ኮንፈረንስ ቱሪዝም
በአለምሸት ግርማ
የቱሪዝም ዘርፍ በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረውን ድርሻ ለማሳደግ ነባርና አዳዲስ የመዳረሻ ልማቶችን ማካሄድ፣ የመስህብ ሀብቶችን ማስተዋወቅ እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት የሚመጥን መዋቅራዊ አደረጃጀትና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ አሠራር መዘርጋትም ሌላው ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ይጠቁማሉ።
ሀገራችን የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች ልማታዊ እንቅስቃሴዎችዋ የአለምን ትኩረት እየሳበች ትገኛለች። ከቀድሞ በተለየ ሁኔታ በርካታ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች የሚስተናገዱባት ከተማ እየሆነች ነው፡፡
ቀዳሚ መዳረሻ የመሆን አቅሟ ከጊዜ ወደ ጊዜ እውን እየሆነ ይገኛል። በተለይም አዲስ አበባን ለነዋሪዎችዋ ምቹ ከተማ ለማድረግ በሚደረገው ጉዞ በርካታ ሰው ሰራሽ መስህቦች ተገንብተዋል። ከፅዳትና ውበት ጋር በተገናኘም ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል።
እንዲሁም በእንግዳ ተቀባይነቷም ተመራጭ እንድትሆን፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው የአገልግሎት አሰጣጥን፣ ደኅንነትን እና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የቱሪዝም አቅርቦትን ለማዳበር በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል የተቀናጀ ስራ እየተከናወነ ነው።
በመሆኑም ሀገራችን 46ኛውን የካፍ መደበኛ አጠቃላይ ጉባኤን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ጉባኤዎችን የማስተናገድ ዕድሉን በማግኘቷ በትጋት እየተወጣች ትገኛለች። በቅርቡ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ከረሃብ ነጻ ዓለም (World without Hunger) ጉባኤ መካሔዱን ተከትሎ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እንግዶችን በሰላም አስተናግዳ ሸኝታለች።
ረሃብን በማጥፋት ለሁሉም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ርብርብ ፍሬ እንዲያፈራ ዓላማ ያደረገው ይህ ጉባኤ ዓለም አቀፍ መሪዎችን፣ ባለሙያዎችን እና ተቆርቋሪዎችን በአንድ ላይ አሳትፏል።
ጉባኤው ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በሀገራችን ባለፉት ስድስት ዓመታት በግብርና ሽግግር እና ምርታማነት ላይ በማተኮር የሠራነው ሥራ የታረሰ መሬታችንን እጥፍ በማድረስ ከፍ ያለ እሴት ባላቸው የኢንደስትሪ አዝርዕት ምርት ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አስገኝቷል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ ማስነበባቸው ይታወሳል።
አክለውም፡- “ከረሃብ ነጻ ዓለም ጉባኤን ስናጠናቅቅ፣ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ውይይቶች የተሳኩ ይሆኑ ዘንድ አስተዋፅዖ ያበረከቱትን ተሳታፊዎች ከልብ አመስግነዋል። አርባ ቢሊዮን ዛፎች በተተከሉበት ምርታማነትን በሚያሳድጉ የለውጥ ሥራዎች፣ ድርቅን በሚቋቋሙ አዝርዕት ልማት፣ እንዲሁም በአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብር ሥራዎች አማካኝነት በዘላቂ የግብርና ሥራ የታየው የኢትዮጵያ እርምጃ በጉባኤው ቀርቧል።
“በኢትዮጵያ ታምርት፣ በአግሮ ኢንደስትሪ ፓርኮች ጥምር የሥራ ፈጠራ ሥራ፣ በገቢ እድገት እና ጽናት የታዩት ኢንቨስትመንቶች በዓለም የግብርና ዘርፍ የኢትዮጵያን ሚና አጠናክረውታል። ረሃብን መዋጋት የጋራ ምላሽን ይሻል።
“ለዚህም ለምግብ ዋስትና የሚሆን የዓለም አቀፍ ድጋፍ አቅርቦት፣ ድንበር ዘለል የሆነ የእውቀት ማካፈል ልምምድ፣ ለፍትሃዊ ተደራሽነት የሚረዳ የፖሊሲ መናበብ ብሎም ለሴቶች ትኩረት የሚሰጥ የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደሮች ድጋፍ ሥራ አስፈላጊ ነው፡፡” ሲሉ በሀገራችን የተሰሩ የልማት ስራዎች እውቅና ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።
ጉባኤው በሀገራችን መካሔዱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን በተለይም ለኢኮኖሚው ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው። እንዲሁም በሆቴልና መሰል አገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ አልሚዎችም ብርታት ከመሆኑም በላይ የኮንፈረንስ ቱሪዝም የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ የሚያጠናክር ነው።
ቱሪዝም በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጣ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ሚና ተኪ እንደሌለውም ይገለጻል። በተለይ የአገልግሎት ሰጪዎች፣ የትራንስፖርትና የአስጎብኚ ባለሙያዎችና ቱር ኦፕሬተሮች ሚና ከፍተኛ ነው።
