“ሰርተን መለወጥ ስንሻ የሚያጋጥመን ማነቆ ብዙ ነው” – ወጣት ባትሪ በቀለ
በደረሰ አስፋው
ለበርካታ ዓመታት ደንበኛቸው እንደሆነ ገለጹልኝ፡፡ አርባ ምንጭ ከተማ እስካሉ ድረስ ጫማቸውን ለሌላ አስነክተው እንደማያውቁ በመጠቆም፡፡ በቆየው የደንበኝነት ጊዜያቸው ጥሩ ወዳጅነት ፈጥረዋል፡፡ በዚሁ ስራ ትዳር መስርቶ፣ ልጆችንም አፍርቶ የሚያስተዳድር በመሆኑ ልዩ አድናቆት እንዳላቸው ነው የገለጹልኝ።
“ሙሉ አካል እያላቸው በአልባሌ ቦታ ጊዜያቸውን ለሚያባክኑም ጥሩ ምሳሌ ሊሆን የሚችል አካል ጉዳተኛ ነው” ሲሉም ደንበኛው ይገልጹታል፡፡ በተለያዩ ሱሶች ተጠቅተው ለዝርፊያ አልያም ለልመና የተዳረጉ ወጣቶችን ሲመለከቱ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው በጫማ ማስዋብ ስራ ላይ የተሰማራው ወጣት አካል ጉዳተኛው እንደሆነም ያነሳሉ፡፡
ወጣቱ አካል ጉዳተኛ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀለት የመስሪያ ቦታ ከማለዳው ነው ያገኘነው፡፡ ደንበኞቹ ባዘጋጀው አግዳሚ ወንበር ተቀምጠው ተራቸውን ይጠብቃሉ፡፡
ተጫዋች ከመሆኑ የተነሳ በአስቂኝ ቀልዶቹ ዘና እያደረገ ደንበኞቹን እንደሚያቆያቸው መታዘብ ችያለሁ፡፡ እኔም በዚህ ብቻ አልቆምኩም፡፡ ወደዚሁ አካል ጉዳተኛ ጠጋ በማለት ሀሳቡን እንዲያጋራኝ ጠየቅኩት፡፡ እሱም ፈቃደኛ ሆነልኝ፡፡
ወጣት ባትሪ በቀለ ይባላል፡፡ የተወለደው ወላይታ ዞን ዳሞት ሶሬ ወረዳ ነው፡፡ አሁን ላይ መኖሪያው በአርባ ምንጭ ከተማ ሲሆን የኑሮ መተዳደሪያውም የጫማ ማስዋብ ስራ ነው፡፡ በተወለደበት ዳሞት ሶሬ አካባቢ እስከ 7ኛ ክፍል ተምሯል፡፡ ወላጅ አባቱ በ1981 ዓ.ም ሲሞቱ እሱም ደጋፊ በማጣቱ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ፡፡
በአባቱ ሞት ምክንያት ሀዘኑ የጎዳው ባትሪ አካባቢውን ለቆ ለመሰደድ ተነሳሳ፡፡ ድንገት አንድ መረጃ ወደ ጆሮው ሹክ የሚለው ሰው አጋጠመው፡፡ የአርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ለአካል ጉዳተኞች የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርግ፡፡ የአባቱን ሞት ማስረሻ ይሆነኛል በማለት ስደትን ሲያስብ የነበረው ወጣት ባትሪ ይህን መረጃ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ነበር የተመለከተው፡፡
ዝግጅቱን አድርጎ በቆረጠው ቀን ሁለት አማራጮችን ይዞ ከትውልድ አካባቢው ተነሳ፡፡ የአርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ድጋፍ ካልተሳካም በዚያው ስራ አፈላልጋለሁ የሚሉ አማራጮችን ይዞ ነበር ወደ አርባ ምንጭ ያቀናው። ዕድልም ሀሳቡን አልነፈገችውም፡፡
አንዱ ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ተሳኩና ከማዕከሉ ክራንች ድጋፍ አገኘ፡፡ ተንቀሳቅሶ ከተማዋን የመቃኘት ዕድል ፈጠረለት፡፡ በተመሳሳይ የጫማ ማስዋብ ስራ ለመጀመር የሚያስችለውንም አጋጣሚ አገኘና ወደ ትውልድ ቀዬው ሳይመለስ አርባ ምንጭ ከተማን ቤቱ አድርጎ እስከ ዛሬም እንደሚኖር ገለጸልኝ፡፡
የቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ የሆነው ወጣት ባትሪ በአርባ ምንጭ ከተማ መኖር ከጀመረ ከ16 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ እሱን ተከትለው የመጡ 3 ወንድሞቹን ይዞ መኖር ቢጀምርም ከዓመታት ቆይታ በኋላ ከእነሱ ተለይቶ የራሱን ትዳር መስርቶ እየኖረ ይገኛል፡፡
ለ16 ዓመታት በቆየው ጫማ ማሳመር (ሊስትሮ) ስራ ህይወቱን እየመራ ነው፡፡ አሁን ላይ የ5 ልጆች አባት ሲሆን የመጀመሪያ ልጁም 7ኛ ክፍል እንደደረሰና ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱትንም የትምህርት ወጪ፣ ቀለብ፣ ልብስ እና ሌሎች ነገሮችንም ሸፍኖ የሚያስተዳድራቸው ከሚሰራው የሊስትሮ ስራው እንደሆነ ይናገራል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤተሰቡንም ወደስራ በማሰማራት ደጋፊ እንዳገኘ ይገልጻል፡፡ የመጀመሪያ ልጁ የሊስትሮ ስራ እየሰራ ሲሆን የትዳር አጋሩ የሆነችው ባለቤቱ በሻይ ቡና ስራ ተሰማርታ ተደጋግፈው እየኖሩ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡
ወጣት ባትሪ ሰርቶ ከሚያገኘው ከዕለት ወጪው አትርፎ በቀን እስከ መቶ ብር እቁብ ይጥላል፡፡ “ቤተሰብ አፍርተህ ስትኖር ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ማሳብ ይገባል” የሚለው ባትሪ የቁጠባ ልምዱም የሚታማ አለመሆኑን ነው የተናገረው፡፡ ከቤተሰቡ አልፎ አቅመ ደካማ የሆኑ ወላጅ እናቱንም ይረዳል፡፡
በህጻንነት ዕድሜው ወድቆ በቀኝ እግሩ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ይነገራል፡፡ ቤተሰቦቹ በወቅቱ ትኩረት ባለመስጠታቸው ወደ ህክምና ተቋማት ሄዶ ከጉዳቱ መዳን አልቻለም፡፡ በእንብርክክ በመሄድ ዋጋ ያስከፈለውን ውጣ ውረድ እንዲጋፈጥ ተገደደ፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ሲማርም የዱላ ድጋፍን እየተጠቀመ ይማር እንደነበር ያስታውሳል። ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ከመጣ በኋላ ግን የአርባ ምንጭ አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ማዕከል ባደረገለት ድጋፍ በክራንች ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡
በእርሻ ስራ ከሚተዳደር ቤተሰብ የተገኘው ወጣት ባትሪ በአካባቢው ካለው የመሬት ጥበት የተነሳ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ እንደነበር ያስታውሳል፡፡
