የወባ በሽታ ስርጭት ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ ተጠቆመ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 17/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰቡን ለጉዳት እየዳረገ የሚገኘውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሚገኙ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት አስታወቀ።
ውኃ ያቆሩ ጉዳጓዶችን በማፋሰስና ሌሎች የመከላከያ ተግባራት ቢከናወኑም፥ በጤና ተቋማት የመድኃኒት እጥረትና የአጎበር ተደራሽነት ክፍተት ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ሲሉ አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር ፀጋዬ ሻሜቦ በአብዛኛዎቹ የልዩ ወረዳው ቆላማ አካባቢዎች የበሽታው ስርጭት መኖሩን ጠቁመው የቁጥጥር ስራዎች በትኩረት እየተሰሩ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
የስርጭቱ ባህርይ ከወትሮ የተለየ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በሚሰሩ የመከላከያ ስራዎች ለውጦች እየታዩ መሆናቸውን አመላክተዋል።
በልዩ ወረዳው ጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና በሽታ መከላከል ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አማረ በየነ በበኩላቸው ከበሽታው ቁጥጥር ስራዎች በተጨማሪ ለህብረተሰቡ በበሽታው ስርጭት ዙሪያ የግንዛቤ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል።
ውኃ በሚያቁሩ አካባቢዎች የኬሚካል ርጭትና የማፋሰስ ስራዎች ብሎም አጎበር አጠቃቀም ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በልዩ ወረዳው ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ውኃ ያቆሩ አካባቢዎችን በማፋሰስና ሌሎችንም የመከላከያ ጥንቃቄ ተግባራትን እያከናወኑ ቢሆንም በጤና ተቋማት አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የመድኃኒት እጥረትና የአጎበር ተደራሽነት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት ሊሰጥ ይገባል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዳውሮ ዞን ሎማ ቦሣ ወረዳ የሚገኙ አመራሮች ደም በመለገሳቸው በደም እጦት ምክንያት የሚሞቱ ወገኖችን ህይወት በማትረፋቸው መደሰታቸውን አስታወቁ
በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ዙሪያ የሚደረገው ጥንቃቄ በመቀዛቀዙ አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየተስተዋለ መሆኑን ተገለጸ
የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የ2017 በጀት ዓመት የጤናው ዘርፍ ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አደረገ