ያለውን ውስን ሀብት በተገቢው በመጠቀም ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት አስታወቀ

አስተዳደር ጽ/ቤቱ የ2017 ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2018 ዓ.ም መሪ ዕቅድ ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡

በመድረኩ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ሮቤ እንደገለፁት፤ በ2017 በጀት ዓመት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ከባለድርሻዎች ጋር በቅንጅት ተግባራትን በመምራታቸው አበረታች ውጤት ከመመዝገቡ ባለፈ በርካታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡

በአዲሱ በጀት ዓመት ያለውን ውስን ሀብት በተገቢው በመጠቀም ተጀምረው ያልተጠናቀቁ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን አቶ ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው በጀት አመት አፈፃፀም የተስተዋሉ ውስንነቶችን በማረም በስኬት የተነሱትን ይበልጥ በማጠናከር የዓመቱን ተግባር በመምራት ለተሻለ ውጤት ጥረት እንደሚያደርጉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሀሳብ አንስተዋል፡፡

የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊና ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ተገኝ ታደሰ፤ ባለፉት ዓመታት በሁሉም ዘርፎች የተገኙ ስኬቶች በጋራ ጥረት የመጡ በመሆናቸው በየደረጃው የተሰጣችውን ኃላፊነት በተገቢው የተወጡ ባለድርሻዎችን አመስግነዋል፡፡

በዞኑ ያለውን እምቅ ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም እንደ ሀገር ለዘመናት በድህነት የቆየንበት ዓመታትን በመረዳት በቁጭት ተግባራትን ማከናወንና ለለውጥ መትጋት እንደሚያስፈልግ አቶ ተገኝ ገልጸዋል።

በመድረኩ በ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም መነሻ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው መዋቅሮች እና ግለሰቦች ማበረታቻ ሽልማትና የዕውቅና ስነ-ስርዓት መርሃ ግብር እንዲሁም ረጅም ዓመታትን አገልግለው በጡረታ ለተሰናበቱ የሀገር ባለውለታዎች የክብር ሽኝት ተደርጓል።

ዘጋቢ፡ ውብሸት ኃ/ማርያም – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን