የ 50 ብሯ ትዝታ
በአንዱዓለም ሰለሞን
የዛሬው ወግ መነሻ የፕላስቲክ ዕቃ መያዣ መከልከሉን ተከትሎ የገጠመኝ ነው፡፡ አንድ ቀን የአከራዬ ልጅ መጣችና፡-
“የማይጠቅም ወረቀት አለህ?” ማለት፡፡
“የማይጠቅም ስትይ?” እየሳቅሁ ጠየኳት።
“ለሱቅ ዕቃ መጠቅለያ ፈልጌ ነው፡፡”
በወቅቱ አጠገቤ የነበረችውን የባለቤቴ ዘመድ እንድትፈልግላት ነገርኳት፡፡ ከሰጠቻት ወረቀቶች ውስጥ መሀል ሁለት ደብተሮች ስላየሁ፣ ተቀበልኳትና ተመለከትኳቸው። አንደኛው የእሷ የበፊት ደብተሯ ነበር፡፡ ሌላኛው ለእኔ የትዝታ ምክንያት፣ ለእነርሱ ግን ምናልባትም የቅርስ ያህል ነበር፡፡ እነሱ የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው፡፡ የእኔን ትዝታ የቀሰቀሰው ደብተር ደግሞ የእኔ የ11ኛ ክፍል ደብተር! አስቡት ከዛሬ 20 ዓመት በፊት የነበረ ማለት ነው፡፡
ሁለቱም ፊት ላይ መደነቅን ተመልክቻለሁ፡፡ መደነቅ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ግራ የመጋባት ስሜትም ፊታቸው ላይ አስተውያለሁ፤ ‹ምን ሊያደርግለት ነው እስከዛሬ ያስቀመጠው?› የሚል የጥያቄ ምልክት ፊታቸው ላይ ተስሎ እንዳየሁም አልተጠራጠርኩም፡፡
የልጄ የአግራሞት ስሜት ግን የተለየ ነበር። የደብተሩ ሽፋን ላይ ስሜን እና “11ኛ C” የሚለውን ጽሁፍ ሲያይ ፊቱ ላይ የተዘበራረቀ ስሜት ይስተዋል ነበር፡፡ ደብተሩን እየገለጠ ሲመለከት፣ የፊቱ ገጽታም ከገጾቹ መገለጥ ጋር አብሮ ይቀያየር ነበር፡-
“እጅ ጽሁፍህ ያምራል!” አለኝ ትክ ብሎ እየተመለከተኝ፡፡ ከዚያ ገጾቹን በጥንቃቄ እየገለጠ መመልከቱን ቀጠለ፡፡
አጋጣሚው ለእኔ ጥሩ ነበር፤ እግረ መንገዴን መጽሀፎቹንና ደብተሮቹን በጥንቃቄ እንዲይዝ የምመክርበት፡፡
በእርግጥ ይህን ቀድሜም አድርጌው ነበር፡፡ የመጀመሪያ ቀን በአግባቡ የተጠረዙ የዘጠነኛ ክፍል የፈተና ወረቀቶቼን ነበር ያሳየሁት፡፡ ስሜቱ ልዩ ነበር፡፡ ይህ ለእሱ የተዓምር ያህል ነበር፡፡ ግን ደግሞ እሱም ለራሱ ነገሮች ጥንቃቄ እንዲያደርግ ከቃላት በላይ በተግባር ያስተማርኩበት አጋጣሚ ሆኖልኛል፡፡
ልጆች በአንደበታችን ከምንናገረው ይልቅ፣ የምናደርገውን የበለጠ ያምናሉ፣ ይቀበሉታልም፡፡ በልባቸው ጽላት የሚጽፉት ከምናወራው ይልቅ የምናደርገውን ነው፡፡ እዚህ ላይ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፡-
የሆነ ቀን በታክሲ ወደ ትምህርት ቤት እያደረስኩት ሳለ፣ ከታክሲ ረዳቱ ጋር ያልተገባ ነገር ተመላለስን፡፡ በወቅቱ ልጁ አናዶኝ ስለነበር ሁኔታውን አላስተዋልኩትም ነበር፡፡ ከታክሲው ወርደን በእግራችን በማዝገም ላይ ሳለን ሁኔታውን የታዘበው ልጄ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፡-
“ባቢ ልክ አይደለህም እኮ፣ ልጁን ይቅርታ መጠየቅ ነበረብህ!”
