የአምራች ዘርፉን የመቀላቀል ውጥን
በደረሰ አስፋው
“ዛሬ ላይ በአንድ የስራ መስክ ላይ ብቻ አይንን መጣል ዘላቂ ጥቅም አያስገኝም። አዋጭ የስራ መስኮችን መቃኘት ጠቃሚ ነው፡፡ በሀገራችን ገና ያልተነኩ የስራ መስኮች በመኖራቸው ይህን ዕድል መጠቀም ይገባል። አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦችን በማመንጨት መስራት ከግለሰብ አልፎ ለሀገርም ጠቃሚ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል” ስትል ነው ሀሳቧን የጀመረችው።
ለዚህም አብነት አድርጋ የምታነሳው በሀገራችን ያለውን የቀርከሃ ምርትን ነው፡፡ እንደዛሬ በቀርከሃ ሥራ ላይ ከመሰማራቷ በፊት በአካባቢዋ በአይን ከማየት ውጭ እንዲህ ጥቅም ይሰጣል የሚል ሀሳብ አልነበራትም፡፡ በስልጠናና ከኢንተርኔት ያገኘችው ዕውቀት ግን አይኗን የከፈተላት መሆኑን ታነሳለች። ይህ ተክል በአግባቡ ቢሰራበት ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑንም መረዳት ችላለች፡፡ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ብዙ ፋይዳ ያለው እንደሆነ በመጠቆም፡፡
ቀርከሃ በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ይበቅላል፡፡ በዓለም ቀርከሃ በስፋት ከሚበቅልባቸው ሀገራት መካከልም ሀገራችን ተጠቃሽ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ምርቱ ብዙ ጥቅም ያልሰጠ ተክል እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ለአጥር፣ ለቤት መስሪያ ወይም ለማገዶነት ሲጠቀሙበት ከማየት ወጪ ለሌላ ዓላማ ሲውል ማየት የተለመደ አይደለም፡፡ በሰዎች ዘንድም ይህን ያህል ጥቅም ይሰጣል የሚል አመለካካት የለም፡፡
በቅርቡ ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ጎራ የማለት ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ በከተማው አንድ አዲስ ክስተት ተመለከትኩ፡፡ ይህም የቀርከሃን ታሪክ የሚለውጥ ነው፡፡ በቀርከሃ የተለያዩ ግብአቶችን የምታመርት ሴት አገኘሁ፡፡ ወደ ሱቋ ዘለቅ ስልም በተለያዩ ዲዛይኖችና መጠን የተዘጋጁ የቀርከሃ ቁሳቁሶች ተደርድረዋል፡፡ አይንን በሚማርክ መልኩ ለሽያጭ የተዘጋጁ ግብአቶች ይታያሉ። ከመለኛዋ ጋር አጭር ቆይታ አድርግን ሀሳብ ተለዋወጥን፡፡
በቀርከሃ ምርት ላይ በርካታ መገልገያዎችንና ጌጦችን ለመስራት ዕቅድ እንዳላት ነው መረዳት የቻልኩት፡፡ በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ የቀሰመችው ዕውቀት ደግሞ መነሳሳትን ፈጥሮላታል፡፡ ይህ አነስተኛ ግብአቶችን በማምረት የተጀመረው ስራዋ እንደሚያድግ ነው ፍንጭ የሰጠችኝ፡፡ በተለይ ከልማት ባንክ ጋር የፈጠረችው ግንኙነት የማደግ ተስፋዋን ያለመለመ እንደሆነ ነው ከሀሳቧ መረዳት የቻልኩት፡፡ እቱ መለኛዋ በዚህ ስራ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የስራ ዕድል የመፍጠር ውጥን እንዳላትም በመጥቀስ፡፡
ሙሉነሽ ብሩ ትባላለች፡፡ በአርባ ምንጭ ከተማ ነጭ ሳር ቀበሌ ውሃ ምንጭ ቀጠና ነዋሪ ናት፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በኩልፎ 1ኛ ደረጃ፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በጨንቻ ከተማ ጨንቻ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ11ኛ አስከ 12ኛ ክፍል ተምራለች፡፡ ከ12ኛ ክፍል በኋላም አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው ዩኒየን ኮሌጅ በአካውንቲንግ የትምህርት ዘርፍ በዲፕሎማ ተመርቃለች፡፡
ዛሬ የተሰማራችበትን የቀርከሃ ስራ ከመጀመሯ በፊት በአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር በኢንተርፕራይዝ ተደራጅታ በአረንጓዴ ልማት ትሰራ እንደነበር ታነሳለች፡፡ ይሁን እንጂ ስራው አዋጭ ባለመሆኑ ከማህበሩ ራሷን አግልላ በአርባ ምንጭ ሴቶችና ህጻናት ጽ/ቤት በነጻ አገልግሎት ስትሰራ ቆይታለች፡፡ በዚህ ወቅት የገቢ ምንጭ ስላልነበራት በኑሮዋ ተጽእኖ መፍጠሩ አልቀረም። የገቢ ምንጭ ፈጥራ የጓዳዋን ጉድለት መሙላት አለመቻሏ ያሳስባት እንደነበር ገልፃለች፡፡
በዚህ ህይወት ውስጥ እያለች በከተማው የሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት ስራ የሌላቸውን ዜጐች ወደ ሥራ ለማሰማራት ያወጣውን መሥፈርት አሟልተው ካሰባሰባቸው 90 ሴቶች መካከል አንዷ እሷ ነበረች። ድርጅቱም ለ10 ቀናት የህይወት ክህሎት ስልጠና በመስጠት በተለያዩ የስራ ዘርፎች እንዲሰማሩ አደረገ። በዚህም ወደ ቀርከሃ ስራ መግባት እንደቻለች ነው የተናገረችው፡፡ በስልጠና ካገኘችው እውቀት በተጨማሪ ኢንተርኔት በመጠቀም እውቀቷን ማሳደግ እንደቻለች ታነሳለች፡፡ ይህ በቀርከሃ ምርት ላይ ያለው አቅም ውስጧን ማረከው፡፡
በዚሁ ስራ ስትገባ መነሻ ካፒታሏ 55 ሺህ ብር እንደነበር አንስታ የከተማው ሴቶችና ህጻናት ጽ/ቤትና የቀበሌ አመራሮች በበጀት ደግፈዋታል፡፡ ለስራዋ የመስሪያ ቦታ በመስጠትም ህልሟ አውን እንዲሆን ካደረጉት መካከልም ተጠቃሽ እንደሆኑ በመግለጽ፡፡ የቀርከሃ ስራ ውጤታማነትን በመረዳት ሌሎች ድርጅቶችም ማሽኖችን በመለገስ በስራዋ ውጤታማ እንድትሆን ድጋፍ ማድረጋቸውን ታነሳለች፡፡
በቀርከሃ ሆቴል ቤቶችና መዝናኛ ስፍራዎች የሚሰቀሉ ጌጣጌጦችን ታመርታለች። በተጨማሪ ቀርከሃን በመጠቀም ቤትን ማስዋብም ሌላው ስራዋ ነው፡፡ የመቀመጫ ወንበሮችን፣ መደርደሪያዎችና ጠረጴዛዎችን በተለያዩ ዲዛይኖች ታዘጋጃለች። ለቤተሰብ በስጦታ መልክ የሚሰጡ ፓኬጆችን አዘጋጅታም የሥራ አድማሷን አሥፍታለች። አበባ ማስቀመጫ እና ሌሎችም የቀርከሃ ስራዎችን በስፋትና በአይነት ታመርታለች፡፡ ዛሬ ላይ ይህ ስራ ከስራ አጥነት አላቋት የስራ ባለቤት አድጓታል። በህይወቷም ተጨባጭ ለውጥ አምጥታበታለች። ይህንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ነው የዘወትር ምኞቷ፡፡
ቀርከሃ ያልተሰራበት የሀገራችን ሀብት ነው የምትለው ሙሉነሽ በዚህ ዘርፍ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በኩልም የእሷ ጅምር ስራ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጻለች። በከተማው በሚዘጋጁ ባዛሮች ምርቷን ይዛ በመቅረብ የቀርከሃን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት ለማየሳት ዕድል ፈጥሮላታል፡፡ ህብረተሰቡም ምርቶችን ከመግዛት ባለፈ ጥሩ አስተያየት እንደሚሰጣት ትናገራለች፡፡ በማኔጅመንትም በመጀመሪያ ዲግሪ እየተማረች እንደሆነና በመጭው ዓመት እንደምትመረቅ የገለጸችው እቱ መለኛዋ ይህም ስራዋን በአግባቡ ለመምራት እንደሚያግዛት ነው ተስፋ ያደረገችው፡፡
አሁንም ቀርከሃ የሚሰጠው አገልግሎት በውል ያልታወቀ በመሆኑ ይህን ከመስራት እንደማትቦዝን ታነሳለች፡፡ ቀርከሃ ከጓዳ ወጥቶ ወደ ሳሎን እና ወደ ተለያዩ አገልግሎቶች በማዋል የምርቱን አስተዋጽኦ ማጉላት ይገባል ስትልም አስተያየቷን ትሰጣለች። በአሁን ወቅት የገበያውን ተደራሽነት ማስፋት ከተቻለ በኢንተርኔት በምታገኘው መረጃ መሰረት ብዙ ነገር ለመስራት ዕቅድ እንዳላት ትገልጻለች፡፡
የተለያዩ ግብአቶችን ከማምረት ባለፈ በቅርቡም ቀርከሃን በጥሬ እቃነት በመጠቀም እስቲኪኒ ለማምረት እየተዘጋጀች ነው፡፡ ለዚህም ይረዳት ዘንድ ከልማት ባንክ ብድር ማግኘት የምትችልበት አሰራር እየተዘረጋ ነው፡፡ የልማት ባንክ ከፍተኛ ኃላፊዎችም ጉብኝት በማድረግ ሀሳባቸውን እንደለገሷት ተናግራለች፡፡
“የቀርከሃ ምርት በአቅራቢያ በሚገኙ በገረሴ፣ ጨንቻና ቦንኬ በስፋት እንዳለ ታነሳለች፡፡ ወደ ስራ ብትገባ የጥሬ ዕቃ እጥረት እንደማይገጥማትም በጥናቷ ማረጋገጧን ነው የተናገረችው፡፡ ቀርከሃን መትከል እንደ ሀገርም ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው። የአየር ጸባይን በመለወጥ፣ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ጉልህ አገልግሎት አለው፡፡ ይህን ምርት የስራ ዕድል መፍጠሪያ ማድረግ ከተቻለ ደግሞ በርካቶችን የስራ ባለቤት ያደርጋል፡፡ ተክሉም ትኩረት እንዲደረግበት ዕድል ይፈጥራል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ማግኛም ይሆናል፡፡
“በአሁኑ ወቅት የቀርከሃ ስራ ወደ ማህበረሰቡ እየገባ ነው፡፡ ገበያው ጅምር ቢሆንም ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር ፈጥሬያለሁ። የመንግስት ተቋማት ዘንድ በመሄድም ምርቱን እያስተዋወቅኩ ነው። ቤት ለቤት በመዞርም የመሸጥና ምርቱን የማስተዋወቅ ስራ እሰራለሁ፡፡ በአካባቢው የሚመጡ ጎብኝዎችንም የገበያ ዕድል ለማድረግ ጥረት አደርጋለሁ፡፡
