“እስከ ጥር ወር መጨረሻ ጥንቃቄ ይፈልጋል” – አቶ ከፍያለው አየለ

“እስከ ጥር ወር መጨረሻ ጥንቃቄ ይፈልጋል” – አቶ ከፍያለው አየለ

በገነት ደጉ

የበጋው ፀሐያማ እና ነፋሻማ አየር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መጥቷል፡፡ ሆኖም ግን ከተለመደው ለየት የሚሉ ንፋስና ቅዝቃዜ አዘል አየር፤ ቀትር ላይ ደግሞ ከበድ ያለ ሙቀት  ከበጋው አየር ለየት ብሎ ተስተውሏል፡፡

ሰሞኑን ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ያወጣው ቅድመ ትንበያ ማስጠንቀቂያ እንደሚያመላክተው ቅዝቃዜ፣ ውርጭ እና ፀሀያማ አየር  እስከ ጥር ወር መጨረሻ ሊቀጥል ይችላል፡፡  

ህብረተሰቡም ይህንን ተከትሎ አለባበሱን ማስተካከልና ከጤናው ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ ከሚችሉ የጤና እክሎች እራሱን መጠበቅ አለበት፡፡ በእንሰሳት ብሎም በምርት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት  መረጃዎችን ማውጣቱ ይታወሳል። 

እኛም ከዚህ ወር ጀምሮ ያለው የአየር ትንበያ በሰዎች ጤና ላይ ሊያደርሱ የሚችሉ ተግዳሮቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በኢትዮጵያ ሜትዎሮሎጂ አገልግሎት የሃዋሣ ማዕከል የሥራ ኃላፊዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

የሲዳማ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የሜትዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከፍያለው አየለ  በበጋ ወቅት እስከ ጥር ማለቂያ ድረስ ፀሐያማ፣ ውርጭ እና ቀዝቃዛማ አየር  ሊቀጥል እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በአራቱም ክልሎች  እስከ ጥቅምት ወር  ዝናባማ የአየር ሁኔታ እንደነበር ያስታወሱት የማዕከሉ ኃላፊ ከታህሳስ  እስከ ጥር ወር ድረስ ደግሞ የሌሊት እና የማለዳው ቅዝቃዜ ከሌሎቹ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ቅዝቃዜው የሚጎላበትና ቀን ላይ ያለው ሙቀት ከፍ ብሎ የሚታይበት ወቅት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በማዕከሉ ቅዝቃዜው መደበኛ ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን አልፎ አልፎ ግን ከመደበኛው በታች የሚሆን በመሆኑ በቀጣይ ቀሪ ሁለት ወራት /ታህሳስ እና ጥር/ ደረቅ እና ከአየር ግፊት ጋር ተያይዘው ከፍተኛ የሆነ የማለዳ ቅዝቃዜ እንደሚቀጥል  አንስተዋል፡፡

በተለይም በከፍተኛ እና ተራራማ አካባቢዎች በሲዳማ ክልል፣ ጌድኦ ዞን፣ ሀዲያ ዞን፣ ዱራሜ ከተማ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  ከፍታ ቦታዎች፣ ወላይታ ዞን አካባቢ ከፍተኛ የማለዳ ቅዝቃዜ ሊኖር እንደሚችል ነው ያስታወቁት፡፡

ከዚህም ባሻገር በተጠቀሱ ቦታዎች  አልፎ አልፎ ውርጭ  አዘል የአየር ሁኔታዎች  ስለሚኖሩ በሰውም ሆነ በእንሰሳት ጤና ላይ ጉዳት ሊያደረስ ስለሚችል ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ቅዝቃዜው በጣም ዝቅ ብሎ ከዜሮ ድግሪ ሴልሽየስ በታች ሲሆን በቤትም ሆነ በዱር እንሰሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል የሚመለከተው አካል የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ 

የተጠቀሱት ወራት እስኪያልፉ ድረስ ህብረተሰቡ የሌሊት እና የማለዳ ልብስ አለባበስን ማስተካከል እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ 

በተመሳሳይ የቤት እንሰሳት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል በጥዋት ከቤት ከማውጣት ይልቅ ማቆየቱ ተመራጭ እንደሆነ መክረዋል፡፡

በተለይ ውጪ ላይ የሚያድሩ እንሰሳት ሊሞቱ  እንደሚችሉ ያስረዱት አቶ ከፍያለው ህብረተሰቡ  ለእንሰሳቶቹ ሙቀት የሚያገኙበትን መንገድ ቢያመቻቹ  መልካም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

በአብዛኛው አካባቢዎች የአገዳ  ሰብሎች አጨዳ ላይ ያሉ ሲሆን የቀኑ ሙቀት እና የሌሊት ቅዝቃዜው  የምርት ብክነት እንዳይኖር እንደሚያግዝ ጠቅሰው  በተለይም በእድገት ላይ ባሉ ሰብሎች ላይ  ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ግን ጠቁመዋል፡፡ 

ከጤናው አንፃር ያለፉት ሁለት ወራት የወባ በሽታ  ስርጭት ላይ ጫና ማሳደሩን  ያነሱት የማዕከሉ መሪ ስራ አስፈፃሚ የባለፈው እርጥበታማ ወራት ተጽዕኖአቸው የሚታየው አሁን በመሆኑ የጤናው ሴክተር እየተከታተለ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ የከፍተኛ ሙቀት እና ቅዝቃዜው መፈራረቅ በሰዎች ጤና ላይ በአንድም ሆነ በሌላ ጎን ተጽዕኖ ሊያደርስ እንደሚችል ጠቁመው ባለድርሻ አካላት እየተከታተሉ በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡

የከፍተኛ ሙቀትና ቅዝቃዜ መፈራረቅ በጤናው ላይ ተጽዕኖ ሊያደርስ እንደሚችል ያስታወሱት አቶ ከፍያለው  ቀደም ሲል በቆላማ አካባቢዎች ይከሰት የነበረው የወባ በሽታ አሁን ላይ ደጋማ አካባቢዎች ጭምር በስፋት እየተከሰተ በመሆኑ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ  ቅኝት ሊደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ ለግብርናው ዘርፍ የሚያደርሰውን መረጃ  እንደ ክረምቱ  የበጋውን አየር ቅድመ ትንበያ እያደረሰ ሲሆን ቀሪ ሁለት ወራቶችንም በቅርብ ቀናት ውስጥ ይፋ ለማድረግ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ደረቃማ የአየር ሁኔታው ውሃ አቅርቦት ላይም ችግር ሊያስከትል ስለሚችል የቅድመ ጥንቃቄ ሥራ ሊሰራ ይገባል፡፡ አያይዘውም የውሃ መስሪያ ቤቶች እና ከሩቅ አካባቢ ከሚነፍሰው ግፊት ካለው ንፋስ ጋር ተያይዞ የእሳት  አደጋዎች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ መደረግ አለባቸው በማለት መክረዋል፡፡

ማህበረሰቡም የሚወጡ መረጃዎችን በመመርኮዝ የራሱን በቂ ዝግጅት በማድረግ ጤናውን እና አካባቢውን መጠበቅ እንዳለበትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በማዕከሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ  የትንበያ ኦፊሰር አቶ አለምገና ረታ በበኩላቸው ተቋሙ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ትንበያ ስራዎችን እየሰራ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እንደሚለቅ አስታውቀው አሁን ያለንበት የበጋ ወቅት ነፋሻማ እና ቀዝቃዛ አየር የሚስተዋልበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከአራቱ ክልሎች መካከል ሲዳማ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የበጋ ተጠቃሚ አካባቢዎች ስለመሆናቸው አንስተው እስካሁንም ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ እርጥበታማ አየር ያለ ሲሆን ታህሳስ እና ጥር ወር ደረቅና ቀዝቃዛማ አየር ሊጨምር እንደሚችል ነው የገለፁት፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት ከተለመደው አየር ውጪ እየተስተዋለ ነው ያሉት ባለሙያው ይህም ደረቅና ቀዝቃዛው አየር በታህሳስ እና ጥር ወር እንደሚቀጥል ነው የብሔራዊ ሜትዎሮሎጂ መረጃዎች ያመላክታሉ ብለዋል፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አየር ግፊት ከሳይቤሪያ አካባቢ የሚነሳ ቀዝቃዛ አየር እንዳለ  የጠቆሙት ባለሙያው የዚያ ተጽዕኖ የሚያገኝባቸው አካባቢዎች ናቸው ብለዋል፡፡ ከፍተኛ እና ተራራማ አካባቢዎች ለአብነትም በሲዳማ ክልል አርቤጎና፣ በደቡብ ኢትዮጵያ  ክልል ደጋማ አካባቢዎች፣ የጋሞ ከፍተኛ ቦታዎች፣ የወላይታ እና የጎፋ ከፍተኛ አካባቢዎች እንደዚሁም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ከፍተኛ ቦታዎች፣ ሀዲያ ከፍተኛ አካባቢዎች የማታውና የጥዋት ደረቅ እና ቀዝቃዛ አየር በስፋት እንደሚስተዋልባቸው አስረድተዋል፡፡  

ከአራት ክልሎች መካከል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የኮንጎ ቤዝን የሚያገኘው ክልል እንደመሆኑ ደረቁና ቀዝቃዛ አየር  እዛው አካባቢ እንዳለ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡ በተለይም ከፋ፣ ሸካ እንዲሁም ቤንች ማጅ አካባቢዎች ደመና አለ፡፡ ይህም ማለት በደረቁ እና ቀዝቃዛ አየር ተጽዕኖ ውስጥ ይወድቃል ማለት እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

 ደጋማ አካባቢዎች ላይ ከዚህ ውጪ የሆነ ቅዝቃዜ ሊኖር እንደማይችል ጠቅሰው ይህ ቀዝቃዛ እና ደረቅ አየር ዓለም አቀፍ ኡደት (ሲስተም) ስለሆነ አብዛኛው አካባቢዎች በዚህ ተጸዕኖ ውስጥ እንደሚሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ በአራቱ ክልሎች ሰብል ታጭዶ  አውድማ ላይ ያለ ሲሆን በቀኑ ደረቅ አየር እና ቅዝቃዜ የምርት ብክነት እንዳይኖር ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ 

አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ በአራቱም ክልሎች ወጥ የሆነ የአየር ሁኔታ እንደማይኖር ያነሱት ባለሙያው ባሳለፍነው ሁለት ወራት  እርጥበት አዘል አየር ስለነበር አሁን ላይ ያለው የአየር ሁኔታ አዲስ አይደለም ስንል ግን ተጽዕኖ የለውም ማለት እንዳልሆነ ህብረተሰቡ ሊረዳ ይገባል ብለዋል፡፡ 

በተለይም የሳይቤሪያ የሙቀት ግፊት ተጽዕኖ እኛ ጋር ስለሚኖር ህብረተሰቡ እስከ ጥር ወር መጨረሻ ድረስ ቀዝቃዛው አየር እንደሚቀጥል ተረድቶ ሌሊትም ሆነ ጥዋት ላይ አለባበሱን ጨምሮ ከወትሮው የተለየ ጥንቃቄ አድርጎ እንዲያስተካክል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