ከውስን የግብርና ስራ በተጨማሪ የቀን ስራ እየሰሩ የቤተሰቡን የእለት ጉርስ የሚሸፍኑትን አባቱን ማጣት ለመላው ቤተሰቡ ችግርን ይዞ ነበር የመጣው፡፡ የአባቱ በሞት መነጠቅ ደግሞ በችግር ላይ ሌላ ችግር ነበር፡፡ ለእሱም ቢሆን የትውልድ አካባቢውን ለመልቀቅ ዋና ምክንያቱ ይኸው ነበር።
ዛሬ ላይ ወጣት ባትሪ የቤተሰቡን ሀላፊነት ተሸክሟል፡፡ ለቤት ኪራይ ወጪ በወር 1 ሺህ ብር ይከፍላል፡፡ የቤተሰቡንም ቀለብ እንዲሁ። በሚኖርበት አካባቢ በሀዘን ቢሆን በደስታ የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፍነውም እሱ ነው፡፡
እንደዚህም ሆኖ ነገን አርቆ በማሰብ እቁብ በመጣል የቤተሰቡን ህይወት ለመለወጥ ላይ ታች ይላል፡፡ በክራንች እየተንቀሳቀሰ ከሊስትሮ ስራው በተጨማሪ በመኖሪያ አካባቢው ስራ ካገኘ ራሱን ደካማ አድርጎ አያይም፣ ይሰራል፡፡ ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ምሳሌ ሆኖ የመታየትም ዓላማ ያለው ነው፡፡
“የአስተሳሰብ ችግር ካልሆነ በስተቀር አካል ጉዳተኝነት ላለመስራት ምክንያት አይሆንም። መስራት ያስከብራል፡፡ ስራን ንቆ ወይም ራስን ደካማ አድርጎ መቁጠር መጨረሻው ውድቀት ነው፡፡ ስለዚህ እጄን አልሰጥም” ያለው ወጣት ባትሪ፣ አሁን ላይ ከሊስትሮ ስራው ጎን ለጎን የጫማ ማደስ (ስፌት) ስራ መጀመሩም ተጨማሪ የገቢ አቅምን ፈጥሮለታል፡፡
ቦታ ላይ እንዳይሰራ ባይከለከል ደግሞ ካልሲ፣ የጫማ ሶል፣ ቀበቶ፣ የጫማ ማሰሪያና ሌሎች ቀላል ነገሮችን የመነገድ ውጥን እንደነበረውም ያነሳል፡፡
“አካል ጉዳተኞች ከልመና ይልቅ ሰርተን መለወጥ ስንሻ የሚያጋጥመን ማነቆ ብዙ ነው፡፡ የማህበረሰቡን ተጽእኖ አልፈን ለስራ ስንገለጥ ወደ ኋላ የሚጎትተን ደግሞ ብዙ ነው፡፡ ለዚህ አንዱ በምስራበት ቦታ ተነስ መባሌ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡
“ተለዋጭ ቦታ ማዘጋጀት እንጂ ስራ እንዳቆም መገደዴ ብዙ የቤተሰብ አባላቴን ጭምር በረሃብ እንደመቅጣት ይቆጠራል፡፡ ይህ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ እጂን ለልመና አልዘረጋሁም፤ ሰርቼ ልብላ ነው ያልኩት፤ ይህ ደግሞ ተቀባይነት ያለው ሀሳብ ነው፡፡
“ቁጭ ብዬ መስራት የምችላቸው በርካታ የስራ አማራጮች አሉኝ፡፡ ለዚህ ግን የተመቻቸ ቦታ ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ በርካታ አካል ጉዳተኞች ትምህርታቸውን አጠናቀው ዲግሪያቸውን ይዘው ስራ አልባ የሆኑት የስራ ቦታ ስላጡ ነው፡፡
“አካል ጉዳተኛ አንዳንድ ጊዜ ለልመና የሚያጋልጣቸው ችግር ነው፡፡ ሁሉንም ማለት ባይቻልም፡፡ ስራ አጥቶ፣ ልስራ ሲል ደግሞ ቦታ አለያም ብድር ሲያጣ መውደቂያው ምን ሊሆን ይችላል? ያው ልመና እንጂ፡፡ መንግስት በዚህ ላይ ልዩ ትኩረት ሊያደርግ ይገባል” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
More Stories
“ጉንፋን በአንቲባዮቲክስ መድሀኒቶች አይታከምም” – ዶክተር ሚስጥር አወቀ
እርቅ
የአምራች ዘርፉን የመቀላቀል ውጥን