የጡት ካንሰር ተገቢው ህክምና በወቅቱ ካልተደረገ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ እንደመሆኑ ድንገት ሲያጋጥም በባህል ህክምና ከመዘናጋት ይልቅ በአፋጠኝ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ተገቢ ነው – ዶክተር ተሾመ አለምቦ

የጡት ካንሰር ተገቢው ህክምና በወቅቱ ካልተደረገ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ እንደመሆኑ ድንገት ሲያጋጥም በባህል ህክምና ከመዘናጋት ይልቅ በአፋጠኝ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ተገቢ ነው – ዶክተር ተሾመ አለምቦ

ሀዋሳ፡ ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጡት ካንሰር ተገቢው ህክምና በወቅቱ ካልተደረገ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥ እንደመሆኑ ድንገት ሲያጋጥም በባህል ህክምና ከመዘናጋት ይልቅ በአፋጠኝ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ተገቢ ነው ሲሉ በዱራሜ ዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ተሾመ አለምቦ አሳሰቡ።

የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ስለበሽታው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ዶክተሩ አስገንዝበዋል።

የጥቅምት ወር ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ ወር ሲሆን በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ ካንሰር ህመሞች እስከ 30 በመቶ የሚይዘው የጡት ካንሰር እንደሆነ የዘርፉ ህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ከስምንት ሴቶች አንዷ በጡት ካንሰር እንደምትጠቃም ያመላክታሉ።

በዱራሜ ዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ተሾመ አለምቦ፤ የጡት ካንሰር በሽታ በተለይም በሴቶች ላይ በስፋት የሚከሰት እንደሆነ በመግለጽ መንስኤውም በጡት ውስጥ የሚገኝ ህዋስ (cell) ያለአግባብ ሲያድግ እና ወደተለያየ የሰውነት ክፍል ሲሰራጭ እንደሆነ ገልፀዋል።

የጡት ካንሰር በሴቶች የሚከሰተውን ያህል ውስብስብ ባይሆንም በወንዶችም ላይ እንደሚከሰት ጠቁመው በብዛት ከአርባ ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶችን እንደሚያጠቃም አመላክተዋል።

ከዚህ ቀደም በቤተሰብ ውስጥ በበሽታው የተያዘ ሰው መኖር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያለመኖር፣ የአመጋገብ ስርዓት፣ አልኮል ማዘውተር፣ የመጀመሪያ የወር አበባ ከ12 አመት በታች ማየት እና የመቆሚያ ጊዜው መራዘም ለጡት ካንሰር አጋላጭ ምክንያቶች እንደሆኑ አብራርተዋል።

ማንኛዋም ሴት ሰውነቷን በምትታጠብበት ጊዜ ሁሉ የጡቷን ጤንነት በመዳሰስ ማረጋገጥ እንዳለባት የሚመክሩት ዶክተር ተሾመ ህመም፣ የተለየ ፈሳሽ፣ ጠረን እና ጠጠር ያለ ነገር በሚስተዋልበት ጊዜ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም መሄድ አለባቸው ብለዋል።

የጡት ካንሰር አራት የተለያዩ ደረጃዎች እንዳሉት በመግለጽ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከመድረሱ በፊት በጊዜ ከተደረሰበት የሚድን በሽታ መሆኑን ገልጸዋል።

ጡትን በራስ ከመመርመር በተጨማሪ ከስድስት ወር እስከ አንድ ዓመት ብሎም እስከ አንድ አመት ተኩል ጊዜ ድረስ ማጥባት በሽታውን ለመከላከል እንደሚረዳ በመጠቆም አመጋገብ ላይ ፍራፍሬን ማዘውተርና መሰል ቅድመ ጥንቃቄዎች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል።

በሚስተዋሉ የግንዛቤ እጥረቶች የጡት ካንሰር ሁሉ ለጡት መቆረጥ ይዳርጋል በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እናቶች ከህመሙ ጋር በጓዳ እንዲቆዩ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ሴቶች በተለያየ መልኩ በጡት ላይ የሚስተዋል ያልተለመደ ክስተትን በሚያዩበት ጊዜ በባህል ህክምና ከመዘናጋት ይልቅ በአፋጠኝ ወደ ጤና ተቋማት እንዲያመሩም አሳስበዋል።

ከህክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ ባለድርሻ አካላት መጠነ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ሊሠሩ እንደሚገባ ዶክተር ተሾመ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ: ኤደን ተረፈ – ከሆሳዕና ጣቢያችን