ለሀገራችን ተስፋ የሰጠው ስምምነት

በፈረኦን ደበበ

ሥቃይና መከራ እንደሚያልፍ ሰሞኑን የተገኘው ዕድል ሌላ ማሳያ ነው። በታሪክ ትልቅ የነበረችው ሀገር ወደ ቀድሞ ታላቅነቷ ለመመለስ የሚያስችላት እና ወደ ዓለም የምትወጣበት የባህር በር አጥታ መቆየቷ ማንንም ሲያሳዝን ቆይቷል፡፡

እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት እንደ ወንጀል የሚታይበት ጊዜ ሁሉ አልፎ አሁን ሀገራዊ አጀንዳ መሆኑ ሲያስደስት መንገዱም ተመቻችቶ ከሰሞኑን ወደ መግባባት ተደርሷል፡፡ ድርብ ደስታን ፈጥሯል።

ብዙ ሀገራት በተፈጥሮ የባህር በር ኖሯቸው ካለምንም ውጣ ውረድ የዜጎቻቸውን መሠረታዊ ፍላጎት ሲያሟሉ ኢትዮጵያ ግን ይህን ያህል የህዝብ ቁጥር ይዛ ለጎረቤቶች ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈለች መጠቀሟ ፍትሀዊ አልነበረም፡፡

ችግሩን የተገነዘበው መንግሥት ዘዴ ማፈላለግ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ እንቅፋቶቹን ሁሉ በብስለት እያለፈ ወደ ውጤት እያደረሰ ይገኛል፡፡ በቱርኪዬ መንግሥት አማካይነት ከሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፑብሊክ መንግሥት ጋር ሰሞኑን የተደረሰው ስምምነት በር ከፋች፣ ተስፋ የሚያለመልምና የጋራ ተጠቃሚነትንም የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡

ሀገራችንን እየገጠማት ያለውን ችግር ገልጸን ጥያቄ ያቀረብንላቸው ጎረቤት ሀገራት ጀርባ በሰጡበት ጊዜ ፊታችንን ወደ ሶማሌ ላንድ አዙረን ባለፈው ዓመት ታሪካዊ የሆነ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመን ነበር፡፡

እስከ 50 ዓመታት የሚቆየው ይህ ስምምነት ሀገራችን ወደብና ክብሯን ማረጋገጥ የሚያስችል ባህር ኃይል ለመገንባት መፍቀዱ አስደሳች ቢሆንም በቅርቡ በግዛቲቱ በተካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ከተቃዋሚ ወገን የተወዳደሩት አብዱራህማን መሀመድ አብዱላሂ አሸንፈው ሥልጣን መያዛቸው እንቅፋት እንዳይፈጥር በጥበብ መያዝ ያስፈልጋል።

ተመራጩ ኘሬዝዳንት ኢትዮጵያ ወደ ግዛቲቱ አትግባ የሚል አቋም ባይኖራቸውም መጀመሪያ የተካሄደው የመግባቢያ ስምምነት ግልጸኝነት ይጎድለዋል በማለት ፊታቸውን ወደ ዓለም ማህበረሰብ ማዞራቸው ጥርጣሬን ይፈጥራል።

ከዚህ ባሻገር የሶማሊያ ፌዴራላዊ መንግሥት ሲያሰማ ከነበረው ተቃውሞ ጋርም ተያይዞ የመግባቢያ ስምምነቱ ሀገራችንን ወዳልታሰበ ውጥረት ውስጥ ከቷት ነው የቆየው። ሶማሊያ የሀገራችን ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብጽና እንዲሁም ኤርትራን ሁሉ በመጋበዝ አፍራሽ ድርጊቶችን ስትፈጽም ስለነበረ፡፡

የኋላ ኋላ ግን ነገሩ “እሱ የከፈተውን ጎሮሮ ማንም አይዘጋውም” እንደተባለው አስደሳች ሆኗል፡፡ ውጣ ውረዱ ቀርቶ የተስፋ ብርሃን በሀገራችን እንዲፈነጥቅ አድርጓል፡፡ በትንሹ የተጀመረው ሥራ አሁን ማከናወን እንድንችልም በር ከፍቷል፡፡

ተስፋ የተበሰረው ሰሞኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሴን ሼክ መሀሙድ ጋር በአንካራ ባደረጉት ስምምምነት ነው። ብዙ መገናኛ ብዙሀን “ሰጥቶ መቀበል” ብለው የሚገልጹት ይህ ስምምነት ለሁለቱ ጎረቤታሞች ጥቅም የሚሰጥ ነው፡፡

ሀገራችን እያቀረበች ያለው የባህር በር ጥያቄ በአንድ በኩል በሶማሊያ የታጣው ሀገራዊ የአንድነት ችግር ተጠቃሽ ሲሆን ሁለቱ ሀገራት ደግሞ ከመነጣጠል ይልቅ በጋራ ከሠሩ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት ይችላሉ የሚለው በአሸማጋዮች ተወስዷል፡፡

ለሀገራችን ሌላው መልካም አጋጣሚ ወዳጅ የሆኑት የቱርኪዬው ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣሂብ ኤርዶጋን ጉዳዩን መያዛቸው ሲሆን ሀገራችንን በዓለም ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ኖሯት ብቸኛዋ ወደብ አልባ በማለትም ጠርተዋታል። ችግሩን እንዲፈቱ እያሉ ቀጥታ ለወንድም ሼክ መሀሙድ ጥያቄ ማቅረባቸውም ለሀገራችን ባለውለታነታቸውን ያረጋግጣል፡፡

አፍሪካ ኒውስ፣ አልጀዚራ እና ሌሎች የመገናኛ ብዙሀን እንደዘገቡት ከሆነ ስምምነቱ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጠውን የንግድ ግንኙነቱን ለማጠናከር ሲረዳ፤ ለኢትዮጵያ ደግሞ “አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ዘላቂ” የባህር በር አገልግሎት ያስገኝላታል ተብሏል፡፡

ለሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፑብሊክ መንግሥትም የሉዓላዊነት ሥልጣንን ያጎናጽፋል የተባለለት ይህ ስምምነት ከሚቀጥለው የካቲት ወር ጀምሮ ወደ ዝርዝር አፈጻጸም ውይይት የሚገባ ሲሆን እስከ አራት ወራት የሚቆየው ውይይትም ለሁለቱ ሀገራት ጠቃሚ ነገሮችን እንደሚያስገኝ ተነግሯል።

የቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣሂብ ኤርዶጋን በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ሠላማዊ ትብብር ለማስጀመር የመጀመሪያ ምዕራፍ ብለው የጠሩት ስምምነት በመጨረሻ የባህር በር ለሌላት ኢትዮጵያ ዕድል እንደሆነ ጠቅሰው፤ በዕለቱ የተካሄደውንም ውይይት አድንቀዋል ችግሩ እንዲፈታ ለሶማሊያው ፕሬዝዳንት አደራ በማለት፡፡

የተደረሰው ስምምነት “የወደፊት እንጂ ያለፈውን ችግር እንደማይመለከት” ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ ለእኛ ጠቃሚ የሆኑት እነዚህ ሁለቱ ወዳጅ ሀገራት ወደፊት የሚገነቡበትን መርህ ይቀርጻል በማለትም ነው የተናገሩት፡፡

ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ያላቸው የሀሳብ ልዩነቶችና አወዛጋቢ ነገሮችን ወደ ጎን በመተው በቁርጠኝነት ወደ ፊት መገስገስና ለጋራ ብልጽግና መሥራት እንደሚገባም ተመልክቷል፡፡

በቱርክዬ ዋና ከተማ አንካራ ከተደረገው ከዚህ ውይይት በኋላ ሁለቱ ሀገራት ለአፈጻጸም የሚረዱ “ቴክኒካዊ” ውይይቶችን እስከ ቀጣይ የካቲት ወር መጨረሻ ማጠናቀቅ ሲገባቸው ቀሪ ጉዳዮች ካሉም በራሳቸው አልያም በቱርኪዬ ድጋፍ ማከናወን እንደሚችሉ ከመግባባት ተደርሷል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ባለፈው ዓመት የተከሰተውን ያለመግባባት ለማስቀረት ሥራዎች ሲሠሩ እንደቆዩ ገልጸው ኢትዮጵያም የባህር በር ለማግኘት ያቀረበችው ጥያቄ ሠላማዊና ጎረቤቷን የሚጠቅም እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር በገባችው እሰጥ አገባ ምክንያት የህልውና አደጋ የተጋረጠባት ሶማሊያ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ደስታቸውን ገልጸዋል፤ ስምምነቱ የተከሰተውን ችግር መፍታት እንደሚያስችልና ለዚህም ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ጋር ለመሥራት መዘጋጀታቸውን በማስታወቅ፡፡

ሀገራችን የቀደምት ፖለቲካ ሥልጣኔና የባህር በር ባለቤነቷን በታሪክ አጋጣሚ ማጣቷ ሲያሳዝን ያሁኑ ስምምነት ደግሞ ቀደም ብለው የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች የፈጠሩትን ስህተት ሁሉ በማካካስ ታላቅነቷን በአጭር ጊዜ ሊያበሥር ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የሉዓላዊነታችን አንድ ማሳያ የሆነውን ባህር በራችንን ስናገኝ ወደ አካባቢው ዘልቆ የገባውን የግብጽና የኤርትራ ጦርን በማስወጣት ሀገራችን በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ላይም የነበራትን ሚና ማጠናከር ስለሚያስችል በመልካም ገጽታ ይታያል፡፡

አሁን በሶማሊያ የተከሰተውን ፖለቲካዊ ቀውስ አረጋግቶ የተፈለገውን ሀገራዊ ሉዓላዊነት ለማስከበርም እንደ ቱርኪዬ ካሉ አጋር ሀገራት ጋር መሥራት ያስችለናል ማለት ነው፡፡