የአንጀት ጥገኛ ትላትል በሽታ የህብረተሰብ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ መቆጣጠር መቻሉ ተጠቆመ
ለህጻናት በ6 ወር አንዴ ሲሰጥ የነበረው የአንጀት ጥገኛ ትላትል በሽታ መከላከያ መድሃኒትን በየወሩ ተደራሽ ማድረጉን የአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ገልጿል።
በግልና አካባቢ ንጽህና ጉድለት አማካኝነት በዙሪያ ወረዳው ቀበሌያት በስፋት ይስተዋል የነበረው የአንጀት ጥገኛ ትላትል ተጋላጭነትን መቆጣጠር መቻሉ ተመላክቷል።
በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ የቆላ ሼሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉነሽ ሙርቼ፤ ልጆቻቸው ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለሆድ ህመም ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰው አሁን የግልና የአካባቢ ንጽህና በመጠበቃቸው ከችግሩ መላቀቃቸውን ገልጸዋል።
ሌላኛዋ የአካባቢው ነዋሪ ወ/ሮ ሙሉነሸ በላይ እንደተናገሩት፤ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሰጡት የቅድመ መከላከል ትምህርት ጤናችንን ማምረት ጀምረናል።
የጤና ኤክስቴንሽን ወ/ሮ መቅደስ ዳንኤል፤ ህብረተሰቡ የግልና አካባቢ ንጽህና እንዲጠብቅ በተሰጠው የግንዛቤ ትምህርት የባህሪ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ከ5 አመት በታች ላሉ ህጻናት በ6 ወር አንዴ በዘመቻ ይታደል የነበረው የአንጀት ጥገኛ ትላትል መከላከያ መድሃኒት በአሁኑ ወቅት በየወሩ ተደራሽ በመደረጉ በሽታውን መቆጣጠር እንደተቻለ ጠቁመዋል።
በአርባምንጭ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የእናቶች እና ህፃናት ጤናና ስርአተ-ምግብ ዳይሬክቶሬት ባለሙያ አቶ ሙላቱ ዱርጎ እንደተናገሩት፤ በወረዳው ባሉ 5 ጤና ጣቢያዎች ስር በሚገኙ የጤና ኬላዎች እድሜያቸው ከ5 አመት በታች የሆኑ ህጻናት የአንጀት ጥገኛ ትላትል መከላከያ መድሃኒት በየወሩ በመሰጠቱ በሽታው ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ደርሷል።
ከ6 ወር በኋላ ተጨማሪ ምግብ የሚጀምሩ ህጻናት ለአንጀት ጥገኛ ትላትል ስለሚጋለጡ የመከላከያ መድሃኒት ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ባለሙያው የግልና አካባቢ ንጽህናን በመጠበቅ፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማረጋገጥ፣ ወሳኝ በሆኑ ሰአታት የእጅ ንጽህናን በመጠበቅ ብሎም የተሻሻሉ መፀዳጃዎችን ከመጠቀም ረገድ በስፋት መሰራት አለበት ብለዋል።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ተረፈ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች ደም በመለገሳቸው በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት በማትረፋቸው መደሰታቸውን አስታወቁ
በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ በመቀዛቀዙ አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየተስተዋለ መሆኑን ተገለጸ
የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የጤናው ዘርፍ ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አደረገ