ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የወጣውን ገቢ መሰረት ያደረገ የስላይዲንግ ስኬል ለመተግበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

ከማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የወጣውን ገቢ መሰረት ያደረገ የስላይዲንግ ስኬል ለመተግበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 14/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገር ደረጃ ወጥ የሆነ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የወጣውን ገቢ መሰረት ያደረገ የስላይዲንግ ስኬል ለመተግበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2016 ዓ.ም ማህበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድህን አፈጻጸም ግምገማና የ2017 ዓ.ም ዕቅድ ዙሪያ፣ የገቢ አቅም መሰረት ያደረገ የጤና መድህን መዋጮ አከፋፈል ማስጀመሪያ እና የ2017 ዓ.ም የዞኑን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ንቅናቄ መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አካሂዷል።

በመድረኩ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በተሠራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በህብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ለውጥ እየታየ ቢሆንም በቀጣይ ትኩረት መስጠት የሚሹ ጉዳዮች ለመኖራቸው አመላክተዋል።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጊያ መንገዶች አንዱ የማህበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድህን አባል በመሆን ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ የተገልጋዮችን ቁጥር ለማሳደግ በ2017 ዓ.ም ዕቅድ መነሻ መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

በ2016 ዓ.ም በዞኑ 115ሺህ የሚሆኑ ግለሰቦች የተለያዩ የህክምና አገልግሎት እንዳገኙ የተናገሩት በጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ የህክምና አገልግሎት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ በላይ ዘውዴ 41 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበው ገንዘብ ወደ ባንክ ገቢ ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።

በመድረኩ ከኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የሐዋሳ ክላስተር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ያሬድ አስራት፤ በሀገር ደረጃ ወጥ የሆነ ገቢን መሰረት ያደረገ የስላይዲንግ ስኬል በጌዴኦ ዞን ባሉ ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ እና በዞን ደረጃ የጋራ ቋት በመመስረት ላይ ትኩረት ያደረገ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።

የጌዴኦ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዱአለም ማሞ ከውይይቱ ተሳታፊዎች በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ሀሳብ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በሀገር ደረጃ ወጥ የሆነ ማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተ ገቢን መሰረት ያደረገ የስላይዲንግ ስኬል ለመተግበር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የማህበረሰብ ዐቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ዙሪያም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የታዩ ክፍተቶችን በማረም የህብረተሰቡን ጤና ለማረጋገጥ በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዘጋቢ: እንግዳየሁ ቆሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን