በአለምሸት ግርማ
ስራን ለመውደድ የውስጥ ፍላጎት፣ ጥንካሬ፣ አስተዳደግና የመኖሪያ አካባቢ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በትምህርትም ሆነ በስራ እችላለሁ ብሎ መሰናክሎች ቢገጥሙት እንኳን በቀላሉ ተስፋ አይቆርጥም። ጠንክሮ የተማረ ወይም የሰራ የድካሙን ያህል ያገኛል። ዓላማውን ለማሳካት መሰናክሎችን በትዕግስት ያለፈ ቢዘገይም ካሰበበት መድረሱ አይቀርም።
አንዳንድ ሰዎች መሆን የሚፈልጉትን ያልማሉ፤ እዚያ ለመድረስም የሚጠበቅባቸውን ዋጋ ይከፍላሉ። አንዳንዶች ደግሞ ፍላጎታቸውና ተግባራቸው ለየቅል ሲሆን ይስተዋላል። በምኞት ብቻ የሚገኝ ነገር የለምና ያሰቡበት ለመድረስ ትጋት የግድ ይላል።
በተለይም ከአካል ጉዳት ጋር ሆኖ ያሰቡበት መድረስ የራስን የውስጥ ጥንካሬና ትዕግስት እንደሚጠይቅ እሙን ነው። የዛሬዋ የችያለሁ አምድ ባለታሪካችን ተሞክሮም የሚያሳየን ይህንኑ ነው። አካል ጉዳት ቢገጥማትም ፈተናዎች በፅናት በማለፍ በአሁኑ ወቅት ደስተኛ ህይወት እየመራች ትገኛለች።
ወይዘሮ መዓዛ ጋሻው ትባላለች። ትውልድና ዕድገቷ በወላይታ ዞን ዳሞት ፉላሳ ወረዳ ነው። ለቤተሰቦቿ ሁለተኛ ልጅ ናት። ጉዳት አልባ ሆና ብትወለድም፤ ገና በህፃንነቷ ነው የአካል ጉዳት የገጠማት። የጉዳቷ ምክንያት ደግሞ የልጅነት ጨዋታ ነበር። በጨዋታ መሃል የተከሰተ ጥቂት የሚመስል እክል፤ ነገር ግን ውሎ ባደረ ቁጥር ለጉዳት መንስኤ የሆነ ክስተት።
እንደወትሮው ሁሉ ከእኩዮቿ ጋር የተለመደውን ጨዋታ እየተጫወቱ ባለበት ሳር ጠልፏት ትወድቃለች። በወቅቱ ብዙም ህመም እንዳልተሰማት ነው የምታስታውሰው። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ እግሯ ላይ ህመም መሰማት ጀመረ። ህመሙ እየጨመረ በተረከዝ መርገጥ እያቃታት መጣ። በዚህም ምክንያት ስትራመድ በሙሉ እግሯ ከመርገጥ ይልቅ በእግሮቿ ጣቶች ለመርገጥ ተገደደች።
መደበኛ ትምህርቷን እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ በተወለደችበት አካባቢና አቅራቢያ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተከታተለች ሲሆን፤ አስረኛ ክፍልን ካጠናቀቀች በኋላ ኑሮዋን ሃዋሳ አድርጋለች።
ወደ ሃዋሳ የመጣችበት ዋና ምክንያት ወደ መሰናዶ ትምህርት የሚያስገባ ውጤት አለማምጣቷ ነበር። በ1998 ዓ.ም ሃዋሳ ስትመጣ ያረፈችው ዘመዶቿ ጋር ነበር። በወቅቱ ዘመዶቿ ባደረጉላት ድጋፍ “አዲስ ልማት ራዕይ” የተሰኘ በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰራ ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የሲንጀር ስልጠና የመውሰድ ዕድሉን አገኘች።
ስልጠናዋን ተከታትላ ስትጨርስ ድርጅቱ እንዲሁ አልሸኛትም፤ ይልቁንም የስራ መሳሪያና መጠነኛ ድጋፍ አድርጎላት እንጂ። በመቀጠልም ወደ ስራ ለመግባት ቅድመ ሁኔታዎችን እያመቻቸች ባለችበት ወቅት የተሰጣት የሲንጀር ማሽን ይዘረፍባታል። በወቅቱ በገጠማት ነገር አዝና ነበር። ምክንያቱም በተከሰተው ክስተት ስራዋን መቀጠል ሳትችል ቀርታ ነበር።
ነገር ግን በገጠማት ነገር አዝና ብቻ አልተቀመጠችም። ሌሎች አማራጮችን ማየት ጀመረች። ከዚያም አነስተኛ ንግዶችን ጀመረች። ጥሬ አቮካዶ በመግዛት እና በማብሰል በሰው ሻይ ቤት በር ላይ ተቀምጣ ትሸጥ ነበር። በዚያም ለራሷ ገቢ መፍጠር ቻለች፤ ከምታገኘው ገቢም የሚያስፈልጋትን ወጪ ከመሸፈን አልፋ ቤተሰቦቿንም ትደግፍ ነበር። ያም በወቅቱ ደስተኛ እና ጠንካራ እንዳደረጋት አጫውታናለች።
በዚህ ሁኔታ እያለች የአካል ጉዳተኞች ማህበር በሰጣት የድጋፍ ደብዳቤ መሰረት ሃዋሳ የሚገኘው “ዛየን ቢዝነስና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ” የዲፕሎማ ነፃ የትምህርት እድል አገኘች። ጎን ለጎን ስራዋን እየሰራች ትምህርቷን ተከታትላ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በዲፕሎማ መርሃ ግብር በ2003 ዓ.ም መመረቅ ቻለች። ከተመረቀች በኋላ ማስታወቂያዎችን ስትከታተል ቼሻየር ኢትዮጵያ ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድራ በማለፍ ተቀጠረች።
በዚያም በእንግዳ ተቀባይነትና በፀሐፊነት ስራዋን በትጋት መስራት ጀመረች። በመቀጠልም ባገኘችው ስራ ብቻ ረክታ አልተቀመጠችም። በ2008 ዓ.ም በሃዋሳ ኢንፎሊንክ ኮሌጅ የዲግሪ መርሃ ግብር ትምህርቷን መከታተል ጀመረች።
መደበኛ ስራዋን ቼሻየር ኢትዮጵያ ሃዋሳ በሚገኘው ቢሮዋ ስታከናውን ቆይታ በትርፍ ጊዜዋ ደግሞ ትምህርቷን ትከታተል ነበር። ከነዚህ ነፃ የሆነውን ጊዜዋን ደግሞ ቀድሞ ትሰራ የነበረውን የንግድ ስራ በመስራት ጊዜዋን ያለአግባብ አታባክንም ነበር። ስራ መስራት ያስከብራል፤ ስለዚህ ማንኛውም ስራ መናቅ የለበትም የሚል ጠንካራ እምነት አላት።
በዚህ መሃል በ2006 ዓ.ም ለእግሯ የተሻለ ህክምና አደረገች። በምትሰራበት ቼሻየር ማዕከል የሚያስፈልጋትን ህክምና በነፃ ነበር የምታገኘው። የዚህኛውን ህክምና ግን አርሲ ነገሌ በሚገኙ ካቶሊኮች አማካኝነት ያደረገች ሲሆን፤ በተደረገላት የቀዶ ጥገና ህክምና ከፍተኛ ለውጥ እንዳገኘች ትናገራለች።
ባገኘችው ለውጥ ከዚህ ቀደም የማትጠቀማቸውን ዓይነት ጫማዎች እንደልቧ ማድረግ ቻለች፤ ለመርገጥም አትቸገርም፤ ስትራመድም በነፃነት የምትራመድ ሲሆን፤ በዚህም ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።
የገጠማትን አካል ጉዳት ተቋቁማ ጠንክራ በመስራቷ ከራሷ አልፋ ለታናናሾቿ አለኝታ መሆን ችላለች። ከምታገኘው ገቢ አካፍላ ጉድለታቸውን ለመሙላት ትተጋ ነበር። እነሱም አላሳፈሯትም፤ የከፍተኛ ተቋም ትምህርታቸውን አጠናቀው በመመረቅ በተለያየ ሙያ ወደ ስራ መሰማራት ችለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በ2012 ዓ.ም ወደ ትዳር ዓለም የገባች ሲሆን፤ የአንድ ወንድና የአንድ ሴት በድምሩ የሁለት ልጆች እናት መሆን ችላለች። በዚህም ደስተኛ መሆኗን ትናገራለች።
“እግዚአብሔር በብዙ ረድቶኛል። በትምህርቴ ምናልባትም ብዙዎች ትደርሳለች ብለው ያልገመቱበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ፤ በስራዬ ውጤታማ ነኝ፤ በትዳሬም መልካም የትዳር አጋር አለኝ። ስለዚህ አምላኬን ሁሌም አመሰግነዋለሁ፤ አሁን በህይወቴ የቀረብኝ ነገር ስለሌለ ደስተኛ ሆኜ እየኖርኩ ነው። በስራም ይሁን በግል የማገኛቸውን አካል ጉዳተኞች አበረታታለሁ፤ ጠንካራ እንዲሆኑም እመክራለሁ” ስትል ነበር ደስታዋን ያጋራችን።
