የሲዳማ ክልል የቱሪዝም መዳረሻዎች
በመሐሪ አድነው
የሲዳማ ክልልን ታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ የክልሉን ምዕራባዊ ክፍል አቋርጦ የሚያልፍ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ ሥነ-ምህዳሮች ፍል ውሃ፣ ሐይቅ የመሳሰሉ በርካታ መስህቦች ይገኛሉ፡፡ በርካታ ባህላዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦች መኖራቸው፣ የክልሉ መዲና ሐዋሣ ከተማ በፍጥነት እያደገች መምጣቷና ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የማስተናገድ አቅም በመኖሩ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ከታጩት የክልል ከተማች ውስጥ ግንባር ቀደም አድርጓታል። ከሞጆ ሐዋሣ ፈጣን መንገድ፣ የሐዋሣ አየር ማረፊያ፣ እንደዚሁም ከሐዋሣ ሙምባሳ ዓለም አቀፍ የደረቅ ወደብ መንገድ መኖራቸው የቱሪዝሙን አቅም ከፍ አድርጎታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የሲዳማ ህዝብ በርካታ ባህላዊ ቅርሶችና በዓላት ያለው መሆኑ፣ የተለያዩ ባህላዊ የዳኝነት ሥነ-ስርዐቶች ያሉት ከመሆኑም ባሻገር ክልሉ ሠላማዊ፣ እንግዳ ተቀባይና አክባሪ ህዝብ የሚኖርበት መሆኑ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምቹ መሆኑ የበለጠ መስህብ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ የጋራምባ ተራራ በክልሉ የሚገኝ ትልቁ ተራራ ነው፡፡ ይህ ተራራ የ9 ሺህ 927 ጫማ ወይም ከባህር ጠለል በላይ 3 ሺህ 368 ሜትር ከፍታ እንዳለው ይነገራል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የተራራው ከፍታ በኢትዮጵያ ደረጃ አንድ መቶ ሠባተኛ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ተራራው ከክልሉ መዲና ሐዋሣ ከተማ 9ዐ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በስተደቡብ ምስራቅ የሚገኝ ሲሆን በተራራው ሥነ ምህዳር ውስጥ የቀርከሃ፣ የጥድ፣ በአካባቢው አጠራር ጋራምቢቾ እና የተለያዩ ቁጥቋጦዎች፣ እንዲሁም ሀገር በቀል ዛፎች የተሸፈነ ነው፡፡ ከተራራው ከ7ዐ በላይ ምንጮች የሚፈልቁ በመሆኑ የአካባቢው የውሃ ማማ በመባልም ይታወቃል፡፡
በብዛት በቀርከሃ ደን የተሸፈነው የጋራምባ ተራራ በውስጡ ቀበሮ፣ የደጋ አጋዘን፣ ሚዳቆ፣ ጉሬዛ፣ ጦጣ እና ዝግጀሮ፣ ንስርና ሌሎች የዱር እንስሳት፣ አዕዋፋትና እፅዋት ይገኙበታል፡፡ በሲዳማ ክልል አርቤጐና ወረዳ ከያዬ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በታላቅ ግርማ ተጀንኖ የሚታየው የጋራምባ ተራራ እስከ ወገቡ ድረስ በሀገር በቀል ደን የተሸፈነ ከመሆኑም በላይ በብሔረሠቡ አጠራር ወሊማ የምትሰኘው ወፎችን በመሳሰሉ ብርቅዬ አዕዋፋትና የዱር እንስሳት የተሞላ ተራራ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር እንደ ሎጊታ፣ ጐሮንቲ፣ ገላና፣ ጊዳቦ እና ገናሌ ለመሳሰሉ በርካታ ትላልቅ ወንዞች መነሻ እንደሆነም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሲዳማ ክልል አግራሞትን የሚፈጥሩና የሚያስደምሙ በርካታ ወንዞችና ፏፏቴዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የሎጊታ፣ ገላና አሳሮ፣ ቦኖራ፣ ጊዳቦ እና ቂንቃሞ አስደናቂ ውበትና ልዩ የተፈጥሮ ክስተት ያላቸው ወንዞች ሲሆኑ አብዛኞዎቹ የሚመነጩት ከጋራምባ ተራራ ስር መሆኑ ነው፡፡ የሚያስደንቁ ፏፏቴዎችን ለመጐብኘት ታዲያ ተስማሚ ቦታዎች በቦና ወረዳ ወራንቻ ቀበሌ ውስጥ ያሉት የገላና እና የሎጊታ ፏፏቴዎች ካላቸው ተፈጥሯዊ ግርማ – ሞገስ አንፃርና ሁለቱም ፏፏቴዎች በአንድ ሥፍራ መኖራቸው ልብን የሚገዛ ተፈጥሯዊ ትዕይንቶች የሚታይበት በመሆኑ የጐብኚዎችን ቀልብ የሚስብ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ያደርገዋል፡፡
በሁለቱም ፏፏቴዎች መካከል የተገነባው ሎጊታ ሎጅ አካባቢውን ለሚጐበኙ ቱሪስቶች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ሎጁ የሲዳማን ባህላዊ የደጋ መንደርን ተመስሎ የተሠራ መሆኑ ከተፈጥሯዊ መስህብነት በተጨማሪ ለጐብኚዎች የሲዳማን ባህል ለማስተዋወቅ ጭምር ጥሩ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ወረዳው በጥንት ጊዜ የተገነባ ቂቄ ማሪያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የተፈጥሮ ጋዝ ያለው ምንጭ ውሃ /ሆራ/ መገኛም ነው፡፡ በንሣ ወረዳ ደግሞ የአሳሮ ቦኖራ ፏፏቴና ሌሎችም የሚገኙበት ወረዳ ሲሆን ቦኖራ ፏፏቴ በሲዳማ ክልል ትልቁ ፏፏቴ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በፏፏቴው ስር ቦኖራ ዋሻ ተብሎ የሚታወቅ ትልቅ ዋሻ ይገኛል፡፡ በሎጁ ውስጥ ቁጭ ብሎ ፏፏቴውን መመልከት የመንፈስ ደስታን ያጐናፅፋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ አዕዋፋትን ለማየትና ለእግር ጉዞ ቱሪዝም (ሃይክንግ) የሚሆን አካባቢም ነው፡፡ የሎጊታና ገላና ፏፏቴዎች ከሐዋሣና ከአዲስ አበባ በ119 ኪሎ ሜትር እና 394 ኪሎ ሜትር ተቀራራቢ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ከሎጊታ ፏፏቴ የሚፈጠረው ሃይለኛ ተፈጥሯዊ ድምፅ እና ቀስተ ደመና ያልተለመደ የውበት ስሜትና አድናቆትን ይፈጥራል፡፡
የገላና ፏፏቴ በየደረጃው ተፈጥሯዊ ፋውንቴን የሚፈጥር ሲሆን ብርቅዬ ወፎች ከነዝማሬያቸው የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎችና አስደናቂ የመሬት ገፅታዎች ልዩ ባህርያት ያሉ ቦታዎችን የያዘ ነው፡፡ ሎጊታና ቦኖራ ፏፏቴዎች ታዲያ በሁሉም ወቅቶች ለመጐብኘት የሚቻልባቸው የተፈጥሮ ገፀ በረከቶች ናቸው፡፡
More Stories
ከተጫዋችነት ተተኪ ወደ ማፍራት
“ማንበብና መፃፍ ልዩ ባህሪዬ ነው” – ነጋሽ ወልደኪዳን /ገጣሚ፣ ጋዜጠኛና ሐያሲ/
ዓላማን ያስቀደመች