የአካል ጉዳተኞች ተሣትፎና የአመራርነት ሚና

የአካል ጉዳተኞች ተሣትፎና የአመራርነት ሚና

በመሐሪ አድነው

በሀገራችን አካል ጉዳተኞች በማህበራዊ ጫናዎችና በመዋቅራዊ አድሎ ምክንያት ከውሳኔ ሰጭነትና የአመራርነት ሚና ተገልለው ቆይተዋል። የችግሩ ስፋት በግሉ ዘርፍ በኩል ደግሞ የባሰ ነው። አካል ጉዳተኞችን በአመራርና በውሳኔ ሰጭነት ሚና የማሳደግ ጥያቄ የቅንጦት ጥያቄ ሳይሆን የመብት ጉዳይ በመሆኑ ለዘመናት ለከፋ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የተዳረጉ እንደመሆናቸው እኩል ተጠቃሚነቱንና ተካታችነቱን ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡

አካል ጉዳተኞችን ከአመራርነትና ከውሳኔ ሰጪነት ማግለል አካታች ማህበረሠብ እና ሥርዓት ለመፍጠር የሚደረጉ እርምጃዎችን ወደ ኋላ ይጐትታል፡፡ በሌላ በኩል አካል ጉዳተኞች በአመራርና ውሳኔ ሰጭነት ላይ ያላቸውን ሚና ማጉላት መሠረታዊ የአካል ጉዳተኞችን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡ ለምሣሌ ያህል በወረዳ አመራርነት የተመደበ አካል ጉዳተኛ አመራር ቢኖር፣ በዚያ ወረዳ ያሉ የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ጥርጥር የለውም፡፡

በተመሳሳይም፤ የሚወጡ ህጐች፣ መመሪያዎችና ደንቦች አካል ጉዳተኞችን አካታች በሆነ መልኩ ወደ ሥራ እንዲገቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር አካል ጉዳተኞችን የወከሉ እንደራሴዎች ቢኖሩ እንደዚሁ ትልቅ ተፅእኖ መፍጠር ይችላሉ፡፡ ችግሩን የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጐጌ ተስፋዬ ሲገልፁ የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና ማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ የሚቻለው ለህግ እና ለፖሊሲ መደላድሎችን በመፍጠርና በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ስንችል ነው ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞች ወደ አመራርነት ሚና እንዳይመጡ የሚያደርጉ እንቅፋቶችን ከመሠረቱ ማስወገድ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡ ይህ የሚጀምረው የትምህርት፣ የሥራ፣ የጤና አጠባበቅ እና የቴክኖሎጂ ተደራሽነት እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችን ማቅረብ ሲቻል እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና ለማሳደግ በመንግስትም ሆነ በግል ድርጅቶች ለአካል ጉዳተኞች ፍትሐዊ የትምህርት እድል፣ የሙያ ክህሎት ማሻሻያ የአመራርነት ሥልጠናን ጨምሮ አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር እንዲሁም በሁሉም የህይወት ዘርፎች እኩል ተሣትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋም በመያዝ በየደረጃው አካታች ፖሊሲ እና ኘሮግራሞችን ቀርፆ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ዶ/ር ኤርጐጌ ገልፀዋል፡፡

ሆኖም ከጉዳቱ ስፋት አንፃር ከተሠራው ይልቅ ገና ብዙ የሚቀር ሥራ እንዳለ ገልፀው ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመሥጠት ሁሉን አቀፍ ርብርብ ማድረግ ከሁሉም ይጠበቃል ሲሉም አክለዋል፡፡

በዚህ ዓመት መሪ ቃል መሠረት የአካል ጉዳተኞችን መብት ማጉላትና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ መሪነታቸውን ማረጋገጥ አለብን ያሉት ዶ/ር ኤርጐጌ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ፍላጐት በትክክል የሚያካትቱና የሚያረጋግጡ አዳዲስ ፖሊሲዎችንና የአሠራር ስልቶችን በማዘጋጀት አካል ጉዳተኞች ወደ መሪነት የሚመጡበትን፣ ችሎታና ሥራቸውን የሚያጐለብቱበትና ተነሳሽነታቸውን ይበልጥ የሚያሳድጉበት አካባቢ መፍጠር ይኖርብናል በማለትም ተናግረዋል፡፡

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ተሣትፎና ተጠቃሚነትን ለማጐልበት የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች እና ፖሊሲዎችን እንዳዘጋጀ ገልፀው ሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመፈራረም እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ በሁሉም ሴክተር የልማት ዕቅዶች ውስጥ እንዲካተቱና ተግባራዊ እንዲሆኑ በሁለንተናዊ መልኩ በመሥራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ በህብረተሰቡ ውስጥ አካል ጉዳተኝነትን በሚመለከት ሠፍኖ የኖረው የተዛባ አመለካከት መድሎና ማግለል እንዲሁም ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቅረፍ የግንዛቤ ማዳበሪያ ሥራዎችን በትኩረት መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡

አካል ጉዳተኞችን በኢኮኖሚና ማህበራዊ ግልጋሎት እንዲሁም በፖለቲካ እኩል ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንዲሁም የአመለካከትም ሆነ ተቋማዊ መሠናክሎችን ለማስወገድ ከምንጊዜውም በላይ መንግሥት በትኩረት ይንቀሳቀሳል በማለት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አረጋግጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ባስተላለፉት መልዕክት በመሪ ቃሉ ዓላማ መሠረት የአካል ጉዳተኞችን ተፅእኖ ፈጣሪነት እና የመሪነት ሚና በህብረተሠቡ ውስጥ የማሳደግ አስፈላጊነትና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው እንዲያድግ አበክሮ ይሠራል ብለዋል፡፡

ስለሆነም የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና ለማጉላት አግላይ የሆኑ የህግ እና ፖሊሲ ማዕቀፎችን ማሻሻልና የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቅረፍ ፖሊቲካዊ ቁርጠኝነት ከመቼውም በላይ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የማህበራትን አቅም ከመገንባት አንፃርም በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ በግጭት ምክንያት ወደ መፍረስ ደረጃ ደርሶ የነበረውን የትግራይ ክልል የማህበራት እንቅስቃሴን ፌደሬሽኑ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመሆን መልሶ የማቋቋም ሥራ መሥራቱን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም በፌደራልና በክልል ደረጃ ያሉ የአካል ጉዳተኛ ማህበራትን መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ እንዲደግፉ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ሂደት የጐላ ተሣትፎ እንዲኖራቸው የተቀናጀና የተደራጀ ተግባርን ማከናወን መቻሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአካል ጉዳተኞችን ድምፅ ወደ አንድ በማምጣት ጠቃሚና አካታች የሆኑ ሦስት አጀንዳዎችን ለሀገራዊ ምክክር ለይተዋል፡፡ የአጀንዳ ልየታ በተካሄደባቸው ሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የአካል ጉዳተኞችን አጀንዳ ሙሉ ለሙሉ ማስያዝ ተችሏል፡፡ በቀጣይም አጀንዳዎቹ ብሄራዊ የምክክር አጀንዳ ሆነው እንዲወጡ ፌደሬሽኑ በትኩረት ይሠራል በማለት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ አስረድተዋል፡፡