“አካል ጉዳት ማለት ምንም ማለት አይደለም፤ ምናልባት ከተወሰነ እንቅስቃሴ ልንገደብ እንችላለን። ዋናው ነገር ሰዎች መስራት እንደሚችሉ ማመን ነው የሚያስፈልጋቸው። የሚችሉትን ነገር በመስራት ከጥገኝነት መላቀቅ መቻል አለባቸው። እኔ አካል ጉዳተኛ ነኝ አልችልም ብሎ ማሰብ አቅምን ስለሚያሳጣ ከእንደዚህ ዓይነት አመለካከት ራሳቸውን ማውጣት አለባቸው።
ራስን ከሌላው ዝቅ አድርጎ ማየት አስፈላጊ አይደለም። እችላለሁ ብለው ካመኑ የሚችሉትን ስራ በመስራት እንደሌላው ሰው ሁሉ መኖር፣ መማር፣ መቀጠር፣ መነገድ፣ ማግባት፣ መውለድ እንዲሁም ሀብት መፍጠር ይችላሉ። ለዚህ ሁሉ ግን ዋናው ነገር እችላለሁ ብሎ ማመን ነው” ስትል በትኩረት ትናገራለች።
“እኔም በቂ ግንዛቤ ሳይኖረኝ በፊት ከአካል ጉዳተኞች ጋር ያለኝ ግንኙነት ውስን ነበር። አሁን ግን ግንዛቤ ስላገኘሁ ከአካል ጉዳተኞች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነው ያለኝ። የምሰራውም በአካል ጉዳተኞች ላይ በሚሰራ ድርጅት ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ለጉዳዩ ያለኝ መረዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል።
በመሆኑም አካል ጉዳተኝነት የተለየ ነገር አለመሆኑን ተረድቶ፥ ካሉበት ሁኔታ በመውጣት ከሌላ አካል ጉዳተኞች ጋር መገናኘትና ልምድ መለዋወጥ ጠቃሚ መሆኑንም መናገር እፈልጋለሁ ትላለች።
“ከቤተሰባችን እኔ ብቻ ነኝ አካል ጉዳት የገጠመኝ። ነገር ግን እኔ ጠንካራ በመሆኔና እችላለሁ ብዬ በመስራቴ ጉዳት አልባ ለሆኑት ቤተሰቦቼ መትረፍ ችያለሁ። ስለሆነም ሌሎችም እንዲሁ እችላለሁ ብለው በማመን ካሉበት መውጣት፤ ብሎም ለሌሎች አርዓያ መሆን እንደሚችሉ ሙሉ እምነት አለኝ” በማለት ነበር መልዕክቷን ያስተላለፈችው።
እንደወይዘሮ መዓዛ በልበ ሙሉነት ህይወታቸውን የሚመሩ አካል ጉዳተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። ይህም የግንዛቤ ክፍተቱ እየጠበበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። ወይዘሮ መዓዛ ይቻላል የሚለውን እሳቤ በህይወቷ በተግባር ያሳየች ጠንካራ ሴት ናት። የአካል ጉዳት ከተወሰነ የእንቅስቃሴ ገደብ የዘለለ እንዳልሆነ ደጋግማ የምትናገር ሲሆን፤ ስራ ላለመስራት ምክንያት ሊሆን እንደማይገባም ትመክራለች።
በአንፃሩ ስለ አካል ጉዳት አሁንም ያልተቀረፉ የአመለካከት ክፍተቶች መኖራቸውን የሚያሳዩ ሁኔታዎች መኖራቸው አልቀረምና አካል ጉዳት የገጠማቸው አካላት፣ እንዲሁም አካል ጉዳተኛ ቤተሰብ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በማስተማርና ድጋፍ በማድረግ ድርሻቸው የጎላ ነውና ኃላፊነታቸውን በትዕግስት ቢወጡ መልካም ነው።

More Stories
“ወታደርነቴ ያስተማረኝ በራስ መተማመንና ሥራ ወዳድነትን ነው” – ወታደር ከበደ ደቀማ
“በዓሉ የሀዋሳ ከተማን በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ የገጽታ ግንባታን ፈጥሯል” – መላከ ኤዶም ቀሲስ ተዋበ ምትኩ
“ጠንክረን ከሰራን ሰዎችን መሳብ እንችላለን” – መምህር ቃልኪዳን መንክር