እርቅ

በይበልጣል ጫኔ

በሀገራችን ከሚታወቁ ጠቃሚ ባህሎች አንዱ የሽምግልና ስርዓት ነው። ሽማግሌ የተጣላን ያስታርቃል። የተፈቃቀደንም ያጋባል። አንዲህ ሲባል ግን አጋቡ ሲባሉ ግራ የሚያጋቡ÷ አስታርቁ ሲባሉም÷ የሚያራርቁ መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። የዚህ ዓይነት ሽማግሌዎች የሽምግልናን በጎ ገፅ ጥላሸት የሚቀቡ ናቸው።

ሽምግልና የተሳካ እንዲሆን የአስታራቂዎቹ ብልህ እና አስተዋይ መሆን አስተዋፅኦው የጎላ ነው። ታራቂዎቹም ቢሆኑ ሰከን ማለት እና ማሰብ ይኖርባቸዋል። “ስትጣሉ እንድትታረቁ ሆናችሁ ተጣሉ” የሚባለው እኮ ለዚህ ነው።

አንዳንዱ ሰው ሲጣላ÷ ነገ መታረቅ እንደሚኖር ይረሳዋል። በስሜቱ ይሸነፍና ብዙ ያወራል። ሰው ፊት መባል የማይገባውን ነገር ሁሉ ይላል። የጋራ ምስጢራቸውን አደባባይ ላይ ይዘረግፈዋል። የኋላ ኋላ የስሜታዊነቱ ጊዜ አልፎ ሰከን ብለው ሲነጋገሩ ትርፉ ፀፀት ይሆናል። አይመለስ ነገር ወደ ኋላ÷ “ከአፍ የወጣ አፋፍ” ነው ነገሩ።

አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነላችሁ። ባልና ሚስት ከመጋባታቸው በፊት÷ ለወሬ የማይመች ቦታ ነው የተገናኙት። አንድም በውበቷ ተማርኮ÷ በሌላ መልኩም ሃሳብ ለሃሳብ ተግባብተው ወደ ቤቱ ይዟት መጣ። ዋለች። አደረች። ሚስቱ ሆነች።

በዚህ ሁኔታ ጊዜያት አለፉ። እነሱም በፍቅር ከነፉ። “አሁን ይህቺን ሚስት ትሆነኛለች ብሎ ነው ያገባት?” የሚሉና መሰል ሽሙጦችንም እንዳልሰማ አለፉ። ልጅ መጣ። ትዳራቸው የሚቀናበት ዓይነት ሆነ።

ከቀናት መካከል በአንዱ ፍቅራቸው በጠብ ተለወጠ። ነገራቸው ጎረቤት እስኪያየው አገጠጠ። እዚህ ጋ “ታድያ ምን አዲስ ነገር አለ?÷ ባልና ሚስት ይጋጫል÷ ይታረቃል”÷ የሚል አንባቢ ቢኖር÷ አዲሱ ነገር የመጣው ከዚህ በኋላ ነው።

ወግ ነውና ጎረቤት ሰብሰብ ብሎ ሽምግልና ያዘ። ተበደልኩ ባዩ ባልየው ነበር። ተናገረ ብዙ። ተራው የሚስት ሆነና÷ እሷም መናገር ጀመረች። አፋቸውን ያዙ ሽማግሌዎቹ። ብዙ የተበደለችው እሷ ናት። ብዙ የተገፋችው እሷ ናት። ግን ዝም ብላ እየኖረች ነበር። ባልየው ተበደልኩ ብሎ አደባባይ አወጣት። እንዲህ ነው እኮ “ተበዳይ ዝም ሲል ተከሳሽ ይሆናል” ማለት። በዚህም ደስተኛ አይደለችም። ግን ጉዳዩ አንዴ ተነስቷልና የከረመ ብሶቷን ሁሉ ዘረገፈችው። ችግሩ የተፈጠረው ይኼኔ ነው። ሰውየው ከአፉ ከባድ ነገር አወጣ። አወጣ ከምለው አፈነዳ ብለው ይቀለኛል፦

“ከየት እንዳነሳሁሽ ረሳሽው እንዴ?” አላት ሚስቱን።

መብረቅ የወደቀባት መሰለች። እውነት ነው ያለፈ ህይወት ነበራት። እውነት ነው መጥፎ ታሪክ ነበራት። ቀን ነው እዚያ የከተታት። ደግሞ ቀን ቀና አደረጋት። ያለፈ ታሪኳን ረስታው ነበር። አሁን ባለትዳር ናት። የተከበረች ወይዘሮ። ሌላው ሁሉ የረሳውን ታሪክ የገዛ ባሏ አስታወሳት። አስታወሳት እና አሳመማት። እሷ በምላሹ፦

“አንተስ ምን ስታደርግ አገኘኸኝ?” አለችው።

መልስ አልነበረውም። ቀላሉን ነገር አወሳሰበው። የሽማግሌዎቹን ስራ አከበደባቸው። ቅድሚያ ሲገፋት ኖረ። በኋላ ደግሞ ገፍትሮ አስወጣት። እሷ ስትወጣ ደስተኛ የሚሆን መስሎት ነበር። ግን ኑሮው ካሰብው ተቃራኒውን ሆነበት። ለዚህ ነው “ስትጣሉ መታረቅ መኖሩን አትርሱ” የሚባለው።

የሆነ ጊዜ ደግሞ አንድ ወዳጃችን ሳተ። ከፈረሱ ጋሪው ቀደመና ጓደኛው አረገዘች። ይኼንን ለቤተሰብ መንገር በጣም ከባድ ነበር። እዚህ ጋ ነገሩን በጣም የሚያከብደው ሴቷም ወንዱም ተማሪዎች መሆናቸው ነው። የሆነው ሆነና ቤተሰብ ጋ ሽማግሌ ልከው አብረው ለመኖር ወሰኑ። በውሳኔያቸው መሰረትም ሽማግሌ መራርጠው ላኩ። 

የተላኩት ሽማግሌዎች ሴቷ ቤተሰቦች ጋ ሄደው እንደ ባህሉ ቀጠሮ ተቀብለው መጡ። በመኃል ግን አንደኛው ሽማግሌ ተመልሰው ሄደው፦

“እናንተ ግን ያማችኋል?÷ ምን ብላችሁ ነው ይኼንን ሽምግልና የተቀበላችሁት?÷ በምኑ ያኖራታል ብላችሁ ነው?÷ … ወይስ ልጅቷን ጠልታችኋታል…” ብለው ቤተሰቦቿን ግራ አጋቧቸው።

የልጅቷ ቤተሰቦች የልጃቸው ነፍሰጡር መሆን ክብረ ነክ ሆኖባቸዋል። አንድ ላይ ይሁኑና ደጋግፈን እናቋቁማቸዋለን የሚል ሃሳብ ነበራቸው። ዳሩ ምን ያደርጋል?÷ አጋቡ የተባሉት ሽማግሌ ግራ አጋቧቸው።

በነገራችን ላይ÷ በዚያ ሰዓት ሽማግሌው ልክ ነበሩ የሚሉም አልታጡም። “እውነታቸውን ነው ታድያ በምኑ ያኖራታል?” የሚል መከራከሪያ እያነሱ። እንዲያም ቢባል ገና ጉዳዩ ተነግሯቸው ሂዱ ሲባሉ፦

“ለመሆኑ በምን ልታኖራት አስበህ ነው?” ቢሉ÷ ጥያቄያቸው ቦታውን ያገኝ ነበር። ወይ ደግሞ እንደ አባት፦

“አንድ ጊዜ ስህተት ተፈጠረ ብላችሁ ለመጋባት ከምትወስኑ÷ በየቤተሰቦቻችሁ ጋ እደጉና ጋብቻው በኋላ ይደርሳል” ቢሉ÷ ተደመጡም አልተደመጡም ትክክል ይሆኑ ነበር። እሳቸው ግን አካሄድ አበላሹ። ለሳቸው ሌላ ሽምግልና ተይዞ ከሽምግልናው ተሰረዙ። ሽበት ያለው ሁሉ ሽማግሌ እንደማይሆን የገባኝ በዚህ ጊዜ ነበር።

ከሁሉ በላይ የሚያስገርመኝ ግን÷ ሁለት ወንድሞቹን ለማሸማገል የተቀመጠው ሰውዬ ጉዳይ ነው። ወንድሞቹ ተቀያይመውበት ተቸግሯል። የአንደኛው ወንድሙ ራስ ወዳድነት ነው ሁለተኛውን ያስቀየመው። እርግጥ ራስ ወዳድ ነው ባልኳችሁ ሰው አሸማጋዩም በደል ደርሶበታል። ግን ደግሞ ወንድምነቱን አስበልጦ÷ በደሉን ናቅ አድርጎ ትቶታል።

ወንድሞቹን ለማሸማገል ሲያስብ÷ አንድ ላይ ካነጋገራቸው የባሰ ነገሩ ይበላሻል ብሎ በማሰብ ለየብቻ አገኛቸው። ቅድሚያ በዳይ የተባለው ጋ ሄዶ፦

“የፈለገ ነገር ቢልህ ችለህ ይቅርታ መጠየቅ አለብህ” ብሎ አሳመነው።

ደግሞ በተራው ተበዳዩ ጋ ሄዶ ጉዳዩን ሲያነሳበት÷ ያኛው ተማረረ። “ወንድም አለኝ ብዬ ሽምግልና አልቀመጥም” ብሎ አመረረ። ቢለው ቢሰራው አልሰማ ስላለው አሸማጋዩ ተናዶ፦

“አንተ ግን እንዴት ነው አልታረቅም የምትለው?÷ መበደልህን አውቃለሁ። ለመሆኑ ግን ከኔ በላይ ተበድለሃል?” አለ በስሜት።

አልታረቅም ባዩ ነቃ ብሎ ማድመጡን ቀጠለ። “አንተ ደግሞ ምን ተበደልክ?” በሚል ጥያቄያዊ እይታ ወንድምዬው ነገሩን እንዲቀጥል አበረታታው።

