በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በቆይታቸው ተደስተው እንዲመለሱ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በቂ ዝግጅት መደረጉ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሕዳር 23/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) 19ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን ለማክበር የሚመጡ እንግዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በቆይታቸው ተደስተው እንዲመለሱ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በቂ ዝግጅት መደረጉን የጋሞ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
ከተማዋን በሚመጥን መልኩ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የታክሲና ባለ 3 እግር ባጃጅ ማህበራት አረጋግጠዋል።
አቶ ነዋይ ጌታቸው እና ዘሪሁን ዘገዬ የዛሩማና የዜብራ ባለ 3 እግር ባጃጅ ባለንብረቶች ማህበራት ቦርድ ሰብሳቢዎች ሲሆኑ የሚመጡ እንግዶች ከተማዋን በሚመጥን መልኩ እንዲስተናገዱ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።
የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት፣ የታሪፍ ጭማሪ እንዳይኖር እና መጉላላትን ለማስቀረት ተጨማሪ መስመሮችን የመክፈት ስራ መሰራቱንም አብራርተዋል።
የአርባምንጭ ከተማ ትራፊክ ፓሊስ አስተባባሪ ረዳት ኢንስፔክተር ሀብታሙ አዱኛ በበኩላቸው፤ እንግዶች በከተማው 24 ሰዓት በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ የትራፊክ ፖሊሶች ከመቸውም ጊዜ በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።
የአርባምንጭ ከተማ በአገር አቀፍ ደረጃ በሰላም ወዳድነቷና እንግዳ ተቀባይነቷ የምትታወቅ ናት ያሉት የጋሞ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ ምክትል ኃላፊና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አክሊሉ ኢያሱ፤ እንግዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ በቆይታቸው ተደስተው እንዲመለሱ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
የታክሲና ባጃጅ ማህበራትን ቀድመን አወያይተናል ያሉት ኃላፊው አገልግሎቱን ቀልጣፋና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲሰጥ ሙሉ ዝግጅት መደረጉንም በማከል።
የአርባምንጭ ከተማ በታሪክ አጋጣሚ ይህንን በዓል አዘጋጅ በመሆኗ መደሰታቸውን የተናገሩት ኃላፊው እንግዶች በሚኖራቸው ቆይታ ተደስተው እንዲመለሱ ይደረጋል ሲሉ አብራርተዋል።
የዞኑን የሠላም ተምሳሌትነት እና የእንግዳ አቀባበል ባህልን በማጉላት እንግዶች በቆይታቸው እንዲደሰቱ ሁሉም አካል ቅንጅት መፍጠሩን አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
ከ148ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ
የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን እንደሚያረጋግጥ ተገለፀ
የተመሰከረለት ምርጫ