“ኩሙሩ”

“ኩሙሩ”

በደረሰ አስፋው

ከአርብቶ አደሩ መንደር የወጡ ናቸው። እሳቸው በተማሩበት ወቅት በመንደራቸው የተማሩ የሚባሉ ሴቶች ቁጥር 3 ብቻ እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡ እነዚህም ቢሆን እሳቸውን በማየት ተነሳስተው የተማሩ መሆናቸውን በመጥቀስ፡፡ ይህ የሆነው የምትማር ሴት ልጅ በአካባቢው ጠፍታ ሳይሆን በአካባቢው በሴቶች ላይ ባለው ባህላዊ ተጽእኖ እድሜዋ 10 እና ከዛ በላይ ከሆናት ለትዳር እንጂ ለሌላ ዓላማ ያልተፈቀደላት በመሆኑ ነበር፡፡

አካባቢያቸው አርብቶ አደርና ከፊል አርሶ አደር በመሆኑ የትምህርት ተደራሽነት አለመስፋፋቱም ችግሩን አግዝፎታል ማለት ይቻላል፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብ ለትምህርት ያለው ንቃተ ህሊናው አለማደግ በሴት ልጅ ላይ ያለውን አመለካከት የተለየ አድርጎታል፡፡

ሴት ልጅ ተምራ ለቁም ነገር ትደርሳለች የሚል አመለካከት የለም፡፡ ይህ ችግር የሚጀምረው ደግሞ ከሴቷ ቤተሰብ ነው፡፡ ሴት ልጅ ስትወለድ የሚታሰበው በጋብቻ ብዙ ከብቶች፣ መሳሪያና ፍየል የምታስገኝ የሀብት ማግኛ እና መክበሪያ ተደርጎ ነው የሚቆጠረው፡፡

እንደመታደል ሆኖ ግን በደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ አንዲት ሴት ከትዳር ይልቅ መማርን መረጠች፡፡ የ3 ቀን መንገድ እየተጓዘች በመማር ትምህርቷን ያጠናቀቀች እንስት እንደ አበባ ፍክት ብላ በአካባቢው ብቅ አለች፡፡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን እንዳጠናቀቀችም የኮሌጅ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ ሆነች፡፡

በዚሁ የኮሌጅ ትምህርቷ ላይ እያለችም በአካባቢው የሴት አመራሮች ሲፈለግ ብቸኛ የተማረች ሴት ሆና ተገኘች፡፡ መመረቂያ ጊዜዋ ወር ሲቀረውም ለአካባቢው ሴቶች ብርሃን ሆና ልትታይ በፖለቲካ አመራርነት ታጨች፤ የወረዳው ሴቶችና ህጻናት ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን፡፡

ዛሬ ተሞክሯቸውን ልናስቃኛችሁ የወደድነውን ባለታሪክ ያገኘናቸው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ሲሳተፉ ነው፡፡ እኛም መገናኘታችንን እንደመልካም አጋጣሚው በመጠቀም ሴቶችን በማንቃት ዘወትር ሰለቸኝ የማይሉትን የእኚህን እንስት ተሞክሮ ለማስቃኘት አጭር ቆይታ አድርገን ያገኘነውን የእቱ መለኛዋን ታሪክ እነሆ ለአንባቢያን ለማጋራት ወደድን፡፡

ወ/ሮ አበባ ስፍታዬ ይባላሉ፡፡ በደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ ዴሜ ገሮ ቀበሌ ነው የተወለዱት፡፡ የደቡብ ኦሞ ዞን ሰላማጎ ወረዳ ዋና አፈ ጉባኤ ናቸው፡፡ የክልል እና የፌደሬሽን ምክር ቤት አባል እና ተወካይ ናቸው፡፡ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም አካባቢያቸው በሚገኝ ብቸኛ ትምህርት ቤት ገብተው ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡

ቀጣዮቹን ክፍሎች ለመማር አካባቢያቸውን ለቀው መሄድ የግድ ስለነበር በዚሁ ዞን ቀይ አፈር ወደሚባል አካባቢ ተዘዋውረው ለመማር ግድ አላቸው፡፡ በዚህም ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡ ከዚህም በመቀጠል ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ጂንካ ከተማ አዳሬ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡

ከዚህም በኋላ በአካባቢያቸው በጤና ኤክስቴንሽን ሙያ ህዝባቸውን ለማገልገል ተመልምለው ወደ ወላይታ ሶዶ ነው ያቀኑት፡፡ ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁም በገጠሩ አካባቢ በመንቀሳቀስ ለ6 ዓመታት ህዝባቸውን በሙያቸው አገልግለዋል፡፡ በጤና ኤክስቴንሽን በሰርተፊኬት የጀመረው ትምህርታቸውም አድጎ ዛሬ ላይ በህዝብ አስተዳደር (ማነጅመንት) የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡

ተወልደው ያደጉበት አካባቢ ያለው የትምህርት ተደራሽነት ዝቅተኛ ነበር። በትምህርት ላይ ያለው የማህበረሰቡ ግንዛቤም ዝቅተኛ ነው፡፡ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶም ለመማር መንገድም ሆነ የትራንስፖርት ጉዳይ የማይታሰብ ነበር፡፡ ያሰቡት ደረጃ ለመድረስ በሴትነት የማይታሰቡ ፈተናዎችን ተጋፍጠዋል፡፡

ወ/ሮ አበባ ከትውልድ ቀያቸው ተነስተው በቀይ አፈርና በጂንካ ሲማሩ ከፍተኛ የተባለውን ዋጋ ከፍለው መማራቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ከአካባቢያቸው ተነስተው ወደ ጂንካ ሲሄዱ 140 ኪሎ ሜትር ለ3 ቀናት የሚወስደውን የእግር መንገድ በመጓዝ ነበር መማር የቻሉት፡፡ አካባቢው በጫካ የተሸፈነና ነዋሪውም ቢሆን አርብቶ አደር በመሆኑ ለማረፊያ እንኳ የሚሆን ቋሚ ነገር ለማግኘት አስቸጋሪ ነበር፡፡ የተጫሙት ሸበጥ ጫማ ተበጣጥሶ እግራቸውም ቆስሎ ነበር የሚደርሱት፡፡

በ1998/99 ዓ.ም አካባቢ ግን አካባቢው ላይ ብዙ መሰረተ ልማቶች መስፋፋቱ ለህዝቡ በጎ ነገርንም ይዞ ነበር የመጣው፡፡ በአካባቢያቸው በሰላማጎ ወረዳ የተከፈተው የኩራዝ ስኳር ፋብሪካ መከፈቱ ለአካባቢው ብስራት ነው የሆነው፡፡ ለመንግስት ምስጋና ይድረሰውና በአካባቢያቸው በየደረጃው የሚገኙ በርካታ የመጀመሪያ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል። የቀድሞውንና የአሁኑን ሲያነጻጽሩትም ልዩ ስሜት እንደሚሰማቸው ነው የገለጹት፡፡ ትምህርት ቤት በየቀበሌው ተከፍቷል፡፡ ለአካባቢው ህጻናትም የመማር ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ለውጥ ደግሞ የቀድሞውን መከራ ወደኋላ በማሰብ የሚሰማቸው ደስታ ወደር የለውም፡፡

ወ/ሮ አበባ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ሴት ልጆች ለመማር ፈታኝ ባህላዊ ተጽእኖ እንደነበረባቸው ያወሳሉ፡፡ የወ/ሮ አበባ ወላጅ አባት እና ቤተሰባቸው እሳቸውን ወደ ትምህርት ቤት መስደዳቸው በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ውግዘት ደርሶባቸው ነበር፡፡ ሴት ልጅ ለትዳር እንጂ ለትምህርት አልተፈቀደም በሚል፡፡ ይሁን እንጂ ወላጅ አባታቸው ተጽእኖውን በመቋቋም ልጃቸውን አስተምረው ለቁም ነገር አደረሱ፡፡ ዛሬ ላይ ወ/ሮ አበባ ለብዙዎች ምሳሌ በመሆን ሌሎች ሴቶችም እንዲማሩ አርአያ ሆነዋል፡፡

በወቅቱ ወ/ሮ አበባ ከትውልድ አካባቢያቸው ተነስተው በቀይ አፈርና በጂንካ ከተማ አዳሬ ትምህርት ቤት ሲማሩ 3 ሴት ልጆች ብቻ ይማሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ግን እነሱን በምሳሌነት በማየት በርካታ ሴት ልጆች መማር ችለዋል፡፡ 20 የሚሆኑ ሴት ልጆች ወደ አዳሪ ትምህርት ቤት በመግባት እንደተቀላቀሏቸው ነው የተናገሩት፡፡ ዛሬ ላይ ከዚህ ባሻግር ከዲግሪ አልፎ 2ኛ ዲግሪያቸውን የያዙ በርካታ ሴት ልጆች ከዚሁ ማህበረሰብ መፍለቃቸውን ነው የተናገሩት፡፡