“በኢትዮጵያ በገጠርም ይሁን በከተማ ሴቶች ያልተሻገሩት ችግር አለ፡፡ የቤት ውስጥ ስራ እየሠሩ መኖር፡፡ ወልዶ ልጅን ለማሳደግ ብቻ የተፈጠረች አድርጎ የማሰብ ዝንባሌ አሁንም ያልተፈታ ችግር ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ ሴቷን ለጉስቁልና እየዳረጋት ይገኛል፡፡ መንግስት ለሴቶች ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ይህን እድል መጠቀም ደግሞ ከሴቶች ይጠበቃል። ከቤት ወጥተው ከህብረተሰቡ ጋር መገናኘት፣ የገበያውን አማራጭ መረዳትም በራሱ ውጤት ነውና ከቤት ሊወጡ ይገባል፡፡
“የቀርከሃ ስራ በቤት ውስጥም በቀላሉ የሚሰራ ነው፡፡ በቤት ውስጥ እንደ ጥጥ ፈተላ የሚታይ ነው፡፡ ከተሰራበት ሀብት የሚገኝበት ነው፡፡ አዲስ አበባ የቀርከሃ ምርት በውድ ነው የሚሸጠው፡፡ እዚህም ቢሆን ምርቱ ከተዋወቀ ውጤታማ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ጥሬ እቃው በእጃችን ነው የሚገኘው” ስትል ስለ ቀርከሃ ጥቅም ታብራራለች፡፡
አንድ ትልቅ ቀርከሃ እስከ 120 ብር እንደምትገዛ ገልጻ ይህ ወደ ምርት ሲገባ በርካታ እቃዎችን ማምረት እንደሚያስችል ትናገራለች፡፡ ስራውም አዋጭ መሆኑን እንዲሁ ከቀርከሃ ተክል ጋር ለበርካታ ዓመት ቁርኝት እንዳላት የገለጸችው ሙሉነሽ ለሴቶች በቀላል መሳሪያ በቢላዋ በመሰነጣጠቅ የተለያዩ ምርቶችን በማምረትና በመሸጥ ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ትመክራለች፡፡
ወደ ስራው ስትገባ በጥናት ላይ ተመስርታ ባይሆንም ከስልጠናና ከኢንተርኔት ካገኘችው እውቀት አዋህዳ የጀመረችው የቀርከሃ ስራ ውጤታማ እያደረጋት መሆኑን ነው ያጫወተችን። አሁን ያላትን አቅምም ለማሳደግ ከሌሎች ባልደረቦቿ ጋር በተለያዩ ስፍራዎች የልምድ ልውውጥ እንድታደርግ እንዳገዛትም ታነሳለች፡፡ ወደ ሀዋሳ እና አዲስ አበባ በመሄድ የልምድ ልውውጥ አድርጋለች፡፡ በዚህም ዘርፉ ያልተነካና ሀገርንም የሚለውጥ የስራ ዘርፍ እንደሆነ መገንዘብ እንደቻለች ነው የተናገረችው፡፡ በተለይ ስራው ለሴቶች ምቹ መሆኑን በመግለጽ፡፡
ለጣውላነት የሚያገለግሉ ጽድ፣ ዋንዛ፣ ዝግባና ሌሎች ሀገር በቀል የሆኑ እጽዋትንም የሚታደግ ነው የቀርከሃ ተክል፡፡ በነዚህ ተክሎች የሚሰሩ ግብአቶችን ሊተካም የሚችል ነው፡፡ በፍጥነት የሚያድግ ተክል በመሆኑ የደን መመናመንን በመቅረፍም አስታዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ተክል እንደሆነም ተናግራለች፡፡
ልማት ባንክ የጀመረችው የቀርከሃ ስራ እንዲያድግ እንደሚፈልግ የምታነሳው ሙሉነሽ እስከ ስራ ቦታዋ ድረስ በመምጣት የማማከር ስራ መስራቱን ነው የገለጸችው። የማሽን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱንም እቱ መለኛዋ ጠቁማለች፡፡ ለዚህም ከሚመለከተው አካል ፍቃድ የማውጣት፣ የቦታ ጥያቄ በማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየሰራች መሆኑን ገልጻለች፡፡
More Stories
“የአካል ጉዳተኞችን የመሪነት ሚና በማጉላት አካታችና ዘላቂ ልማትን እናረጋግጣለን!”
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