የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፋ መጀመሩን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለ4 ተከታታይ ቀናት የሚዘልቀው 4ኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ሌሎች ወቅታዊ የጤና ችግሮች የልዬታ ስራዎች ባቀናጀ መልኩ እንደሚካሄድም ተመላክቷል።
ከታህሳስ 3 – 6 2018 ዓ.ም የሚካሄደው 4ኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ የማስጀመሪያ መድረክ በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ ገርተጽ ቀበሌ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አጉኔ አሾሌ በ4ኛው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህጻናት ለመከተብ ግብ መቀመጡን አስታውቀዋል።
ከክትባት ዘመቻው በተጓዳኝ ሌሎች ወቅታዊ የጤና ችግሮች የልዬታና ክትትል ስራዎችም ለማከናወን ስልት ተነድፎ ወደስራ መገባቱንም አብራርተዋል።
የስርአተ ምግብ ችግር ተጠቂ ህጻናት ልዬታ፣ የማርበርግ በሽታና ስርጭት ክትትል ስራና የቆልማማ እግር ችግር ተጠቂ ህጻናት የመለዬት ስራም በዘመቻው የተካተቱ ስለመሆናቸው ነው ዳይሬክተሩ ያመላከተቱ።
የኣሪ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ በድሉ በጊማስ በዞኑ በሚገኙ የጤና ተቋማትና ሙያተኞች ለከትባቱ ዘመቻ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቅሰው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ሁሉም ህጻናት ክትባቱን እንዲያገኙ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
በተቀናጀ መልኩ ለተጀመረው የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ስኬት የጤና መዋቅሩ በቅንጅት የሚያደርገው ርብርብ የሚደነቅ መሆኑን ጠቅሰው እንደ ዞን ሁሉም መዋቅሮች ዝግጅት ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የኣሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ ናቸው።
በተቀናጀ መልኩ የሚከናወኑ የጤና ተግባራት አስቀድሞ የማህበረሰብ ጤና ችግሮችን በመለዬት መፍትሄ ለማበጀት የሚያስችሉ መሆናቸውን ያነሱት አስተዳዳሪው ለውጤታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ ርብርብ እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ ወንድሜነህ አድማሱ – ከጂንካ ጣቢያችን

More Stories
በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የደቡብ ማዕከል ድጋፍ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ ሩዝ ያመረቱ አርሶ አደሮች ምርታማ መሆናቸውን ገለፁ
በክልሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ እናቶችና ሴቶች ተደራሽ በማድረግ ጤናቸው እንዲጠበቅ በትኩረት መሠራቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ
የነበሩ ችግሮች እየተቀረፉ በመምጣታቸው የተሻለ የጤና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን በከምባታ ዞን አንዳንድ የዶዮገና የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገልጋዮች ተናገሩ