ኢና ሞዲጃ – ከድምጻዊነት ባሻገር
በአንዱዓለም ሰለሞን
የልጅነት ምኞቷ ሙዚቀኛ መሆን ነበር። በእርግጥም ይህን አሳክታለች፡፡ በሙያዋ በአለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅ ዝነኛም ሆናለች፡፡
ዝናዋ ግን ከሙዚቃው ያለፈ ነው። ባለብዙ ሙያዋ አርቲስት፣ ሞዴል፣ አክቲቪስት፣ የሴቶች መብት ተሟጋች ብሎም የዓየር ንብረት ለውጥንና በረሀማነትን ከመከላከል አንጻር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አምባሳደር ነች – የማሊዋ ድምጻዊ ኢና ቦኩም፡፡
እ.ኤ.አ ግንቦት 19 ቀን፣ 1984 የተወለደችውና ኢና ሞዲጃ በሚለው ስሟ የምትታወቀው ይህች ድምጻዊ፣ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ካፈራቻቸው በርካታ ስመ ጥር ድምጻዊያን መካከል አንዷ ነች፡፡
ከዲፕሎማት ቤተሰብ የተገኘችው ድምጻዊዋ፣ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደተለያዩ ሀገራት መጓዟ ብዙ ዓይነት ባህሎችን የማወቅ እና የተለያዩ ሙዚቃዎችን የማድመጥ እድልን ፈጥሮላታል፡፡ ይህም ለህይወቷ ሆነ ለሙዚቃ ሥራዋ የተለየ ለዛና ቀለም ሰጥቶላታል። በአንድ ወቅት በሰጠችው ቃለ መጠይቅ፣ ይህን አስመልክታ ስትናገር እንዲህ ብላ ነበር፡-
“ከቤተሰቦቼ ሰባት ልጆች ውስጥ እኔ ስድስተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ከእኛ ጋር አብረው የሚኖሩ 3 የአክስቴ ልጆችም ነበሩ፡፡ አስር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ባሉበት ቤት ውስጥ ነው ያደኩት፡፡ ይህ ደግሞ ቤታችንን አስደሳችና በፍቅር የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
የአምባሳደር ልጅ መሆኔ ደግሞ ከቤተሰቦቼ ጋር ወደተለያዩ ሀገራት የመጓዝ እድል ፈጥሮልኛል፡፡ ያደኩት በማሊና በጋና ነው፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ደግሞ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን ለመጎብኘት ችያለሁ፡፡ ከዚህ ባሻገርም ገና በልጅነት እድሜዬ ወደ አውሮፓ ለመሄድ ችያለሁ፡፡ ይህም ሆኖ ባማኮ ከባህል፣ ከሙዚቃ እና ከፎቶግራፍ ጥበብ አንጻር ከማንነቴ ጋር የሚገለጸውን የህይወቴን መንገድ የቀየስኩባት ናት፡፡”
የጥበብ በተለይም ደግሞ የታዋቂ ድምጻዊያን መፍለቂያ የሆነችው የትውልድ ሀገሯ ማሊ፣ በእርግጥም ተዘዋውራ ካየቻቸው ሀገራትም በላይ ለሙዚቃ የተለየ ፍቅር እንዲኖራት አድርጋታለች፡፡ ከዚህ አንጻር፣ ሳሊፍ ኬታ፣ ኦማ ሳንጋሬ አማዱ ባጋዮኮን የመሳሰሉ ዝነኛ የማሊ ድምጻዊያን ተጽዕኖ ያሳደሩባት ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡ ያም ሆኖ የራሷ የድምጽ ቃና ያላት ከመሆን ባሻገር ከቀደምት የሀገሯ ድምጻዊያን በተለየ የሙዚቃ ስራዎቿን በፈረንሳይኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች ጭምር በመስራት ትታወቃለች፡፡ ይህን አስመልክቶ በሰጠችው አስተያየትም፡-
“በእርግጥ ሙዚቀኛ የመሆን ፍላጎት ያደረብኝ ገና በልጅነቴ፣ የአስራ አራት ዓመት ታዳጊ ሳለሁ ነበር፡፡ በመሆኑም ሙዚቃ መማር እፈልግ ነበር፡፡ ከእኛ ቤተሰብ ውስጥ በሙዚቃም ሆነ በሌላ የኪነ ጥበብ ዘርፍ የሚሰራ ባለሙያ ስላልነበር ሙዚቃን ከሌሎች ሰዎች መማር ነበረብኝ፡፡ ከድምጻዊ ሳሊፍ ኬታ ጋር የተገናኘሁት ገና በልጅነቴ ነበር፡፡ እሱም የመጀመሪያ አሰልጣኜ እና እንደ ሀቢብ ኮይቴ ካሉ ድምጻዊያን ጋር ያስተዋወቀኝ ነው፡፡ በወቅቱ በባማኮ ዝነኛ ከነበረው የራይል ባንድ ጋር ለመገናኘትም ችዬ ነበር። እናም እነርሱ ሙዚቃ ሲለማመዱና ሲሰሩ አብሬያቸው እሆን ነበር፡፡ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ሳልገባ በዚህ መልኩ ነበር ከታላላቆቹ ድምጻዊያን ስለ ሙዚቃ የተማርኩት፡፡