አስታራቂውም በወንድምየው የደረሰበትን በደል መዘርዘር ጀመረ። አላስተዋለውም እንጂ ከተናጋሪው በላይ አድማጩ ስሜታዊ እየሆነ ነበር። ሁሉን በዝርዝር ካደመጠ በኋላ፦

“ታድያ ከዚህ ጋር ነው እንዴ ላስታርቅህ የምትለኝ?÷ እንደውም ያለበት ሄደን እናጋጨው” ብሎ ሲወጣ÷ አስታራቂው ዱላ ይዞ ተከተለው። ለዚህ እኮ ነው አስታራቂ ከስሜት የራቀ መሆን አለበት የሚባለው።

ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ የተጣላ ሲያስታርቁ የኖሩ አንድ አባት ነበሩ። ብልሃታቸው ያስቀናል። ለመገዳደል የሚፈላለጉ እንኳን ቢሆኑ÷ እሳቸው ጋ ከደረሱ ይታረቃሉ። በእርቅ ሂደት ውስጥ ስላጋጠሟቸው ጉዳዮች ሲነግሩኝ፦

“አንዳንዱ ሰው አስቸጋሪ ነው” ይላሉ።  በእርቅ ሂደት የገጠሟቸውን ሰዎች በማስታወስ።

ሰውዬው ነው አሉ። አንዲት ፍየሉ በመኪና አደጋ ሞተችበት። ሹፌሩ መኪናውን አቁሞ እርቅ ተያዘ። ተጎጂው ካሳ ይከፈለኝ አለ። ሹፌሩም ትገመትና እከፍላለው አለ። ሁለቱም እንዲህ ከተስማሙ ጉዳዩ አልቋል÷ ሊል ይችላል ተመልካች።

ተበዳዩ “ፍየሌ በዘሯ መንታ ነው የምትወልደው” አለ። እሷ እስከ ስንት አመቷ እንደምትወልድ አስቦ÷ እንደገና የሷ ግልገሎች የሚወልዱትን አስልቶ የብዙ ፍየል ካሳ ጠየቀ። አካሄዱ ከባድ ስለነበር ባይሆን አስተያየት አድርጎ የግልገሎቹን ቁጥር እንዲቀንስ ተደርጎ ተካሰ÷ አሉ ሰውዬው። ነገርዬው ካሳ ተቀበለ ከማለት ዘረፈ ለማለት ይቀርባል።

አሰብኩት እኮ÷ ይኼ ሰውዬ ፍየል ሊሸጥ ገበያ ቢወጣ። የያዛትን ፍየል ወደፊት ከምትወልዳቸው ግልገሎች ጋር አስቦ ዋጋ መጠየቁ አይቀሬ ነው። ዳሩ ገበያ በራሱ ይወስናል እንጂ÷ እንደ ሹፌሩ ተገዶ የሚከፍልበት አማራጭ አይኖርም።

“ሁሉንም ሰው መጥፎ አድርጎ ማሰብ ግን ጥሩ አይደለም”÷ ይላሉ ሰውዬው÷ በመኪና አደጋ ልጁን ያጣውን ሰውዬ የእርቅ ሂደት በማስታወስ፦

ሰውዬው ልጁ በመኪና ተገጨበት። በዚህም ምክንያት ሃዘኑ ከባድ ሆነ። ከቀናት በኋላ ለሽምግልና ተቀመጡ። ሹፌሩ አንድ እርቅ ፈፅሞ÷ በሌላ መልኩም ካሳ ከፍሎ ነፃ ለመውጣት ተዘጋጅቷል። ለፍየል ከነ ልጅ ልጆቿ (ያውም ላልተወለዱት) ካሳ በሚጠየቅበት ሀገር÷ በቀላሉ እንደማይለቁት ገምቷል። ተጎጂው አባት ተነስተው፦

“ይኼ ሹፌር ከቤቱ የወጣው ለስራ ነው። የኔም ልጅ ከቤቱ የወጣው ለጉዳዩ ነው። አይተዋወቁም። የከረመ ቂም የለባቸውም። ሟች እና ገዳይ አድርጎ ያገናኛቸው አጋጣሚ ነው። ስለዚህ ይቅር ብዬዋለሁ። በሰላም ወደ ስራው ሂድ” ብለው አሰናበቱት÷ አሉኝ። እንዲህ ዓይነት ታሪክ ስሰማ ውስጤ ሃሴት ያደርጋል።

ለማንኛውም ግን ስትጣሉ እንድትታረቁ ሆናችሁ ተጣሉ። በህይወት ገፅ ላይ ታራቂ ብቻ ሳይሆን አስታራቂ ሆኖ መገለጥም ይመጣልና ብልህ፣ አስተዋይ እና ከስሜት የራቀ መሆንም ይገባል።