“ዛሬ የኔ መማር ለወላጅ አባቴና ቤተሰቤ ኩራት ሆኗል፡፡ በአካባቢው ሴትን ልጅ በማስተማር ፈር ቀዳጅ በሚል ወላጅ አባቴ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡ እንዳንተ ቢሆን ኖሮ ልጆቻችን የት ይደርሱ ነበር፤ ለሌሎቻችን ምሳሌ በመሆንህ ኮርተንብሃል በማለት የአካባቢው ማህበረሰብ አድናቆትን ቸረዋቸዋል” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ወ/ሮ አበባ ወደ አመራርነቱ ሲገቡ በወቅቱ በአካባቢያቸው የተማሩ ሴቶች አልነበሩም፡፡ መማርን ተጠይፈውት ሳይሆን በሴቶች ላይ ከሚደርሰው ባህላዊና ማህበራዊ ተጽእኖ የተነሳ እንጂ፡፡ ወ/ሮ አበባ ገና ወላይታ ሶዶ ኮሌጅ ውስጥ እያሉ ከመመረቂያ ጊዜያቸው አንድ ወር ቀደም ብሎ ነበር ለአመራርነት የታጩት፡፡ ለ6 ዓመታት በጤና ኤክስቴንሽን ሙያ ዘርፍ ካገለገሉ በኋላ ህዝብ ወደ መረጣቸው የፖለቲካ አመራርነት ገብተው ማገልገል ችለዋል፡፡

በዚሁ የሹመታቸው ጅማሬም በ1998 ዓ.ም የወረዳው ሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆንም ማገልገል ጀመሩ፡፡ በ1999 ዓ.ም በጦላይ የአመራር ስልጠና ከወሰዱ በኋላም በወረዳው ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ በመሆን ለ4 ዓመታት አገልግለዋል፡፡

ወ/ሮ አበባ የአካባቢውን ባህላዊ ተጽእኖ ተቋቁመው በመማራቸው ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ሴቶችና ለአካባቢው ማህበረሰብ በጎ ተጽእኖ ማሳረፋቸውን ነው የተናገሩት። በወረዳው ሴቶች ጉዳይ ጽ/ቤት በኃላፊነት ባገለገሉበት ጊዜ በአርብቶ አደሩ መንደር የነበረውን የአመለካከትና የግንዛቤ ችግር ለመቅረፍ እንደ እድል እንደተጠቀሙበት ነው የተናገሩት፡፡

ስለሴቶች ነጻነት፣ መብትና ሴቶች ነጻ የህግ አገልግሎት አግኝተው መብታቸውን እንዲያስከብሩ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ጡሩንባ እየነፉ ይቀሰቅሱ፣ ያስተምሩ እንደነበር ነው የገለጹልን፡፡

በዚህም “ኩሙሩ” በአማርኛው “የሴቶች ባላባት” የሚል ትርጓሜ እንደተሰጣቸው ነው የተናገሩት፡፡ ዛሬ በዚህ ስራቸው በርካታ ለውጦች መታየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ሴቶች መብታቸውን ተጠቅመው ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እያደገ እንደሚገኝ በመግለጽ፡፡

የ3 ልጆች እናት እንደሆኑ የገለጹልን ወ/ሮ አበባ ባለቤታቸው የመንግስት ሰራተኛ ሲሆኑ፤ ቤተሰባቸውን በመደጋገፍ ይመራሉ፡፡ አብዛኛውን የአገልግሎት ጊዜያቸውን በምክር ቤት ማሳለፋቸውን ገልጸው በቋሚ ኮሚቴነት ኃላፊና አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡

“በመማሬ ያመጣሁት ለውጥ ለክልልም ሆነ ለፌደሬሽን ምክር ቤት አባልነት አብቅቶኛል፤ በዚህም የህዝቡ አንደበት በመሆን አካባቢው በሁለንተናዊ ዘርፍ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን የበኩሌን ድርሻ ተወጥቻለሁ፡፡” ብለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት ወ/ሮ አበባ እስካሁን በመጡባቸው የጊዜ ኡደቶች በአካባቢያቸው በርካታ ለውጦች መታየታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም አርብቶ አደሩ አካባቢ መምጣት ያለበትን ለውጥ እየተመለከቱ አለመሆኑን ስለመታዘባቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ለዚህም አርብቶ አደሩን ማስተማር እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ የተማሩ አርብቶና ከፊል አርሶ አደሮችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን በማሳደግ መስራትን ይጠይቃል፡፡ መንግስትና አጋር አካላት ተቀናጅተው በመስራት በአርብቶአደሩ አካባቢ ያለውን ችግር መቅረፍ ይገባል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

በሴቶች ላይ ያለው ባህላዊ ተጽእኖ በአካባቢያቸው ይጉላ እንጂ በሌሎችም አካባቢዎች ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል እንደማይባል ነው የገለጹት፡፡ ስለዚህ አሁንም ይህን ባህላዊና ማህበራዊ ተጽእኖ ለመቅረፍ ከምንም በላይ ሴቶች ግንባር ቀደም ተዋናይ ሊሆኑ ይገባል ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

“በአካባቢው አንድ ሴት ልጅ ተወለደች ሲባል አባትና እናት ይሄን ያህል ከብት፣ መሳሪያና ፍየል መጥቶልኛል ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ሴት ልጅ በትዳሯ እንኳ ባይመቻት ከዛ ቤት መውጣት አትችልም። ባለቤቷ እኔ አንቺን በዚህን ያህል ከብት፣ መሳሪያና ፍየል ገዝቼ ነው ያመጣሁሽ፡፡ ከእንግዲህ አንቺ የኔ እንጂ የቤተሰብ ወይም የሌላ አካል አይደለሽም ትባላለች፡፡ ስትሞቺም እንኳ እዚሁ ነው የምትሞቺው ትባላለች” ሲሉ ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ፡፡

“ባል ገና በለጋ ዕድሜዋ ለአባት መሳሪያና ከብት በመስጠት የራሱ ያደረጋትን ሚስቱን እንደፈለገ ቢያደርጋት ለእሷ ከለላና ዋስትና የሚሰጣት አካል አይኖርም፡፡ የህግ አካል ወይም የፖሊስ አባል እንኳ ቢያይ ይሄን የማውገዝ መብት የለውም፡፡ ሁሉም ለባህሉ ተገዥ ስለሚሆን፡፡ የህግ አካል ይሄን ድርጊት እቃወማለሁ ካለም የሚደርስበት ጉዳት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ሊያደርስ ይችላል” ሲሉ ነው የባህሉን ተጽእኖ አስከፊነት የገለጹት፡፡

ወ/ሮ አበባ በቤታቸው ውስጥ ጥሩ ሚስት የሚባሉ፣ ትዳራቸውን አክባሪና በፍቅር የሚመሩ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ለሌሎች ምሳሌ የሆነ ህይወትን በመምራትም እንዲሁ፡፡ ሰርተው ባፈሩት ሀብትም ጥሩ የመኖሪያ ቤት አላቸው፡፡ የትዳር አጋራቸው ከአካባቢው ተወላጅ አለፍ ብሎ የኮንሶ ተወላጅ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡

በዚህ ተግባራቸውም እንዴት እኛ አሳድገንና አስተምረን ከሌላ አካባቢ ለመጣ ሰው ትሰጣለች ቢባሉም እሳቸው ግን ለዚህ ተቃውሞ ቦታ ሳይሰጡ የትዳር ህይወታቸውን አጣጥመው እየኖሩ እንደሆነ ነው የገለጹልን። በዚህም ምሳሌ ሆነው መታየት ነው ፍላጎታቸው፡፡

እኛም ተነግሮ ያላለቀውን የደቡብ ኢትዮጵያ ከልል የምክር ቤት አባልና የሰላማጎ ወረዳ ህዝብ ተወካይ ከሆኑት ከወይዘሮ አበባ ስፍታዬ ጋር የነበረንን ቆይታ ያላጠናቀቅን በመሆኑ በሌላው እትም ተመልሰን እንደምናስነብባችሁ ቃል እየገባን የዛሬውን በዚሁ ቋጨን፡፡