መጀመሪያ ሙዚቃ መጫወት የጀመርኩት በማሊ፣ በባምባራ ቋንቋ ነበር፡፡ እያደኩ ስሄድ ቤተሰቦቼ የተለያዩ ሙዚቃዎችን እንዳደምጥ አደረጉኝ፡፡ ወላጆቼን ጨምሮ ወንድሞቼና እህቶቼ የተለያየ የሙዚቃ ምርጫ ነበራቸው። በዚህ የተነሳ እኔም የተለያዩ ሙዚቃዎችን እየሰማሁና እየተማርኩ ነበር ያደኩት፡፡ ሙዚቀኛ ስሆንም ከእነዚህ ታዋቂ ድምጻዊያን የተማርኩት እንዳለ ሆኖ የራሴን መንገድ ለመከተልና በራሴ የድምጽ ቃና ለመዝፈን አልተቸገርኩም፤ ምክንያቱም እኔ የሌላኛው ትውልድ አካል ነኝና፡፡ ከእነርሱ እየተማርኩ ራሴን ለመሆንና የራሴን መንገድ ለመከተል ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ እነርሱም እስከ አሁንም ድረስ ይደግፉኛል፡፡ እኔም ምንጊዜም ነገሮችን ለማወቅና ለመረዳት ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ከብዙዎቹ ጋር በጥምረት በመስራቴም ደስተኛ ነኝ፡፡ የሙዚቃ ህይወት ጉዞዬ የተቃኘው በዚህ መልኩ ነው፡፡” ብላለች፡፡
በሙዚቃ ስራዎቿ በዓለም አቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፈችው ኢና ስራዎቿ በአፍሪካም ሆነ በሀገሯ ስላሉ ማህበራዊ ጉዳዮች አውስታለች፡፡ ለአብነት “አንድ መቶ ማይሎችን ውሀ ለማግኘት እጓዛለሁ” እያለች ያቀነቀነችበትና በሀገሯ ውሀ ለማግኘት ያለውን ውጣ ውረድና መንግስትም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው የገለጸችበት “ዎተር” የሚለው ስራዋ ይጠቀሳል፡፡
ከምንም በላይ ግን፣ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በተባበሩት መንግስትት ድርጅት አምባሳደር በሆነችበትና “UNCCD” ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመሆን በሚሰራው “ዘ ግሬት ግሪን ዋል” በተሰኘው ፕሮጀክት ላይ የምታደርገው ተሳትፎ አድናቆት የሚቸረው ነው፡፡ ይህን አስመልክቶ በአንድ ወቅት ለቀረበላት ጥያቄ በሰጠችው አስተያየት እንዲህ ብላለች፡-
“ይህ በጣም የወደድኩት ፕሮጀክት ነው፡፡ በህንድ ሳለሁ ነበር አንድ ጓደኛዬ ስለ ሁኔታው ደውሎ የነገረኝና ፍቃደኛ ከሆንኩ እንድሳተፍ የጠየቀኝ፡፡ ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት ስለሆነ ያለማመንታት ነበር የተስማማሁት። የራሴን አስተዋጽኦ ማበርከት እፈልጋለሁ፡፡ እኔ በሳህል (በረሀ) ነው የበቀልኩት፡፡ እናም ስለ ሳህል ገጽታ፣ ውበት እና እውነታ ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ2017 የፕሮጀክቱ አካል የሆኑና በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ገጠራማ አካባቢዎችን ተዘዋውሬ ተመለከትኩ፡፡ ይህም በአካባቢዎቹ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ጊዜዬን በማሳለፍ ስለእነርሱ ለማወቅ አስቻለኝ። ይህን ያደረኩበት ምክንያትም እንደ አንድ አምባሳደር ዝም ብዬ ስለ እነርሱ ማውራት ሳይሆን፣ በቦታው ተገኝቼ ኑሯቸውን ማየት ስለነበረብኝ ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ዶክመንተሪ ፊልም ለመስራት ወሰንን፡፡ ይህ ደግሞ ሳህልን በጉዞ ለማካለል (ዞሮ ለማየት) ብቻም ሳይሆን በዚያ የሚኖሩ ሰዎችን ለማግኘትና ታሪካቸውን ለመናገር የሚያስችል ነው፡፡ ታላቁ ፕሮጀክትም ይህን መሳይ ነው፤ 8 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍነውን ቦታ አረንጓዴ በማልበስ፣ ከሴኔጋል እስከ ጅቡቲ ያለውን 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መልሶ ማልማት!”
