲሆኑ ለማድረግ ከጤና ኤክስተንሽን ባለሙያዎችና ከሴቶች ልማት ቡድን ጋር በቀናጀት ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው ብለዋል።
በዚህም ከዚህ ቀደም ከ3ሺህ በታች የነበረው የአባላት ቁጥር ከጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም ጀምሮ በንቅናቄ በመሠራቱ አሁን ላይ መንግስት ድጎማ ከሚያደርግላቸው 8 ሺህ 730 እማወራ እና አባወራ ጭምር የአባላት ቁጥር 17 ሺህ 554 መድረሱንና የአባላት ቁጥር የማሳደግ ተግባራት በተቀናጀ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተካለኝ ጥላሁን በበኩላቸው በወረዳው ከጤና አጠባበቅ ሥራዎች ጋር የተያያዙ በመደበኛ እና በንቅናቄ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አክለውም የመድኃኒት እጥረት የተስተዋለው እንደ ሀገር የመድኃኒት ዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ሲሆን አሁን ላይ መሻሻሎች መኖራቸውንና ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ኢኒሼቲቭ የሆነው ቢያንስ በወረዳው አንድ የማህበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት መከፈት እንዳለበት በተቀመጠው አቅጣጫ መነሻ ከወረዳው አስተባባሪ እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በወረዳው ሐሩ ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ መድኃኒት ቤት መክፈታቸውንና በቀጣይ በሌሎች ቀበሌዎች ለማስፋት ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች መንግስት በከተማና በገጠር ለጀመራቸው የልማት እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ሞተሮች ናቸው – አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)
መንግሥት የብሔረሰቦች ባህል፣ ቋንቋና መልካም ዕሴቶች እንዲታወቁና እንዲጎለብቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተገለፀ
ሰላምን ለማጽናት የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ሚና መወጣት ሲችል ነው – የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