የትራምፕ “ትራይፌክታ” ጣምራ ሥልጣን

የትራምፕ “ትራይፌክታ” ጣምራ ሥልጣን

በፈረኦን ደበበ

ጊዜ ቢለወጥም “ታሪክ ራሱን መድገሙ አይቀርም” የሚባለው ብሂል በተጨባጭ የተረጋገጠበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በምርጫ ተሸንፈዋል በሚል ዶናልድ ትራምፕ ከዛሬ አራት ዓመታት በፊት ከነጩ ቤተ-መንግሥት ሲወጡ ማንም ዳግመኛ ወደ ሥልጣን ይመለሳሉ ብሎ አልጠበቀም ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በጊዜው ግልጹን ተናገሩ፦ “ከዚህ በተሻለና ባማረ ሁኔታ ተመልሼ መጥቼ አገኛችኋለሁ” በማለት ተናግረው ነበር ደጋፊዎቻቸውን በመጨረሻ ሲሰናበቱ፡፡ በሂደት ውዝግቡ ተፋፋመ፡፡ እንደ እሳትም ለበለባቸው። ከአሥር በላይ የሆኑ ክሶች ተቆለሉባቸው፡፡ ወደ ወህኒ የሚወርዱበት ጊዜም ተቆረጠ፡፡

እሳቸው ግን የዋዛ አልነበሩም፡፡ ለአፍታም የሀገራቸውን ፍቅር ከልባቸው አላወጡም፡፡ ይወጣሉ፣ ይወርዳሉ፡፡ ከውጭ ሀገራት መሪዎች ጀምሮ ከባይደን አስተዳደርና ከራሳቸው ፓርቲ አባላትም ጭምር ጋር ፍልሚያውን ቀጠሉ፡፡

እንደ ሀገራችን ብሂል “ደፋርና ጭስ” መውጫ አያጣም እንደሚባለው የልባቸው መልካምነት ከድፍረት ጋር ተዳምሮ ክብርን አጎናጸፋቸው፡፡ “ትራይፌክታ” የሥራ አስፈጻሚ፣ ህግ አውጪና የዳኝነት አካላትን በፓርቲያቸው ሥር ማስገባት ቻሉ፡፡

በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉ በአንድ ዓይን ይመለከቱዋቸዋል ባይባልም የሚነሳባቸው ወቀሳና ጥላቻ ቀንሶ የትልቅ ሀገር መሪ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ያገኙት ድልም ሰው እምነት ካለውና ጠንክሮ ከሠራ ከማሸነፍ እንደማይመለስ የሚያመለክት ሆኗል፡፡

የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከተካሄደበት ሰሞን አንስቶ የዓለም ህዝብና የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት የሆኑት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከተጠበቀው ጊዜ ቀደም ብለው የመንግሥት ምሥረታ ተግባራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ይህም ለህዝብ የገቡትን ቃል በአግባቡ ለመፈጸም ይረዳቸዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ብዙ አድናቆትና ትችቶችንም ባስተናገደ መልክ የሚያካሂዱት የካቢኔ አመራሮች መረጣ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማታለል የወጠኑት ሆኖም ይታያል፤ ምክንያቱም ኮሮና ቫይረስ በሌለበት ባሁኑ ዘመን የክትባቱን አስፈላጊነት የሚጠራጠሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመሾማቸው፡፡

ኤሎን መስክና ሌሎች በአየር በረራ ዕውቀት የመጠቁ ግለሰቦችን የመንግሥት ቅልጥፍና ኮሚሽነር ማድረጋቸው በህዝቡ ላይ ጫና ሲያደርስ የነበረውን የተንዛዛ አሠራር ለመበጣጠስ ጠቃሚ ሲሆን እንደ ትምህርት ያሉ ሚኒስትሮችን ለማፈራረስ መፈለጋቸው ራሱ ወጪ ቆጣቢ ሥርዓትን ለመተግበርና በቦታው ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚረዳቸው ይሆናል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አመራረጣቸውም እንዲሁ የባይደን አስተዳደር በዓለም ላይ የደቀነውን የጦርነት ሥጋት ለማስቀረት አስተዋጽኦ ያለው ሆኖ ሲታይ በአንጻሩ ያነገቡትን “የአሜሪካ ትቅደም” ፖሊሲያቸውን ለመተግበርም ያመቻል፤ ምንም እንኳን የጸረ-ቻይና አመለካከት ባላቸው ግለሰቦች ላይ ትኩረት ማድረጉ የአሜሪካንን ጥቅም ጭምር ይጎዳል የሚል ሥጋት ቢፈጥርም፡፡

ዓለም ሠላማዊ ከሆነና ህይወት በመደበኛ ሁኔታ የምትቀጥል ከሆነ ብዙ ውጣ ውረድ አይኖርም የሚል አስተሳሰብ ያላቸው ፕሬዝዳንቱ፣ ልዩነት እየፈጠሩ በመገስገስ ላይ ሲሆኑ አሁን ያሉባቸው ሀገራዊ ጉዳዮችን ካገባደዱ ቀጣይ ወሳኝ ወደሆኑ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንደሚሸጋገሩ ይጠበቃል፡፡

ትራምፕ ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ ለህዝብ የገቡትን ቃል በማጠፍ በተለይ ባይደን ሲያካሂዱ የነበሩ ጦርነቶችን ያስቀጥሉ አያስቀጥሉ ለሚለው ጥያቄም ቢሆን የኋላ ታሪካቸውን ብቻ በመመልከት መመለስ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅትን ጨምሮ ከተለያዩ አውሮፓ መሪዎች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ስለገቡ፡፡

በባይደን አስተዳደር የደረሰባቸው ግፍና ጭቆና ከተመለከትንም የፖሊሲያቸው ጠንቅ እንጂ በምንም ሁኔታ የእሳቸውን ዱካ እንደማያስቀጥሉ ይታሰባል፡፡ ያን ጊዜ የአሜሪካ ጦር ከአፍጋኒስታን በፍጥነት እንዲወጣ ያስቀመጡት አቅጣጫም የቁርጠኝነታቸው ሌላ ማሳያ ነው፡፡

ይህንን አቋማቸውን የሚደግፍ ሌላ ማሳያ በአሁኑ ጊዜ ውሳኔ ሰጪው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ወጪዎችን ለመቆጣጠር የተሾሙት እንደ ኤሎን መስክ የመሳሰሉ ባለሀብቶች ሁሉ ተሳታፊ መሆናቸውም ጥንካሬውን ያረጋግጣል፤ ምንም እንኳን በእሥራኤል ላይ ያላቸው የተለሳለሰ አቋም አጠራጣሪ ቢሆንም፡፡

ሰሞኑን ስለ ሩሲያና ዩክሬን የወጡ ዘገባዎችም እንደዚሁ ሥጋት ሳይሆን ተስፋ ማዘላቸው የተመራጩን ፕሬዝዳንት ዝና ከፍ ያደርጋል ለዓመታት ሳይነጋገሩ የቆዩ የአውሮፓ መሪዎች ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መነጋገር በመጀመራቸው፡፡

የባይደንን ፖሊሲ በመደገፍ የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት እንዲቀጥል ግፊት ያደርጉ የነበሩ መሪዎች ተስፋ መቁረጣቸው ትራምፕ ለዓለም ያበረከቱት ትልቅ ሥጦታ ሆኖም ይታያል፤ ቀጣይ በሀገር ቤት የጀመሩትን ሥራ ወደ ዓለም በማሳደግ ባይደን ከነጩ ቤተ-መንግሥት ከመውጣታቸው በፊት ዩክሬንን ለመጎበኘት ቃል የገቡ እንደመሆኑ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የጦርነቱ ቀንደኛ መሪ የነበሩት የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በስልክ ሲነጋገሩ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸውና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለኒስኪ ራሳቸው “ቀጣይ ዓመት ሠላም ለማውረድ ሁሉን እናደርጋለን” ማለታቸው የተሻለና መልካም ብሥራት ሆኖ ይታያል ምንም እንኳን ውኃ በማይቋጥር ምክንያት ጦርነቱ የመባባስ አዝማሚያ ቢያሳይም፡፡

ጽንስ ማስወረድ ከመቃወማቸው አንጻር እንደ ጠንካራ ክርስቲያንና በአንዳንዶች ዘንድ እንደ “አዳኝ” የሚታዩት ትራምፕ ከዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት የሚሠነዘርባቸውን ወቀሳ ግን ማስቆም አልቻሉም፡፡ የእያንዳንዱ ተመራጭ ካቢኔ የግል ባህሪ እያነሱ የሚያብጠለጥሉት ተቃዋሚዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመዘርጋት ያሰቧቸው ራዕይዎቻቸውን ሁሉ ለማደናቀፍ ይሞክራሉ፡፡

ሌላው ትችት ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ህዝቦች ይሰጣሉ የሚባለው ዝቅተኛ ግምት ሲሆን ይህ በተለይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የእሱ ተጠሪ ተቋማትን ይመለከታል፤ በቂ የገንዘብ ድጋፍ አይሰጡም በሚለው ሥጋት፡፡

እሳቸው ሥልጣን ይዘው ሥራ ባልጀመሩበት በአሁኑ ጊዜ ለአፍሪካ ትኩረት አይሰጡም የሚለውም ከሥጋት የዘለለ ተጨባጭ መሆን የማይችል ሀሳብ ሆኖ ይታያል፤ ምክንያቱም ቀጣዩን ካለፈው በተሻለ ሁኔታ ይሠራሉ ተብሎ ስለሚታሰብ፡፡

በዚህም ሆነ በዚያ በተለያዩ ጊዜያት ለግድያ የተፈለጉና፣ ወህኒ ቤት ይገባሉ ተብሎም የተጠበቁት ሰው የሀገር መሪ ሆነው መውጣት እጅግ ይደንቃል። ከዚህ ባለፈ ሦስቱ የመንግሥት አካላት መቆጣጠር የሚያስችላቸው ድጋፍ ማግኘታቸውም በሀገሪቱ ላይ ረጅም አሻራ ለማስቀመጥ ይረዳቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በፓርቲያቸው ያለው አንድነትና ጥንካሬ እንደሚጨምር ተንታኞች እየገለጹ ናቸው፡፡