ከ148ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ

ከ148ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሕዳር 20/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) ከ148ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ እንደሚለማ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታውቋል።

ኤጀንሲው በ2017 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ውሃ አቅርቦትና የመስኖ ተቋማት ኢንቬንተሪ ዙሪያ የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመስኖ ተቋማት ልማት እና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ካሳዬ ተክሌ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ 112 የሚደርሱ ዘመናዊ የመስኖ አውታሮች መኖራቸውን ጠቅሰው የእነዚህ የመስኖ አውታሮች እንደየተቋማቱ አፈጻጸማቸው በየአመቱ ሲታይ ወጣ ገባ የማለት ባህርይ አላቸው።

ልዩነቶችን በማጥበብ በክልሉ በበጋ መስኖ ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ በመጥቀስ ከዚህ ውስጥም እስከ 10 ሺህ ሄክታሩ በዘመናዊ መስኖ የሚለማ ነው ብለዋል።

ትልቁ ነገር ችግሮችን መለየት ነው ያሉት ኢንጂነር ካሳዬ ችግሮቹ የሚቀርፉባቸው ስትራቴጂዎችን መንደፍ አንዱ መንገድ እንደሆነም ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪም በተለያየ ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ ተቋማትን በድጋሚ የጥናትና ዲዛይን ስራ በማካሄድ ወደ ተግባር የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው ብለዋል።

በቀጣይ የመስኖ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት ድህነትን ለመቀነስ በቅንጅት መስራት የሚያስፈልግ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት የተገነቡ የመስኖ መዋቅሮችን በኃላፊነት መጠበቅና መንከባከብ አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ ተቋማት የውሃ ሀብትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም በጋራ የመልማት ዓላማን ይዘው ለጋራ እድገት መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

የበጋ መስኖ ዝግጅት ያለበት ደረጃ እና በዘርፉ ያጋጠሙ ችግሮች በየመዋቅሮቹ ሀላፊዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎችም ያሉንን የመሬት፣ የውሃ እና የሰው ሀይልን በአግባቡ ከመጠቀም ባለፈ የአርሶ አደሮችን የማልማት አቅምን በማሳደግ እና የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ስርዓትን በማዘመን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የጋራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የመስኖ ልማቱን በጊዜ ሰሌዳ መጠቀም ያስፈልጋል ያሉት ተሳታፊዎቹ በተለይም የሶላር ፓምፖችን በአግባቡ በመጠቀም እና ተደጋግፎ በመሥራት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለብን ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ በክልሉ ስር የሚገኙ የግብርና መምሪያ፣ የውሃ መስኖና ማዕድን ልማት መምሪያ እንዲሁም የልዩ ወረዳ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ፡ ብርሃኑ ማሞ – ከወልቂጤ ጣቢያችን