የበረሃው ገነት

የበረሃው ገነት

በፈረኦን ደበበ

የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የእርሻ መስፋፋትና የከተሞች ማደግ ለተፈጥሮ መዛባት ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው። ፓርኮች ደግሞ ጉዳቱን ለመከላከል ይረዳሉ። እነሱ የጥንቱ መስተጋብር ሳይበረዝ ሳይደለዝ እንዲቆይ የሚያደርጉ መሆኑም ጠቀሜታቸውን ከፍ ያደርጋል፡፡

አዎን ከቀን ወደ ቀን ውድመቱ እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር የፓርኮች ቁጥርም የዚያ ያህል እንዲያድግ ያስፈልጋል፡፡ ካለበለዚያ ተፈጥሯዊ ቅርሶችና መስተጋብሮችን ማግኘት ስለማይቻል፡፡ ጣዕሙንም አሁን በከተሞች ከሚያድጉ ወጣቶች ይልቅ አያት ቅድመ አያቶቻችን ስለሚረዱት፡፡

እንዲህ የተባለው ለምን እንደሆነ ማወቁ ከባድ አይመስልም፡፡ የጥንቱ ዜይቤ ቃናውን ሳይለቅ መኖሩ እጅግ የሚያስደስት ስለሆነ ነው፡፡ ደኑ፣ አራዊት፣ አዕዋፋት፣ ወንዙና ሽንተረሩ ተዋደው የሚኖሩ እንደመሆናቸው፡፡

የተፈጥሮ ውበት በጣም የሚያስደስት ጸጋ ሲሆን ተፈጥሮን በአንድ ጣራ አድርገው የሚያሳዩት ፓርኮች ሌላ ጠቀሜታም አላቸው፡፡ በርካታ ጎብኚዎችን በመሳብ የሀገርን ምጣኔ ሀብት ማሳደግ የዚህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ መንግሥት በክልሎች እያስፋፋ ያለው የፓርክ ልማት ሥራዎችም ሀገርን ለማሳደግ ይረዳሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች አበረታች ናቸው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ገጸ-በረከቶች ባለቤት መሆኗ ሲጠቀስ እነዚህም ለቱሪዝም ከፍተኛ አስዋጽዖ ይኖራቸዋል፡፡ ቆላ፣ ደጋ፣ ወንዝ፣ ነፋሻማ አየር፣ ወፍና አራዊቱ ሁሉ የውበቷ ማሳያዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ሀብቶች ደግሞ በደቡብ የሀገራችን ክፍሎች በስፋት መገኘታቸው ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ በተለይ በተቀራራቢ ቦታ ያሉ ፓርኮችን እንኳን ብንወስድ የማዜ ብሄራዊ ፓርክ፣ ነጭ ሳር፣ የማጎ ብሔራዊ ፓርክ፣ ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ እና ሌሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

አሁን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ከሚገኙ ፓርኮች አንዱን እንኳን ወስደን ብንመለከት ስመ-ጥሩው ማጎ ፓርክን እናገኛለን፡፡ ከዕድሜው አንጻር ገና ታዳጊ ቢሆንም የአካባቢውን መስተጋብር አንድ ላይ አካቶ መያዝ መቻሉ አንጋፋ ያደርገዋል፡፡

እየተስፋፋ ያለው የእርሻ ሥራ እና ግጦሹን ተቋቁሞ ያለው ፓርክ በሀገራችን ቆላማ ተብለው ከሚታወቁ ቦታዎች በአንዱ ቢሆንም በውስጡ አቅፎ የያዛቸው ሀብቶችና እርጥብ መሬቶችን ከወሰድን “የበረሃው ገነት” ተብሎ እንዲጠራ ያደርገዋል ምክንያቱም ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚሆኑ ወንዞችና ምንጮችን እያፈለቀ እንደመሆኑ፡፡ አካባቢውን የጎበኙ ጸሀፊዎች እንደገለጹት ከሆነ ፓርኩ እ.ኤ.አ. በ1979 የተመሠረተ ሲሆን ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በ770 እና ከጂንካ ከተማ በምዕራብ በኩል በ40 ኪ. ሜትሮች ላይ ይገኛል፡፡ 21 ሺህ 620 ሄክታር እንደሚያካልል የተገለጸለት ፓርኩ በዋናነት ቁጥቋጦና የሣር ምድር፣ ረግረጋማ ቦታዎችና ወንዝ ተከትሎ የሚያድጉ ዛፎችን እንደያዘም ነው የተገለጸው፡፡

የመሬት ገጽታው ሽንተረርና ወጣ ገባነት የሚበዛበት ይህ ፓርክ ከባህር ጠለል በላይ ከ450 እስከ 2528 ሜትር የሚደርስ ሲሆን ትልቁ ተራራም የማጎ ተራራ ነው፡፡ ከ400 እስከ 500 ሚሊ ሜትር ዓመታዊ የዝናብ መጠን ያገኛል የተባለለት ፓርክ ከፍተኛ ዝናብም በመጋቢትና ሚያዝያ ወራት ያገኛል፡፡

በተቃራኒው ደረቃማ ወራት ከህዳር እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ እንደሆነ የተነገረለት ፓርኩ በስተ ደቡብ እና ምሥራቅ ካሉ ከፍታማ ቦታዎች የሚነሱ ማጎ፣ ነሪ እና ማኪ የተባሉ ወንዞችንም አካቷል፡፡ ዓመቱን ሙሉ ይፈሳሉ ከተባሉት ከእነዚሁ ወንዞች መካከል ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፈው የማጎ ወንዝ ከነሪ ወንዝ ጋር በማጎ ረግረጋማ ቦታ ላይ ይገናኛሉ፡፡

እንደ መረጃ ምንጮች ከሆነ ፓርኩ በውስጡ 74 ዓይነት አጥቢ እንስሳት፣ 237 አዕዋፋትና እንዲሁም 10 ዓይነት ተሳቢ እንስሳትና 14 የዓሣ ዝሪያዎችን አካቷል፡፡ በውስጡ ከሚገኙ በርካታ አጥቢ እንስሳት መካከል ጎሽ፣ ዝሆን፣ ቀጭኔ፣ አጋዘን፣ ድኩላ፣ ዜብራ፣ አንበሳ፣ ነብር፣ ዝንጀሮ እና ሌሎች ይጠቀሳሉ፡፡ አፍሪካ ኤክስፐርት የተባለው ሌላ ድረ ገጽም ስለ ፓርኩ እንደገለጸው ከሆነ መገኛው በኦሞ ወንዝ 90ኛ መታጠፊያው ላይ እንደሆነ ጠቅሶ በተለይ በዝቅተኛው የማጎ ወንዝ እና ዲፓ ሀይቅ አጠገብ የወንዝ ዱካን ተከትሎ በሚያድጉ ዛፎችና ረግረጋማ ቦታዎች የተሸፈነ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ወደ ታች የሣር ምድርን የሚያሳዩ ከፍተኛ ቦታዎች ያሉበት መሆኑን ጠቅሶ አብዛኛው ክፍል በኦሞ ሸለቆ ወይም የስምጥ ሸለቆ ምሥራቃዊ ክፍልን ያዋስናል ብሏል፡፡ የኦሞ ብሄራዊ ፓርክን የሚለየውንና የኦሞ ገባር የሆነውን የማጎ ወንዝን በመጥቀስ፡፡

ከወደ ምዕራብ በኩል ታማ የተባለው የዱር አራዊት ማቆያ የሚገኝ ሲሆን አንዱ ከሌላው የሚለየው ደግሞ በታማ ወንዝ ነው፡፡ በዚህ ድረ-ገጽና በሌሎች በስፋት የተጠቀሰው ሌላው የፓርኩ ገጽታ የአካባቢው ማህበረሰብ ሲሆኑ ይህ የሰውና የተፈጥሮ መስተጋብርንም ያመለክትል ማለት ነው፡፡ የራሳቸው ባህል፣ ወግና ቋንቋ ከመኖራቸው ውጭ የጋራ ማንነትም ያላቸው እነዚህ ማህበረሰቦች ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋርም የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ብሔረሰቦቹም አሪ፣ ማሌ፣ በና፣ ቦንጎሶ፣ ሀመር፣ ክውጉ፣ ካሮ እና ሙርሲ ናቸው፡፡

ከአርባ ምንጭ በጂንካ ወደ ዝቅተኛው የኦሞ ሸለቆ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው የማጎ ብሔራዊ ፓርክ አስደናቂ ገጽታ እንዳለውም ተጠቅሷል ከሰው ገለል ያለና በጥቂት ጎብኚዎች የሚዘወተር መሆኑንም በማንሳት፡፡ ብዙ የአፍሪካ ክፍሎች ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት የኖሩበት ማስታወሻ መሆኑም ነው በድረ-ገጹ የተመለከተው፡፡

ከዚህ አንጻር ብሄራዊ ፓርኮች የአሁኑ ሳይሆን ያለፉ ዘመናት ማስታወሻ መሆናቸው ጠቀሜታቸውን ከፍ ያደርጋል ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በየቦታው የማናገኛቸው ዕጽዋት፣ እንስሳትና አዕዋፋትን አቅፈው ስለሚገኙ፡፡ በፍጥነት እየወደመ ካለው የአካባቢ ሥነ ምህዳርም እንደ ሙዚየም መታየት ይችላሉ ምክንያቱም ግንዛቤ የሌላቸው ህጻናት አድገው እንዲመለከቱና እንዲደሰቱበት ስለሚያደርጉ። ከውበት በተጨማሪ የተፈጥሮ ሚዛን ለመጠበቅም ያገለግላሉ፡፡ በተለይ ጉዳት እያስከተለ ካለው የሰደድ እሳት ከተጠበቁ የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን ለመቋቋምም ይረዳሉና፡፡

ከአየር ንብረት ለውጥ አንጻር ሌላው ጠቀሜታቸው ለጤና ተስማሚ የሆነ አየር ማምረታቸው ነው፡፡ በተጨማሪ ለምግብነት የሚውሉ የተለያዩ ፍራፍሬዎች፣ ዓሳ፣ አዝርዕት ዓይነቶችና እርጥብ መሬትም ይዘዋል የሰው ልጅ ችግር ባጋጠመው ጊዜ መጠቀም እንዲችል፡፡

ለዚህ ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትልቅ አቅም አለው፡፡ በቂ ቦታ፣ የዝናብ መጠን፣ ድንቅዬ የእንስሳትና አራዊት ዝሪያዎች ስለሚኖሩበት፡፡ በፓርኮች አስተዳደር የሚታዩ ችግሮችን በማስወገድ ከማዜ፣ ነጭ ሳር፣ ማጎና ኦሞ ፓርኮች በተጨማሪ ሌሎች ፓርኮችንም ማቋቋም ያስችላል፡፡