“ለትምህርት ጥራት እኔም ድርሻ አለኝ”

በደረሰ አስፋው

ትምህርት በህይወታችን እና በዙሪያችን ባለው አለም ላይ ትልቅ ተጽእኖ አለው። ብሩህ የወደፊት ጊዜ በር የሚከፍት ቁልፍ ነው። ግለሰቦች ወደ ሙሉ አቅማቸው እንዲደርሱ እና የማህበረሰቦችን እድገት እንዲያሳድጉ ያደርጋል። እንዲሁም እንድናድግ፣ አቅማችንን በአግባቡ እንድንጠቀም የሚረዳን መሳሪያ ነው።

ትምህርት የበለጠ ብልህ እንድንሆን፣ አለምን እንድንረዳ ያደርገናል። የተማሩ ሰዎች ለህብረተሰባቸው አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማድረግ ይችላሉ። ብዙዎቹ የዓለማችን ታላላቅ ፈጠራዎች እና ግኝቶች ከተማሩ አእምሮዎች የተገኙ ናቸው።

በፍጥነት እየተለዋወጠ ባለው ዓለም፣ አዳዲስ ፈተናዎችን ለመቋቋም የትምህርት አድማስ እየሰፋ ነው። ለዚህም ሀገራችንም አዲስ የትምህርት ፖሊሲ ቀርጻ ተግባራዊ ማድረግ ጀምራለች፡፡ አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮችን ያካተተ ነው፡፡

ፖሊሲው ለ28 ዓመታት ሲተገበር የቆየውን የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲን የሚተካና አዲስ የመምህራንን የሙያ ደረጃን፣ የተማሪዎችን የክፍል ዕርከኖችን፣ በሥርዓተ ትምህርት የሚካተቱ ቋንቋዎችን፣ እንዲሁም በርካታ የትምህርት ሂደቶችንና አሰራሮችን ጭምር የሚያካትት ነው፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ(ፕ/ር) በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር ረቂቅ ፖሊሲው በተለያዩ ጊዜያት ምክክር ሲደረግበት የቆየ መሆኑን እና በትምህርቱ ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የታሰቡ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን መናገራቸው የሚታወስ ነው። ፖሊሲው በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን በመመልከት በትምህርቱ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ሊፈታ በሚችልና አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ፖሊሲው በመላው ሀገሪቱ መተግበር ከጀመረም አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ ሀገራዊ አጀንዳ ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ምን ለውጦች ተመዘገቡ ብሎ መፈተሽ የሚገባበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ለዚህም ቅኝት ያደረግነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርቱ ዘርፍ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገን እስካሁን የተወሰዱ እርምጃዎችና የመጡ ለውጦችን በማስመልከት ነው፡፡ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የተጀመሩ ተግባራትን በውጤት ለማጀብ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ስለመሆናቸው ነው፡፡

ከነዚህም ውስጥ በአቅም ግንባታ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠቃሾች ናቸው። በክልሉ ምንም አይነት ስልጠና ሳይኖራቸው የመማር ማስተማሩን ተግባር እያከናወኑ ለሚገኙ የቅድመ አንደኛ ደረጃ አመቻች መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠቱ የትምህርት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ከተከናወኑ ተግባራት አንዱ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ህጻናት ምንም አይነት ፊደልና ቁጥር ሳይለዩ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ይገቡ ነበር፡፡ ይህን ስር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ የተጀመረው ተግባር እሰየው የሚያስብል ነው። ይህም ህጻናት በቀጣይ የልጅነት ዘመናቸው የሚቀስሙት ዕውቀትና ክህሎት ለወደፊት ስብዕናቸው መሰረት የሚጥል በመሆኑ ለህጻናት የአእምሯዊና አካላዊ ዕድገት መጎልበት ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ነው፡፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራት እና የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል ከተከናወኑ አንኳር ጉዳዮች በትምህርት ቤቶች ጠንካራ እና ወቅቱን የዋጀ የአመራር ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ ያለው ተግባርም ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዚህም የትምህርት ቤት አመራሮች ሪፎርም ተከናውኗል።

በሪፎርሙ ተወዳድረው ምደባ ለተሰጣቸው የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሠ-መምህራን፣ ምክትል ርዕሠ-መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ከህዳር 16- 25/ 2017 ዓ/ም በ4 ዙር በወራቤ ዩኒቨርስቲ፣ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢና ዱራሜ ካምፓስ እንዲሁም ወልቂጤ ዩኒቨርስቲዎች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በክልሉ የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሽ ነው፡፡ በክልሉ በ164 ትምህርት ቤቶች የማህበረሰብ አቀፍ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ለማስጀመር እየተሰራ ነው፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ የተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግና ውጤታቸውን ለማሻሻል የተማሪዎች ምገባ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የምገባ ፕሮግራሙ የትምህርት ብክነትን፣ መጠነ ማርፈድ፣ መቅረትና ማቋረጥን በመቀነስ ተማሪዎች በትምህርት ውጤታቸው የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ አለው። በክልሉ ከ2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በ5 ዞኖች እና በሁለት ልዩ ወረዳዎች በሚገኙ 66 ትምህርት ቤቶች የምገባ አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ 54 ሺህ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸው ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በ2017 የትምህርት ዘመንም ይሄንኑ በክልሉ በሁሉም ዞንና ልዩ ወረዳዎች ለማስጀመር የክልሉ መንግስት 20 ሚሊዮን ብር ለዚሁ ፕሮግራም መመደቡን መረጃው ያመለክታል።

ትምህርት ያለ ግብአት የሚፈለገውን ውጤት ማረጋገጥ እንደማይቻል የተገነዘበው ክልሉ ሌላው ትኩረት ያደረገው የተማሪ መፅሃፍ ጥምርታን ማሻሻል ነው፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በክልሉ “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” በሚል መሪ ሀሳብ የመጽሐፍ ህትመት ሀብት አሰባሰብ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው፡፡

የመጽሐፍ ተማሪ ጥምርታን ማሻሻልና በወቅቱ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ የተማሪዎች የትምህርት አቀባበልን ከማሳደግ ባሻገር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በክልሉ ባለፈው ዓመት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 3 መቶ 26 ሚልዮን ብር በማሰባሰብ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያና የማስተማሪያ መጽሐፍት በማሳተም ማሰራጨት መቻሉ ተጠቃሽ ተግባር ነው፡፡

በዘንድሮ ዓመትም መላው የክልሉን ህዝብና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ “አንድ መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ” በሚል መሪ ሀሳብ ለትምህርት ጥራት እኔም ድርሻ አለኝ እንዲል የመጽሐፍ ህትመት ሀብት ማሰባሰብ ንቅናቄ ይካሄዳል።

በዚህም ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ መጽሐፍ በማሳተም በክልሉ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተለይም ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን የመማሪያና የማስተማሪያ መጽሐፍ ጥምርታ አንድ ለአራት ለማድረግና የመምህሩን መምሪያ አንድ ለአንድ በማድረስ ለትምህርት ጥራት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ታቅዷል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር በ2017 የትምህርት ዘመን ለ8ኛ እና ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት ዝግጅት ስለመደረጉ አስታውቋል፡፡ የማጠናከሪያ ትምህርቱን በክልሉ በሁሉም ዞንና ልዩ ወረዳዎች ወጥነት ባለው መልኩ መስጠት እንዲቻል በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ስለመደረጉም ነው የተመላከተው።

ባለፉት ዓመታት እንደ ሃገር የትምህርት ውጤት ስብራት ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በሀገር አቀፍና ክልላዊ ፈተናዎች የሚያስመዘግቡት ውጤት ከሚፈለገው በታች ነበር። ይህን ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል በክልሉ በመምህራንና በተማሪዎች ላይ ያተኮሩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው። ለመምህራን በፈተና አዘገጃጀት ላይ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ለ8ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማጠናከርያ ትምህርት ተሰጥቷል።

በዚህም 4 ሺህ የሚሆኑ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች በሆሳዕና ትምህርት ኮሌጅ ከ22 ሺህ በላይ የሚሆኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ደግሞ በክልሉ በሚገኙ ሦስት ዩንቨርስቲዎች አማካኝነት የማጠናከሪያ ትምህርት እንደተሰጣቸው ተመላክቷል። በተሠራው ስራ በክልሉ ካለፉት ዓመታት በተሻለ በተማሪዎች ውጤት ላይ አበረታች ለውጥ ተመዝግቧል፡፡

በ2015 በ8ኛ ክፍል 18 ነጥብ 5 በመቶ የነበረውን የማለፍ ምጣኔ በ2016 የትምህርት ዘመን 44 በመቶ ማድረስ መቻሉ ነው የተገለጸው። በተመሳሳይ 12ኛ ክፍል በ2015 የነበረውን 2 ነጥብ 7 በመቶ የማለፍ ምጣኔ ወደ 3 ነጥብ 4 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ተገልጿል።

በ2017 የትምህርት ዘመን ይህንኑ በማጠናከር በተማሪዎች ውጤት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ በቅንጅት እየተሰራ ነው። በሁሉም አካባቢዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህም ከ26 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎችና ከ29 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት ለመስጠት መታቀዱን የቢሮው መረጃ አመላክቷል።

ሌላው የክልሉ አንኳር የትምህርት ዘርፍ ተግባር የሆነው ብቁ የሆኑ የትምህርት አመራሮች ምደባ ላይ የተሰራው ተግባር ነው፡፡ ይህም ውጤት ማስመዝገብ የማይችሉ የትምህርት ቤት አመራሮች በአመራርነት መቀጠል እንደማይችሉ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው ሌላው መረጃ ነው፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ፦ የትምህርት ስርዓቱ ካሉበት ተግዳሮቶች ለማውጣት የችግሩን ምንጭ በጥናት መለየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ዋነኛው ክፍተት የትምህርት ቤት አመራሮች ሀላፊነታቸውን በተገቢው መወጣት አለመቻል በመሆኑ የሪፎርም ስራ ተግባራዊ መደረጉን አንስተው ይህንንም ለመቅረፍ በተሻሉ አመራሮች የመተካት ስራ መከናወኑን ነው የተናገሩት፡፡

ለቦታው የሚመጥኑ አመራሮችን በማወዳደር 2 ሺህ 783 የሚሆኑ አመራሮችን በማሰልጠን በየትምህርት ተቋማት ተመድበዋል፡፡ ወደ ስራ የገቡት የትምህርት ቤት አመራሮች በሶስት አመታት ውስጥ የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል ለማድረግ ከክልሉ ጋር ውል ገብተዋል፡፡ በገቡት ውል መሠረት ሀላፊነታቸውን መወጣት ካልቻሉ ከአመራርነት እንዲነሱ ይደረጋል። የትምህርት ቤት አመራሮች ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት የመሪነት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውም አቶ አንተነህ ፈቃዱ አሳስበዋል፡፡

በክልሉ ሪፎርሙን ተከትሎ ምደባ በተሰጠባቸው 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰለጠነና ለደረጃው የሚመጥን የትምህርት ቤት አመራር ሽፋን ወደ መቶ በመቶ ማድረስ ተችሏል። በሪፎርሙ ተወዳድረው ምደባ ካገኙት መካከል 68 በመቶው ነባር የትምህርት ቤት አመራሮች 31 በመቶው መምህራን እና አንድ በመቶው የትምህርት ጽ/ቤት ባለሙያዎች መሆናቸውን በማሳያነት ጠቅሰው አስረድተዋል።

በሪፎርሙ በክልሉ ለትምህርት ቤት አመራርነት ከሚፈለገው 3 ሺህ 789 ውስጥ 3 ሺህ 11 ዝቅተኛውን የመወዳደሪያ መስፈርት አሟልተው መመረጣቸውን አቶ አንተነህ ተናግረዋል። ከዚህም ውስጥ 2 ሺህ 727 ወይም 72 በመቶ የሚሆኑት ምደባ ተሰጥቷቸው ወደ ስራ መግባታቸውን አንስተዋል። ምደባ በተሰጣቸው አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ት/ቤት የሰለጠነ የትምህርት ቤት አመራር ሽፋን 61 ነጥብ 7 በመቶ ከነበረበት ወደ መቶ በመቶ ማደጉን እንስተዋል።

ያልተመደበባቸው 442 ትምህርት ቤቶችን ሲጨምር ደግሞ ወደ 75 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል። በተመሳሳይ በ2ኛ ደረጃ ት/ቤት 57 ነጥብ 8 በመቶ የነበረውን የሰለጠነ የትምህርት ቤት አመራር ሽፋን ወደ መቶ በመቶ ማደጉን አንስተው ያልተመደበባቸው 85 ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ወደ 69 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተሰራ ያለው ስራ እሰየው የሚያስብል ነው፡፡ ከክልሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የትምህርት ቤት አመራር ላይ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በትምህርት ንቅናቄ መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ያጋጠሙ ስብራቶችን ለመጠገን አሳታፊ በሆነ መልኩ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ነው፡፡

የተጀመሩ ተግባራት ፍሬያማ ይሆኑ ዘንድ እና ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት የትምህርት አመራሩን አቅም በተከታታይነት ማጎልበትና ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በየጊዜው በጥናትና ምርምር የተደገፉ ስራዎች መስራትም ይገባል ብለዋል።

ጠንካራ የትምህርት ሥርዓት ያላቸው ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች አመርቂ ውጤት አስመዝገበዋል። ብቃት ያላቸው ተወዳዳሪ ዜጎችን በብዛት ለማፍራት በሚደረገው እንቅስቃሴ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን ማጠናከርም አለባቸው።

የትምህርት ግብአት ማሟላት፣ ለተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠት፣ ለመምህራን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናና የትምህርት አመራሩን ማብቃት በተከታታይነት ይሰራል። የተሻሉ ተሞክሮዎች የተካተቱበት የሪፎርም ስራ መሰራትንም ይጠይቃል ሲሉ ነው የተደመጡት፡፡