ዝነኛዋ ድምጻዊ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ባሻገር ከጾታዊ ጥቃት አንጻር ህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስጨበጥና ለውጥ ለማምጣት የተለያዩ ተግባራትን አከናውናለች፡፡ ጾታዊ ጥቃትን አስመልክቶ ከፍተኛ ተደማጭነትን ያተረፉ አራት የሙዚቃ ስራዎችንም ሰርታለች፡፡ ይህን አስመልክታ ስትናገርም፡-
“ስለ ሴቶች በአደባባይ መናገር የጀመርኩት የ19 ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ከማሊ ወደ አውሮፓ በማምራት በዚያ ያለውን ነገር በንጽጽር በማየቴ ነው፡፡ ስለ ሁኔታው (በሴቶች ላይ ስለሚፈጸም ጥቃትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት) አውቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም ወላጆቼ ስለ ጉዳዩ እንድገነዘብ አድርገውኛል፡፡ እነርሱ በሴቶች ላይ የሚፈጸምን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ይቃወሙ ነበር፡፡ እናቴ የሴቶችን እኩልነትና በሴቶች ላይ የሚፈጸምን ጥቃት አስመልክቶ ታስተምር ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ቤተሰብ መካከል በማደጌም የ19 ዓመት ልጅ ሳለሁ በዙሪያዬ ካሉ ሌሎች ሴቶች የተለየሁ እንደሆንኩ ይሰማኝ ነበር፡፡
እኔ ራሴ አምስት እህቶች አሉኝ፡፡ ይህን ነገር መስራት ስጀምር፣ የተለያዩ ጾታዊ ጥቃቶች መኖራቸውንና ስለ እነዚህ ነገሮች ሊነገር እንደሚገባ ተረድቻለሁ፡፡ በብዙዎች ዘንድ ይህ የሚያሳፍር ነገር ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡ በዚህ ረገድ ቤተሰቦቼ በጣም ያግዙኝ ነበር፡፡ በእርግጥም እነርሱ ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደምችል እየነገሩ ነው ያሳደጉኝ፡፡ እናም ከ20 ዓመታት በፊት የጀመርኩትን ስራ አሁንም አላቋረጥኩም፡፡ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን ጾታዊ ጥቃትን አስመልክቶ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራሁ ነው፡፡ ይህ የሴቶች ብቻ ጉዳይና በሴቶች ብቻ የሚሰራ ስራ ሳይሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በጋራ በመሆን ሊያወግዘው የሚገባ ነገር ነው፡፡ አሁን ሴት ልጅ አለችኝ፡፡ ልጄ ከዚህ ስጋት ነጻ በሆነ ሁኔታ እንድትኖር እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ ስልም ማድረግ ያለብኝን ነገርና መክፈል የሚገባኝን መስዋዕትነት ሁሉ እከፍላለሁ” ብላለች፡፡
More Stories
“ማንበብና መፃፍ ልዩ ባህሪዬ ነው” – ነጋሽ ወልደኪዳን /ገጣሚ፣ ጋዜጠኛና ሐያሲ/
ዓላማን ያስቀደመች
ለሀገራችን ተስፋ የሰጠው ስምምነት