እውነቱን ለመናገር የተናገረው ያልጠበኩት ነገር ስለነበር አስደነገጠኝ፡፡
“ጥፋቱ የእኔ ብቻ ነበር እንዴ?” ስል ጠየኩት የምለው ጠፍቶኝ፡፡ በእዚያውም ነገሩን ምን ያህል እንደተረዳው ለማወቅ ፈልጌም ነበር፡፡ ምላሹ ከመጀመሪያው በባሰ ልቤን የነካ ነበር፡፡
“ጥፋቱ የእሱ ነው ግን አንተም ልክ አይደለህም!”
ይኼኔ ነው አንግዲህ ራስን ቆም ብሎ ማየት! ምንም የማስተባብለው ነገር አልነበረም፡-
“ልጁን ባላገኘውም አንተንም ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ!” አልኩት በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆኜ ብዙ ነገር እያሰብኩ፡፡
ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ፤ ለአከራዬ ልጅ የ11ኛ ክፍል ደብተሬን እንደማልሰጣት ነገርኳት፡-
“አሁንም ልታስቀምጠው ነው!” ስትል በመገረም ተመለከተችኝና፡-
“የእኔ እኮ ከአምና ደብተሮቼ አንዱም የለም! አለችና ሌሎቹን ወረቀቶች ይዛ እየሳቀች ሔደች፡፡
የእኔ እንኳ እሺ ተጋነነ እንበል፤ ግን ደግሞ የአምና ደብተርን አለማስቀመጥን ምን ይሉታል? ይህ እኮ አይጠቅምም ሊባል የሚችል ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ የእኔና የወንድሜ ልጅ በአንድ ዓመት ይበላለጣሉ፡፡ የዘንድሮ የእኔ ልጅ መጽሀፎች በቀጣዩ አመት ለወንድሜ ልጅ መማሪያነት ያገለግላሉ፡፡ ያ ባይሆን እንኳ፣ ለራሱም ቢሆን ባለፈው አመት የተማረውን መለስ ብሎ ለመከለስ ይጠቅመዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መጽሀፎቹን በአግባቡ መያዝ አለበት፡፡ ይህንን ነው አንግዲህ በዚያች አጋጣሚ በተግባር ያስተማርኩት፡፡
ወግም አይደል የያዝኩት፣ “ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ፤ እዚህ ላይ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡-
ሰሞኑን ቤት ስንቀይር አንድ ወረቀት አገኘሁ፡፡ ወረቀቱ ዝም ብሎ ወረቀት አልነበረም፡፡ በትዝታ ወደ ኋላ መልሶ፣ ብዙ ነገሮችን እንዳስታውስ ያደረገኝ ወረቀት ነበር።
ወረቀቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁ በአጭር ልበ ወለድ ውድድር የ3ኛ ደረጃን አግኝቼ የተሰጠኝ የምስክር ወረቀት ነበር። ትዝ ይለኛል ከምስክር ወረቀቱ ጋር የ50 ብር ሽልማት ተበርክቶልኝ ነበር፡፡ በነጭ ፖስታ ታሽጎ የተሰጠኝ 50 ብር እንዲህ ቀላል አቅም የነበረው እንዳይመስላችሁ! ከዩኒቨርሲቲ ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ መጀመሪያ የተቀጠርኩበት የዲግሪ ደመወዜ 1068 ብር ነበር እኮ ጎበዝ!
እና ያቺ 50 ብር አንድ ትልቅ ሆቴል ጓደኛዬን ራት ለመጋበዝ አቅም ነበራት፡፡ ካላመናችሁ ጎንደር በሚገኘውን “ላምበርጌር” ሆቴል፣ በወቅቱ የነበረውን አስተናጋጅ መጠየቅ ትችላላችሁ፡፡ ከዚያ ይልቅ ግን እኔን ብታምኑኝስ?
እናም ልቀጥል፤ እንዳልኳችሁ ከጓደኛዬ ጋር ራት በላን፡፡ ይህ ራት እስከ ዛሬ ከበላኋቸው ራቶች ሁሉ የተለየ ስሜት የሚሰጠኝ ነው፡፡ በፍቅር፣ በሳቅና ጨዋታ የደመቀ ምርጥ ራት!
በመጨረሻም ይህን እላችኋለሁ፡-
በዚያች በተሸለምኳት 50 ብር ራት የጋበዝኳት ሴት፣ የልጄ እናት (ባለቤቴ) ነች!

More Stories
ሆና ያሳየች
“ወታደርነቴ ያስተማረኝ በራስ መተማመንና ሥራ ወዳድነትን ነው” – ወታደር ከበደ ደቀማ
“በዓሉ የሀዋሳ ከተማን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ የገጽታ ግንባታን ፈጥሯል” – መላከ ኤዶም ቀሲስ ተዋበ ምትኩ