የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው በራስ አቅም ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ ሲቻል እንደሆነ ተጠቆመ

የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው በራስ አቅም ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ ሲቻል እንደሆነ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ታህሳስ 04/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) የልዩ ወረዳውን የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው በራስ አቅም ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ ሲቻል ነው ሲሉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ ገለፁ፡፡

በልዩ ወረዳው የ2017 በጀት አመት ተሻሽሎ የቀረበው አዲሱ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያና የግብርና ስራ ገቢ ግብር አሰባሰብ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በወረዳው በፍቃዶ ቀበሌ ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞሳ ኢዶሳ እንደገለፁት፤ በልዩ ወረዳው ተሻሽሎ በቀረበው በአዲሱ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያና የግብርና ስራ ገቢ ግብር አሰባሰብ ዙሪያ በየደረጃው ለሚገኙ ግብር ከፋዮችና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀትና የጋራ ተግባቦት በመፍጠር ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡

የልዩ ወረዳውን የልማት ፍላጎት ማሟላት የሚቻለው በራስ አቅም ግብር በአግባቡ መሰብሰብ ሲቻል መሆኑን የጠቆሙት ዋና አስተዳዳሪው፤ አርሶ አደሩ የሚጠበቅበትን የመሬት መጠቀሚያና የግብርና ስራ ግብር በአግባቡ በመክፈል የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል፡፡

በዚህም በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ቀጣይነት ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ ሞሳ ግብርን በወቅቱና በታማኝነት መክፈል ከራስ ወደ ራስ መሆኑንም ገልፀዋል።

በልዩ ወረዳው አዲሱ የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያና የግብርና ስራ ገቢ ግብር አሰባሰብ ለማስጀመር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት ስራ ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ደግሞ የልዩ ወረዳው ገቢዎች ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ በሀሩ ዲጋ ናቸው፡፡

ማህበረሰቡ በየደረጃው የሚያነሳቸው የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች መመለስ የሚቻለው ከግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ከሚሰበሰበው ግብርና ታክሲ መሆኑንም ሃላፊው ገልፀዋል፡፡

በልዩ ወረዳው በጀት አመቱ ከገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያና ከግብርና ስራ ከ28 ሚልየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አቶ በሀሩ አስረድተዋል፡፡

የሚጠበቅባቸውን ግብርና ታክስ በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት በመቻላቸው ትልቅ ኩራትና ደስታ እንደተሰማቸው በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ግብራቸውን የከፈሉ የልዩ ወረዳው አርሶአደሮች ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ተገኝተው የሚጠበቅባቸውን የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያና የግብርና ስራ ገቢ ግብር ለከፈሉ አርሶ አደሮች የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን