ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን በጋራ በመከላከል የሸማቹን ህብረተሰብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ገለጸ፡፡
ጽ/ቤቱ ክልሉ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ባወጣው መመሪያ ቁጥር 01/2017 ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ከንግዱ ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት ጋር በሙዱላ ከተማ አካሂዷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ንግድና ገበያ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተመስገን አለማየሁ እንዳሉት፤ ህገ-ወጥ የንግድ ስርዓትን ለመከላከል እንደ ልዩ ወረዳው ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመው በቀጣይም የንግድ ልውውጥ ሂደቱ ህግን በተከተለ መንገድ ሊመራ ይገባል።
የንግዱን ማህበረሰብ ከፀረ ንግድ ውድድርና ተገቢ ካልሆነ የግብይት ሂደት በመታደግ ሸማቹን የሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች እንዳይፈፀሙ ከማድረግም በላይ ተፈጽሞ ከተገኘም ወጥነት ያለውን አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ የሸማቹን ደህንነት ለመጠበቅ ይሰራል ነው ያሉት።
አቶ ተመስገን አክለውም የንግዱ ማህበረሰብ መመሪያው ፍትሐዊ የገበያ ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ አጋዥ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ህገ-ወጥ የንግድ ስርዓትን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ወልደየሱስ መኮንን በበኩላቸው፤ የንግዱ ማህበረሰብ ህጋዊ የግብይት ስርዓትን በመከተል መመራት እንዲቻል መመሪያው ጉልህ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቁመው ነጋዴው ህጋዊ ፍቃድ ባወጣው ስራ ላይ ብቻ በመሰማራት ለህገ-ወጥ የንግድ ቁጥጥር ስራ ተባባሪ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የንግድ ፍቃድ እድሳት በኦንላይን እስከ ታህሳስ 30/2017 ዓ.ም ድረስ መጠናቀቅ እንዳለበት አንስተው የንግዱ ማህበረሰብ በወቅቱ በማሳደስ ህጋዊ መሆን እንደሚጠበቅበት እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላት መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም ግብረሃይሉ በአግባቡ ተግባራቱን እንደሚያስፈጽም ገልፀዋል።
የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ፀሐይ ሀንቆሬ፤ መመሪያው ነጋዴው መብቱንና ግዴታውን ተረድቶ እንዲሰራ ተግባሩን እንዲፈጽም የሚረዳ እንደመሆኑ በዘርፉ የግንዛቤ ስራዎች እየተሰሩ ህብረተሰቡን ህገ-ወጥ የንግድ ስርዓትን ተከትለው ከሚመጡ እንግልቶች መታደግ እንዲቻል በቅንጅት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ መመሪያው ለፍትሐዊ የንግድ ስርዓት አጋዥ መሆኑን ጠቁመው የግንዛቤ ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በጎፋ ዞን በያዝነው በጀት ዓመት ከ117 ሺህ በላይ አባወራዎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ
ከመማር ማስተማር ተግባሩ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ጥረት ቢደረግም በተፈለገው ልክ እየተከናወነ አለመሆኑን የቱም ኮንስትራክሽን እና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ መምህራን ተናገሩ
ጳጉሜ 2 የሪፎርም ቀን “ሪፎርም ለላቀ አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል በኣሪ ዞን ጂንካ ከተማ የዞንና የክልል አመራሮች በተገኙበት ወይይት ተካሂዷል።