በኮሬ ዞን አራተኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፈ ተጀመረ

በኮሬ ዞን አራተኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፈ ተጀመረ

ሀዋሳ፡ ታኅሥሥ 03/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኮሬ ዞን አራተኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በይፈ መጀመሩን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የኮሬ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሰማ ታምሩ እንደተናገሩት፥ አራተኛ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ከ40 ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት እየተሠጠ ነው።

የፖሊዮ በሽታ በቫይረስ የሚመጣና ከፍ ሲል ለሞትም የሚዳርግ በሽታ በመሆኑ ለተከታታይ ጊዜያት በዘመቻ በተቀናጀ መልኩ እየተሰጠ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፥ በሽታው በህክምና የማይድን በመሆኑ ቤተሰብ ህጻናትን በማስከተብ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ።

የፖሊዮ ቫይረስ ክትባት ዘመቻው ከታህሳስ 03-06/2018 ዓ/ም ድረስ ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕጻናት የሚሰጥ ሲሆን በመደበኛ ክትባቱን ለወሰዱም ሆነ ላልወሰዱ ህጻናት የሚሰጥ መሆኑን አመላክተዋል።

የክትባት ዘመቻውን በይፋ ያስጀመሩት የኮሬ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አስታረቀኝ አንደባ በበኩላቸው፥ ቤት ለቤት ለአራተኛ ዙር እየተሰጠ ያለውን የፖሊዮ ክትባት በአግባቡ ሕጻናትን በማስከተብ በሽታውን መከላከል እንዲቻል ህብረተሰቡ መተባበር አለባቸው ብለዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት ፕሮግራም አፊሴር አቶ ተረፈ ጸዳው፥ እንደወረርሽኝ እየተከሰተ ያለውን የፖሊዮ ቫይረስ ለመከላከልና ጤናማ ህጻናትን ለማሳደግ የሚደረግ ዘመቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግስት መከላከልንና አክሞ የማዳን የጤና ፖሊሲን እየተከተለ መሆኑንና የፖሊዮ ክትባት በሽታውን ቅድሚያ ለመከላከል እንደሚረዳ የገለጹት ኬሌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ዮሐንስ ሐይሉ ናቸው።

በዘመቻው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ቅኝትና አሰሳ፣ ቆልማማ እግር ችግር ያለባቸውን ልጆች የመለየት፣ የህጻናት፣ የነፍሰ ጡር እና አጥቢ እናቶች የስርዓተ ምግብ ደረጃ ልየታ እና ሕክምና እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ከክትባቱ ጎን ለጎን እየተሠራ እንደሆነ ተመላክቷል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከዛሬ ታህሳስ 3 ቀን 2018 ዓ/ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጥ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መግለጹ ይታወሳል።

ዘጋቢ : እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን