ሰላምን ለማጽናት የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ሚና መወጣት ሲችል ነው – የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ
ሀዋሳ፡ የካቲት 04/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሰላምን ለማጽናት የሚቻለው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ሚና መወጣት ሲችል እንደሆነ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለፁ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 6ኛው ሀገር አቀፍ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ እየተካሔደ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በመድረኩ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ ሁሉንም ነገር ለማከናወን ሰላም በእጅጉ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ሰላም በአንድ ቀን ተገንብቶ የሚጠናቀቅ አይደለም ያሉት ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ፤ ሰላም ሁልጊዜ ጥበቃና እንክብካቤ የሚፈልግ እጅግ ታላቅ የጋራ ሃብት ነው ብለዋል።
ሰላምን ለማጽናት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩሉን ሚና መወጣት ሲችል በዘርፉ የላቀ ውጤት ይመዘገባል ሲሉም መክረዋል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰላም ግንባታ ላይ በማተኮር በሁሉም ክልል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተረድተው በባለቤትነት መንፈስ የተቀናጀና ውጤታማ የሰላም ግንባታ ስራ መስራት ይችሉ ዘንድ ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ እንዳለም ጠቁመዋል።
የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በበኩላቸው፤ የሀይማኖት ተቋማት አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን በፍጥነት ለመፍታት ሚናቸውን እየተወጡ መሆኑን አብራርተዋል።
የሀይማኖት ተቋማት በሰላም፣ በልማት እና በዲሞክራሲ ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ስለመሆኑም ዋና አስተዳዳሪ ጠቅሰዋል።
በመድረኩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ፤ በባህላዊና ሃይማኖታዊ የግጭት አፈታት ዘዴዎች በመጠቀም በክልሉ የሰላም ግንባታ ሂደት ላይ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን በተመለከተ የተዘጋጀ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ህዝበ ክርስቲያኑ የ2019 ዓ.ም የእንቁጣጣሽ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሀይማኖት አባቶች ተናገሩ
የ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ታላላቅ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እና የዲጂታል ሽግግር የሉዓላዊነቷ ምሰሶ መሆን የቻለችበት አመት መሆኑን አቶ አልማው ዘውዴ ገለፁ
ጳጕሜን 5 “የነገው ቀን” በኮሬ ዞን በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው