ከመማር ማስተማር ተግባሩ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ጥረት ቢደረግም በተፈለገው ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን የቱም ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ መምህራን ተናገሩ
የበጀት እና የመስሪያ ቦታ ችግሮች እንዲሁም የመብራት መቆራረጥ የቴክኖሎጂ ሽግግሮች ለማድረግ እንቅፋት መሆናቸውን ኮሌጁ ገልጿል።
የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጆች ሲቋቋሙ ዋና አላማቸው በሙያና ስነ-ምግባር የሰለጠነ ባለሙያ ከማፍራት ባለፈ በተቋቋሙበት አካባቢ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎች በሰርቶ ማሳያ በማስደገፍ በመስራት ለአካባቢው ማህበረሰብ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ተግባራቸው ነው።
የቱም ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅም ሲቋቋም በተለይም በአርብቶ እና ከፊል አርሶአደር አካባቢ ያሉ ተማሪዎችን ተቀብሎ በሙያ ከማሰልጠን በዘለል በአርብቶ አደሩ አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲላመዱ እና የቴክኖሎጂ ሺግግር እንዲያደርጉ ታስቦ የተቋቋመ ነው።
መምህር በርጌ በእውቀት እና መምህር ሙልቀን አደመ እንዲሁም መምህር ተድላ ተሰማ በሰብል ልማት እና በእርባታ ዘርፍ ለተማሪዎች ስልጠና የሚሰጡ መምህራኖች ናቸው።
እንደ እነርሱ ገለጻ በተለይ አካባቢው አርብቶአደር እና አርሶአደር አካባቢ እንደመሆኑ መጠን በንብ እና በእንስሳት እርባታ እንዲሁም በሰብል ልማት ዘርፍ ለተማሪዎች በንድፈ ሀሳብ የሚሰጡትን ትምህርት በተግባር በማስደገፍ እየሰጡ ቢገኙም ነገር ግን በስፋት ተግባሩን በማስኬድ ለአርብቶ እና አርሶአደሩ የማስፋት እና የማላመድ ስራ ከመስራት አንጻር ውስንነት መኖሩን ገልጸዋል።
በተለይም የበጀት እና የቦታ ጥበት እጥረት መኖር በሙከራ ደረጃ የሰሩት እና ከአካባቢው ስነ-ምህዳር ጋር እያላመዱ ያሉትን የሙዝ፣ የሸንኮራ አገዳ፣ የቡና ምርቶችን እንዲሁም የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በስፋት ለማምረትም ይሁን ለማስተዋወቅ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል።
የቱም ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮልጅ ተወካይ ዲን አንለይ አሀዱ በበኩላቸው፤ ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን በኮሌጁ ለተማሪዎች ማስተማሪያ የተዘጋጁ እና ወጤት ተገኝቶባቸው ለአርሶ እና አርብቶ አደሩ የተሰራጩ ከቴክኖሎጂ አንጻር የተሻሻሉ የበቆሎ መፈልፈያ፣ የዘር መዝሪያ ቴክኖሎጂዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም በኮሌጁ ባለው ውስን መሬት አካባቢው አርብቶ እና ከፊል አርሶአደር አካባቢ እንደመሆኑ መጠን የተሻሻሉ የእንስሳት መኖዎችን እንዲሁም የቡና፣ የሙዝ እና የሸንኮራ አገዳ ምርቶችን ከተማሪዎች መማሪያነት ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ ለማስተላለፍ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህንን የተጀመረውን ስራ አስፍቶ ለመስራት ከክልሉ የሚመደበው በጀት በተማሪ ቁጥር ተሰልቶ በመሆኑ የበጀት እጥረት መኖር እንዲሁም የመስሪያ ቦታ እና የመብራት የኃይል መቆራረጥ መኖር ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ እነዚህ ችግሮች ከተፈቱ በተለይም ከአካባቢ አመራር አካላት ጋር በመቀናጀት የመስሪያ ቦታዎች ከተገኙ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን አጠናክሮ ለመስራት እንደሚጥሩም ገልጸዋል።
የምእራብ ኦሞ ዞን የመንግስት ዋና ተጠሪው አቶ በደሉ ሀምዛ በበኩላቸው የቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ከመማር ማስተማር ስራ ባለፈ የአካባቢን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸው ኮሌጆቹ ምንም እንኳ በክልሉ የሚተዳደሩ ቢሆንም በተለይም የሚነሱ እጥረቶችን ለመቅረፍ በዞኑ የሚፈቱትን በመውሰድ ኮሌጁ የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን
More Stories
በጎፋ ዞን በያዝነው በጀት ዓመት ከ117 ሺህ በላይ አባወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ
ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በጋራ በመከላከል የሸማቹን ህብረተሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ
ጳጉሜ 2 የሪፎርም ቀን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ የዞንና የክልል አመራሮች በተገኙበት ወይይት ተካሂዷል።