መንግሥት የመስህብ ሥፍራዎችን የመለየት፣ የማልማት፣ የመጠበቅና የጎብኚዎችን ደህንነት የማረጋገጥ ድርሻን ይውሰድ እንጂ፤ ከግል ዘርፉ ጋር ካልተቀናጀ የሚፈለገው ውጤት ሊመጣ አይችልም።
በሀገራችንም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እያደገ የመጣ ሲሆን ከሰሞኑ የተመረቀው የግል ኢንደስትሪ ዘርፍም አንዱ ማሳያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል አልሚዎች ወደ ትልልቅ እና የተደራጀ ኢንደስትሪ ዘርፍ ውስጥ መግባት አለባቸው ሲሉም አበረታተዋል።
የግል ባለሃብቶች በሆቴልና በመዝናኛ ዘርፍ እንዲሁም በተለያዩ መስኮች እየተሳተፉ እንደሆነ እሙን ነው። ይህም መንግስት የሚያደርገውን የልማት ጉዞ የሚያፋጥን ነው። በተለይም በቱሪዝሙ ዘርፍ በርካታ መስህቦች እየተገነቡ ባሉበት በዚህ ወቅት አልሚዎችም ትልቅ አበርክቶ እንዳላቸው እየታየ ነው።
በዘርፉ የዓለም አቀፍ ቱሪስት ፍሰት ከፍተኛ እንዲሆን የዘርፉ ባለሙያዎች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። የኢትዮጵያን የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮና ሌሎች የቱሪዝም መስህቦችን ለጎብኚዎች በማስተዋወቅ ከፍተኛ የቱሪስት ቁጥር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ፤ ቆይታቸውንም በማራዘም፣ የሀገሪቱን ገፅታና ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲያሳድግ የማድረግ ኃላፊነትም ይጠበቅባቸዋል።
የውጭ ሀገር ዜጎች በተለያየ አጋጣሚ የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻ መስህቦች ለመጎብኘት በሚመጡበት ወቅት የጉዞ እቅድ በማውጣት፣ የሚያርፉበትን ሆቴል፣ የሚጎበኟቸውን መስህቦች በማመቻቸት፣ በቆይታቸው የተሻለ ልምድና ተዝናኖትን አግኝተው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ በኩል ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።
በኢትዮጵያ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች እየተገነቡ ስለመሆናቸውም እየተመለከትን ነው። መስህቦች ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች በብዛት እንዲመጡ ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።
ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸው ወንጪ፣ ጎርጎራ፣ በቅርቡ የተመረቀው በበሰቃ ሃይቅ ዳርቻ ላይ እጅግ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች፣ አዳራሽ፣ ሲኒማ ቤት የመዝናኛ ስፍራዎች፣ ስፓ፣ እንዲሁም የፍራፍሬ ልማት እና የሌማት ትሩፋትን አካቶ የያዘው የቤኑና መንደር ተጠቃሾች ናቸው።
ቱሪዝም በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ልዩ ድርሻ እንዲኖረው መዳረሻዎችን ማልማት፣ ማስተዋወቅና ነባሮቹን ከጉዳት መጠበቅ አስፈላጊ ነው። ይህንን ማድረግ ከተቻለ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የሚያጠናክሩ ይሆናሉ።
በተለይም ዓለም ዓቀፍና አህጉራዊ ጉባኤዎችና መድረኮች በሀገራችን መካሔዳቸው የሀገሪቱን የቱሪዝም ፍሰት የሚያበረታታ ነው። የዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ተከትሎ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሽፋንም የሚገኝ በመሆኑ አጋጣሚው የቱሪስት መስህቦችን ለማስተዋወቅ የሚያስችልም ነው።
መንግሥት መዳረሻዎችን ከማልማት፣ ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቦታዎችን ከመጠበቅ ባሻገር ኢንደስትሪውን ከሚያንቀሳቅሱ መሰል ድርጅቶች ጋር በቅርበት መሥራት ይጠበቅበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም “በቱሪዝም ሴክተር የጀመርነውን እንቅስቃሴ አጠናክረን በመቀጠል የኢትዮጵያን ልክ ለዓለም እንገልጣለን” ሲሉም በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አስፍረዋል።
የቱሪዝም ዘርፍ አንዴ ተሰርቶ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ አሁንም መንግሥት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ አጠናክሮ መስራት ይጠበቅበታል። በዘርፉ ተወዳዳሪና ተመራጭ ለመሆን አሁን ከተሰሩት መዳረሻዎች በተጨማሪ ሌሎችም በዘርፉ እንዲሰማሩ መደረግ አለባቸው። በተለይም ከመሰረተ ልማትና ከቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ በየወቅቱ ማዘመን የሚጠበቅ ነው።
ስራው የተቀናጀ ምልከታን ስለሚፈልግ እና በአንድ ዘርፍ ብቻ የሚሠራ ባለመሆኑ የሁሉንም የጋራ ትብብር ይጠይቃል።
ሀገራችን በቀጣይም ሌሎች የዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማሰናዳት የተመረጠችበት ሁኔታ በመኖሩ ከኮንፈረንስ ቱሪዝም ተጠቃሚነቷን አስጠብቃ ትቀጥላለች።
More Stories
“ኩርፊያ እና ንትርክ አልወድም” – ጋዜጠኛ ገናናው ለማ
በ2030 ደህንነቱ የተጠበቀ መጸዳጃ ቤት ለሁሉም
የትራምፕ “ትራይፌክታ” ጣምራ ሥልጣን